View in English alphabet 
 | Wednesday, December 12, 2018 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

ብጹእ አቡነ ፋኑኤል በሲያትል ከተማ በዓለ ጥምቀትን አከበሩ፤ ሐዋርያዊ የሥራ ጉብኝትም አደረጉ!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የካሊፎርኒያና ሰሜን ምእራብ አሜሪካ አኅጉረ ስብከት ሥር በሚገኘው የዋሽንግተን ስቴት ወረዳ ቤተክህነት አስተባባሪነት የከተራ እና የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ቅዳሜ ጥር ፲፫ እና እሑድ ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ/ም በከፍተኛ ድምቀት ተከብሮ ዋለ።

የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብጹእ አቡነ ፋኑኤል በከተማው ውስጥ ባሉ ስድስት አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት በሚከበረው በዓል ላይ ከከተራው እለት አንስቶ ተገኝተው ታቦታቱን በዝማሬ በእልልታና በሆታ አጅቦ የሚሄደውን ሕዝብ ባርከዋል። በማግስቱም እሑድ ሌሊት ቅዳሴ ከቀደሱ በኋላ በዓሉን የተመለከተ ሰፋ ያለ አጽናኝና ደስ የሚያሰኝ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል። ብጹእነታቸው በትምህርታቸው ክርስቲያኖች የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ኃጢአታችን የተደመሰሰበት ከማይጠፋው ሰማያዊ ዘር በመወለድ የልጅነት ሀብት የተቀበልንበት ዐቢይ በዓል መሆኑን ገልጠው፡ በጥምቀት ያገኘነውን የልጅነት ጸጋ ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል። እንደዚሁም የጥምቀት በዓልን በኅብረትና በአንድነት፡ በፍቅር በመረዳዳትና በመተሳሰብ ልናከብር እንደሚገባ አስረድተዋል። በተጨማሪም ክርስቲያኖች ሁላችን ለቅድስት ኦርቶዶ ክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አንድነትና በአስተዳደር ልዩነት ምክንያት ለተለያዩት አባቶች እርቀ ሰላም መጸለይና መሥራት እንደሚገባ አስተምረዋል።

 

ከዚሁ ቀደም ብሎ ብጹእነታቸው በዓሉን ለማክበር በሲያትል ከተማ በተገኙበት ወቅት በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል የሲያትል ንኡስ ማእከል ባደረገላቸው ግብዣ መሠረት ቅዳሜ ጥር ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ/ም የሲያትል አቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ የትምህርትና ማሰልጠኛ ሁለገብ ማእከል ባትል ከተማ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።

ብጹእነታቸው ከትምህርት ቤቱ እንደደረሱ ካህናት፡ የትምህርት ቤቱ መምህራን፡ ወላጆችና ተማሪዎች እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን የሲያትል ንኡስ ማእከል አባላት አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ በባትል ከተማ የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር መሪነት በየመማሪያ ክፍሉ እየተዘዋወሩ የጎበኙ ሲሆን በማእከሉ ስልጠና እና ትምህርት እየተሰጣቸው ያሉትን የሕጻናትና አዳጊ ተማሪዎች ትምህርት ተመልክተዋል። በዚሁም ወቅት ብጹእነታቸው ተማሪዎቹን እየባረኩ የአንገት መስቀል ስጦታ አበርክተውላቸዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ የትምህርት ቤቱ የአብነት መምህር የግእዝና የአማርኛ መወድስ ቅኔ አቅርበዋል። ተማሪዎቹም እየተማሩ ያሉትን ማሳያ የሚሆን የቃል ትምህርትና ምስባክ በብጹእነታቸው ፊት ያቀረቡ ሲሆን ትምህርት ቤቱ ስለሚሰጣቸው የትምህርት አይነቶች ለብጹእነታቸው ገለጻ ተደርጎላቸዋል። በተጨማሪም በማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማእከል የተተኪ ትውልድ ክፍል /የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ የትምህርትና ሥልጠና ሁለገብ ማእከል/ አማካኝነት ማኅበረ ቅዱሳን ለቅድስት ቤተክርስቲያናችን በውጭው ዓለም ተተኪ አገልጋዮችና ምእመናንን ለማፍራት እያደረገ ስላለው ጥረት ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በገለጻውም ወቅት የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ የትምህርትና ሥልጠና ሁለገብ ማእከል በሲያትል ንኡስ ማእከል ውስጥ በሲያትል በቤልቪዉ እና በባትል ሶስት ቦታዎች ፤ በሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ባሉ ተጨማሪ ሌሎች ሶስት ከተማዎች፤ በድምሩ በስድስት ትምህርት ቤቶች ከ፪፻ በላይ ተማሪዎች እያስተማረ እንደሚገኝ ተገልጿል።  በዚሁ ትልቅ ድካምና ጥረት በሚጠይቀው አገልግሎት ውስጥ በማኅበሩ ውስጥ ታቅፈው ከሚያገለግሉት አባላት በተጨማሪ በከተማው የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም ሰባክያነ ወንጌል መምህራን የኔ ድርሻ ነው በሚል ፍጹም ቅንዓትና ትጋት እያገለገሉ እንዳሉ እንደዚሁም የሕጻናትና አዳጊ ወጣቶች ወላጆች ተኪ የሌለው ድርሻ በመወጣት ላይ መሆናቸው ለብጹእነታቸው ተብራርቷል።

በመጨረሻም ብጹእነታቸውም ማኅበረ ቅዱሳን ከመነሻውም ጀምሮ ዓላማውና ሥራው ለቅድስት ቤተክርስቲያን ተተኪዎችን ማፍራትና ስብከተ ወንጌል ማስፋፋት መሆኑን እንደሚያውቁ፤ አሁንም እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው “ኅይንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ - በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ ” በማለት ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የተናገረውን ቃለ ትንቢት መነሻ በማድረግ ትምህርት ሰጥተዋል። ብጹእነታቸው በተመለከቱት ነገር በከፍተኛ ሁኔታ መደሰታቸውንና ይህም ሥራ ቤተክርስቲያን በዚህ ዘመን እየገጠማት ካለው ፈርጀ ብዙ ፈተና የተወሰነውን ሊቀርፍ የሚችል እንደሆነ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው በሥራው ውስጥ ያሉት ባለድርሻ አካላት፦ ማኅበረ ቅዱሳን፡ መምህራንና ወላጆች ፤ እንዲሁ እድለኛ ያሏቸውን ሕጻናት ተማሪዎች ሁሉ አመስግነዋል። በመጨረሻም ቃለ ምእዳን በማስተላለፍ የጉብኝት መርሐግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

ብጹእነታቸው በሲያትል ከተማ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ጥምቀተ ባህር በተከበረት ስፍራ እና በሲያትል ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል የቅድስት ቤተክርስቲያንን የአብነት ትምህርት በተገቢው ሁኔታ ለተከታተሉ አዳጊ ወጣቶች ማእረገ ዲቁና መስጠታቸው ታውቋል።


Written By: useducation
Date Posted: 1/30/2017
Number of Views: 2240

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement