View in English alphabet 
 | Thursday, March 21, 2019 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል 19ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል 19ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በቦስተን-ማሳቹስቴስ ከአርብ ግንቦት 18/2009 ዓ/ም እስከ እሑድ ግንቦት 20/2009 ዓ/ም ባሉት ቀናት አካሄደ። በጉባኤው ላይ የማኅበሩ አባላት፡ በቦስተን ከተማ የሚገኙ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ካህናት፣ የዲሲና አካባቢው እና የካሊፎርንያና ምዕራብ አሜሪካ አኅጉረ ስብከት ጸሐፊ መልአከ ሰላም ቀሲስ ዶ/ር መስፍን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጠቅላላ ጉባኤው አርብ ማምሻውን በአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተደረገ ጸሎተ ወንጌል ከተከፈተ በኋላ የእንግዶች አቀባበልና መስተንግዶ ተደርጓል። በማግስቱም ጉባኤው ቅዳሜ በጸሎተ ኪዳን ተጀምሮ የማዕከሉ ሰብሳቢ አቶ ማስተዋል ጥሪ የተደረገላቸውን ካህናት፣ እንግዶች፣ የጉባኤውን አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በማስተላለፍ በማዕከሉ የተተገበሩ ዋና ዋና የአገልግሎት ሥራዎችን ሪፖርት አድርገዋል። በመቀጠልም በ19ኛው ጠቅላላ ጉባኤ መሪ ቃል “በርቱና ሥሩ” በሚል ርዕስ ትምህርተ ወንጌል በመልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን ተሰጥቶ የማዕከሉ ዓመታዊ ጠቅላላ የአገልግሎት እና የሂሳብ ሪፖርት፣ እንዲሁም የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ሪፖርት ቀርቦ በጉባኤው ጸድቋል። በቀረበው ሪፖርት በተለያዩ ንዑሳን ማዕከላት በሕጻናትና አዳጊ ወጣቶች ዙርያ የተለያዩ ሥራዎች እንደተጀመሩ ፥ ለገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኗ በአገልግሎት ያልደረሰችባቸውን ሕዝቦች ለማስተማር እና ለማስጠመቅ ለተዘረጋው የስብከተ ወንጌል ፕሮጀክት ከአባላት እና ከምዕመናን የተሰበሰቡ እርዳታዎች ወደ ዋናው ማዕከል እንደተላከ ተገልጿል።

የዋናው ማዕከል ተወካይ መምህር ብርሃኑ አድማስ የዋናውን ማዕከል መልእክት እና ሪፖርት አቅርበው ከጉባኤው ለቀረበላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። እንዲሁም ዝክረ አበው በሚል መርሐ ግብር ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገ/አማኑኤል የቀደምት አበውን እና እማትን ሥራዎችና ስለነበራቸው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለጉባኤው ገለጻ አድርገዋል።  በመቀጠልም ቀሲስ ሰይፈሥላሴ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በዝርወት ምድር” በሚል ርእሰ ጉዳይ ለወጣቶችና አዳጊ ወጣቶች እየተሰጠ ባለው አገልግሎት ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ ሃሳብ የሚጠቁም፡ ለበለጠ ሥራና ኃላፊነት የሚጋብዝ ዝግጅት አቅርበዋል። እሑድ በቀጠለው ጉባኤ የማዕከሉ የመጪው ዓመት የአገልግሎት ክፍሎች እና የበጀት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመጨረሻም የማዕከሉ 19ኛ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ የቦስተን ንዑስ ማዕከል ስለዝግጀቱ ሂደት የነበረውን ሂደት በዝርዝር ገልጾና ለዝግጅቱ መሳካት የተራዱትን ሁሉ አመስግኗል። በማስከተልም ቀጣዩ 20ኛው የማዕከሉ ጠቅላላ ጉባኤ በቨርጂንያ ንዑስ ማዕከል አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ በመወሰን ጉባኤው በዝማሬ እና በጸሎት ተጠናቋል።  


Written By: useducation
Date Posted: 6/3/2017
Number of Views: 2916

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement