View in English alphabet 
 | Thursday, April 25, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል 18ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል 18 ጠቅላላ ጉባኤውን በሲያትል ዋሺንግተን ግንቦት 20 እና 21 ቀን ተካሄደ። በጉባኤው ከ400 በላይ የማዕከሉ ኣባላት የተሳተፉ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው ካህናት፣ የዲሲና አካባቢው እና የካሊፎርንያና ምዕራብ  አኅጉረ ስብከት ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንገዶች ተገኝተዋል።

ጉባኤው ቅዳሜ በጸሎተ ኪዳን ተጀምሮ የማዕከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር ሕልምነህ ስንሻው  ጥሪ የተደረገላቸውን ካህናት፣ እንግዶች፣ የጉባኤውን አባላት እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው በማዕከሉ የተተገበሩ ዋና ዋና የአገልግሎት ሥራዎችን ዘግበዋል። የዲሲ እና አካባቢው አገረ ስብከት ጸሐፊ መልአከ ሰላም ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ የአገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን መልእክት ለጉባኤው አስተላልፈዋል። በጉባኤው መሪ ቃል “ሥራ የሞላበት ታላቅ በር” /1 ቆሮ 16፡9/ በሚል ርዕስ ትምሕርተ ወንጌል በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ተሰጥቶ የማዕከሉ ዓመታዊ ጠቅላላ የአገልግሎት እና የሂሳብ ሪፖርት፣ እንዲሁም የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ሪፖርት ቀርቦ በጉባኤው ጸድቋል። በቀረበው ሪፖርት በተለያዩ ንዑሳን ማዕከላት በርካታ ትምህርታዊ ጉባኤዎች እንደተካሄዱ፣ በተለያዩ ከተሞች የማኅበረሰብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንደተጀመረ፣ ለገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም ኢኣማንያንን ለማስተማር እና ለማስጠመቅ ለተዘረጋው የስብከተ ወንጌል ፕሮጀክት ከአባላት እና ከምዕመናን የተሰበሰቡ እርዳታዎች ወደ ዋናው ማዕከል እንደተላከ ተገልጾአል። 

የዋናው ማዕከል ተወካይ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ / ሙሉጌታ ሥዩም የዋናውን ማዕከል መልእክት እና ሪፖርት አቅርበው ከጉባኤው ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ በተመለከተ ስለአመጣጡ እና አሁን ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል። እንዲሁም ዝክረ አበው በሚል መርሐ ግብር የሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ሰባተኛ ዓመት የዕረፍታቸውን መታሰቢያ በማድረግ የተዘጋጀ የመታሰብያ ፊልም ታየቷል። ሊቀ ካህናት ኃይለሥላሴ ዓለማየሁ የካሊፎርንያና ምዕራብ አገረ ስብከት የሰበካ አስተዳደር መንፈሳዊ ጉባኤ ኃላፊና የዴንቨር ደብረ ሰላም  መድሃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አሰተዳዳሪ ስለ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ምስክርነት እና የማኅበሩ መካሪ በመሆን ስለነበራቸው ከፍተኛ አስተዋጽዖ አውስተዋል። ቀደም ብለውም ስለብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የቀድሞው የትግራይ ሊቀጳጳስ ሕይወት፣ አገልግሎት፣ እና ታላቅ መንፈሳዊ አባትነት፣ በትምህርታቸው እና በተለያዩ አጋጣሚዎች ስላስተላለፏቸው ጠቃሚ ምክሮች እና ብፁዓን አባቶች ስለእርሳቸው የተናገሩትን ምስክርነት በማወሳት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለነበራቸው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለጉባኤው ገለጻ አድርገዋል።

በሲያትል የኮፕቲክ ቅድስት ማርያም ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ አባ አርሳንዮስ ለጉባኤው ትምህርታዊ መልእክት አስተላልፈዋል። የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን አደጋ ላይ በነበረችበት ወቅት ትልቅ ለውጥ ያመጡቱ ወጣቱ ዲያቆን ሃቢብ ጊዮርጊስ እንደሆነ አውስተው እያንዳንዳችን ለቤተ ክርስቲያን ፍሬ ለማፍራት እና ልጆችንም በማስተማር መልካም ለውጥ ለማምጣት እንደምንችል ገልጸዋል።

በሁለቱ ቀን ጉባኤ በቤቴል እና ሲያትል የአቡነ ጎርጎርዮስ ሁለገብ ማዕከል ተማሪዎች ከተማሩት ትምህርት የሰኞን ውዳሴ ማርያም በዜማ እና በንባብ እንዲሁም ቅኔ እና የተለያዩ ማራኪ ዝግጅቶችን አቅርበዋል። የሲያትል ንዑስ ማዕከል አገልግሎት በሌሎችም ንዑሳን ማዕከላት እንዲጀመር ንዑስ ማዕከሉ የነበረውን ልምድ ለጉባኤው አካፍሏል።

 

እሁድ በቀጠለው ጉባኤ የማዕከሉ የመጪው ዓመት የአገልግሎት ክፍሎች እና የበጀት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ነሐሴ በሚደረገው የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀጥለው ስድስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድ ስለሚጸድቅ በአዲሱ ስልታዊ ዕቅድ መሠረት ዕቅዱን ለማስተካከል ከስድስት ወር በኋላ የማዕከሉ የዕቅድ ክለሳ እንደሚደረግ ተገልጾአል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ማዕከሉን ይመራ የነበረው የሥራ አስፈጻሚ የሥራ ዘመን ስለተፈጸመ፣ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ማዕከሉን በሥራ አስፈጻሚ አባልነት የሚመሩ 13 አባላት በጉባኤው ፊት በዕጣ ተመርጠው ጸሎት ተደርጎላቸዋል።

በመጨረሻም የማዕከሉ 18 ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ስለዝግጀቱ  የነበረውን ሂደት በዝርዝር ገልጾ ጉባኤው በዝማሬ እና በጸሎት ተጠናቋል። ቀጣዩ 19ኛው የማዕከሉ ጠቅላላ ጉባኤ በቦስተን፣ እንዲሁም 20ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በቨርጂንያ እንደሚካሄድ በመወሰን ጉባኤው ተጠናቋል።


Written By: useducation
Date Posted: 6/1/2016
Number of Views: 3787

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement