View in English alphabet 
 | Friday, April 26, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

በአሜሪካ ማዕከል የዳላስ ንዑስ ማዕከል በዳላስ ከተማ በቴክሳስ ግዛት “መጪው ዘመን እንዳይቀድመን እንነሳ” በሚል መሪ ቃል ዐውደ ርእይ በተሳካ ሁኔታ ቀረበ።

 

በማኅበረ  ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል የዳላስ ንዑስ ማዕከልመጪው ዘመን እንዳይቀድመን እንነሳ” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 24-25 ቀን 2008 .  በዳላስ ከተማ ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ በርካታ ምእመናን እንደጎበኙት ተገለጸ።

 

በዐውደ ርእዩ  መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የካልፎርኒያና አከባቢው ሀገረ ስብከት ጸሐፊ መልአከ ብርሃን ቀሲስ መስፍን ደምሴ ባስተላለፉት መልእክት ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቷ መሰረተ እምነት ፣ ሥረዓትና ትውፊት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያደርገውን ሁለገብ ጥረት አድንቀው በተለይም በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን አጥሯ እንዳይነቃነቅ ፣ ሥርዓቷም እንዳይበረዝ ምእመኑን በማሳወቅና በማንቃት ማኅበሩ እያደረገ ያለውን ተግባር ሁሉም የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባል ሊደግፈው እንደሚገባ አስታውቀዋል። ወደፊትም ማኅበሩ ለሚያደርገው መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ ሀገረ ስብከታቸው የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

 

የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ መልአከ ምህረት አባ ምህረት ዘውዴም በበኩላቸው ማኅበሩ ባለፉት  ሁለት አስርት ዓመታት ያደረገውን መንፈሳዊ አገልግሎት አድንቀው ቤተ ክርስቲያኒቷ ለሌላው ዓለም የምትተርፍና ዘመን ተሻጋሪ እንድትሆን ማኅበሩ የሚያደርገውን ጥረት አስታውሰው ወደፊትም እንደቀድሞው በጥበብና በጸሎት ተግቶ መሥራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል። 

ዐውደ ርእዩ በተለያዩ ትእይንቶች ተከፋፍሎ የቀረበ ሲሆን እነዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሦስቱ ሕግጋት ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የ2000 ዓመት ጉዞ ፣ ሥነ ጥበባት ፣ የዘመን አቆጣጠር ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ በሕግ፣ በማኅበራዊ ሕይወት እና በልማት ፣ ቤተ ክርስቲያን ነገ እና የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት የሚሉት ናቸው።

ዐውደ ርእዩን የተመለከቱ ምእመናን እንደገለጹት በዐውደ ርእዩ ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ትምህርት ያገኙበት ፣ ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ እንድያውቁ ያደረገና በድርሻቸውም ምን ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በተለይም ቤተ ክርስቲያኗ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ በመረጃ ተደግፎ የቀረበ በመሆኑና ከትናንትና እና ከዛሬ ተሞክሮዎች በመነሳት ነገ ምን ይጠበቅብናል የሚሉ ጥያቂዎች እንደፈጠረባቸው ምእመናኑ አስታውቀዋል።

ዐውደ ርእዩ በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ለእይታ ቀርቧል። በመሆኑም የውጪ ሀገር ዜጎችና በአሜሪካ ሀገር የተወለዱ ኢትዮጵያዊያን ጭምር የጎበኙት ሲሆን በተለይም በአካባቢው ከሚገኘው የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመጡ ካህናት፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትና ምእመናን ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ትምህርት እንዲያገኙ መልካም ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

 

በመጨረሻም የአሜሪካ ማእከል ሰብሳቢ / ሕልምነህ ስንሻው ለዐውደ ርእዩ መሳካት የተባበሩትን ሁሉ አመስግነው ማኅበረ ቅዱሳን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያንን ዘመን ተሻጋሪ አገልግሎት ለምዕመናን እንዲሁም ለሌላው የዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ  ይህን እና መሰል የዐውደ ርእይ  ዝግጅቶችን በቀጣይነትም በሌሎች የአማሪካ ግዛቶች ለማሳየት እቅዱ አንዳለ አስታውቋል ።

 

በዚህ ዐውደ ርእይ ዝግጅት በርካታ ምዕመናን ክፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን በገንዘብ በሃሳብ እና በተለያየ ሁኔታ ትብብር ላደረጉ ምእመናን እና ድርጅቶች ማዕከሉ ከፍ ያለ ምስጋና ያቀርባል።


Written By: useducation
Date Posted: 4/10/2016
Number of Views: 3834

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement