View in English alphabet 
 | Friday, April 26, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

የሚኒያፖሊስ ንዑስ ማዕከል “ማዕዶት ዘቤተ ጉባኤ ወገዳማት” በሚል መሪ ቃል ዐውደ ርእይ አዘጋጀ።

በኢ//// ማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል የሚኒያፖሊስ ንዑስ ማዕከል “ማዕዶት ዘቤተ ጉባኤ ወገዳማት” በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ ፯-፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም (August 13-14, 2016) በሚኒያፖሊሰ ርዕሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቅጥር ግቢ ውስጥ ያዘጋጀውን ዐውደ ርእይ በርካታ ምእመናን እንደጎበኙት ተገለጸ።

ዐውደ ርእዩን የርዕሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ መልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል ሙላት የደብሩ አገልጋይ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በጸሎት የከፈቱ ሲሆን ከመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት በኋላም ዐውደ ርእዩን  እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል።  በተጨማሪም በሴንት ፖል ከተማ የምትገኘው የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ዘርዓ ዳዊት ብርሃኔ ከአጥቢያው ካህናትና ምዕመናን ጋር በመሆን ዐውደ ርእዩን ጎብኝተዋል።

ዐውደ ርእዩ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች የትምህርት እና የኑሮ ሁኔታ፣ ተግዳሮቶች እንዲሁም ማኅበረ ቅዱሳን በእነዚህ የቤተ ክርስቲያን ተቋማት ላይ እየሠራቸው ያሉትን የረዥምና የአጭር ጊዜ ፕሮጀክቶች እና የተገኙ ውጤቶች በስምንት ትዕይንቶች ተከፍለው የቀረቡበት ሲሆን እነዚህም፤

  1. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
  2. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማት፤
  3. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤቶች፤
  4. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለዓለም ያበረከቱት አስተዋጽዖ፤
  5. በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች የተከሰቱ ችግሮችና ያስከተሉት ጉዳት፤
  6. በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች የተከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ በማኀበረ ቅዱሳን የተወሰዱ መፍትሔዎች፤
  7. በማኀበረ ቅዱሳን የተከናወኑ ሥራዎችና የተገኙ ለውጦች፤
  8. ወደፊት ምን መደረግ አለበት? የሚሉት ናቸው።

 

ዐውደ ርእዩን የበለጠ ድምቀት እንዲኖረው ካደረጉት ትዕይንቶች ዋነኛው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ዲያቆናት በራሳቸው አነሳሽነት በአንድ አገልጋይ ካህን መምህርነት የአብነት ትምህርት አሰጣጥ ሂደትን በተዘጋጀላቸው ጎጆ ሥር ሆነው ሲማሩ ማቅረባቸው ነበር። ይህም ምዕመናን ቤተ ክርስቲያናችን የምታፈራቸው ሊቃውንት በምን ዓይነት ሁኔታ ተምረው ለማዕረግ እንደሚደርሱ በተግባር እነዲገነዘቡት አድርጓቸዋል።  ጥቂት የማይባሉ ምዕመናንም ደስታቸውን በእንባ ገልጸው፣ ይህን የመሳሰሉ መርሐ ግብሮችን ደጋግሞ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀው አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮችም ለመርዳት ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል። ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አባቶች እና ምዕመናን ስለ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ሰፊ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑን አስረድተዋል። 

በዐውደ ርእዩ ለምዕመናን ገለጻ በማድረግ እና በማስተባበር የሁለቱም አጥቢያዎች ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፣ ምዕመናን እና የንዑስ ማዕከሉ አባላት  ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሲሆን በዚሁም የአገልግሎት አንድነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።

በመርሐ ግብሩ ፍጻሜም የንዑስ ማዕከሉ ተወካይ ለዐውደ ርእዩ መሳካት ከካህናት ጀምሮ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ምዕምናን በሙሉ ላደረጉት አስተዋጽዖ እና ትብብር ከፍተኛ መንፈሳዊ ምሥጋና  አቅርበዋል።


Written By: useducation
Date Posted: 8/29/2016
Number of Views: 5934

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement