በዓውደ ጥናቱ ላይ በአቅራቢነት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መምህራን እና የውጭ ዜጎች የተሳተፉ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ በሀገሪቷ ሰላምና ልማት እንዲጠናከር ከማድረግ አንጻር ፤ የተለያዩ የእምነት ተቋማትና ኅብረተሰብ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ተቻችለውና ተከባብረው ለዘመናት እንዲኖሩ ከማስቻል አንጻር ፤ እንዲሁም በሥነ ጽሑፍ ፣ በቋንቋ ፣ በሥነ ዜማ እና በተለያዩ መስኮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ዝግጅቶች ቀርበው ውይይቶች ተካሂደዋል።
በዚህ ዓውደ ጥናት ላይ ከፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ ተቋማትና አካባቢዎች የመጡ ተሳታፊዎች የተገኙበት ሲሆን መርሐ ግብሩ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተካሂዷል። ዓውደ ጥናቱን በተመለከተ አንዳንድ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ይህ ዓይነቱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለተቀረው ዓለም የማስተዋወቁ ሥራ ማኅበሩ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው አስፈላጊነቱ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በውጪ ሀገር ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኩራትና ለሀገራችንም በብዙ መልኩ እንደሚጠቅም ገልጸዋል። በመጨረሻም ለዚህ መርሐ ግብር መሳካት ቦታ በማመቻቸት ፣ በቁሳ ቁስ አቅርቦት እና አስተርጓሚ በማዘጋጀት የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ላደረገው ከፍተኛ ትብብር እንዲሁም ለጥናት አቅቢዎችና ተሳታፊዎች የማኅበሩ ተወካይ ምስጋናቸውን አቅርበው ወደፊትም ይህን መሰል ዓውደ ጥናቶችን ማዕከሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጋር በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚያካሂድ ገልጸዋል።