View in English alphabet 
 | Friday, April 26, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

የጨጎዴ ጉባኤ ቤትን ለመርዳት በአሜርካ የተደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ እንደነበር ተገለጸ።

በአሜሪካ ባሉ ሶስት አካላት አስተባባሪነት በቃጠሎ የወደመውን ጉባኤ ቤት መልሶ ለማቋቋም የተደረገው ጥሪ ስኬታማ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን አስተባባሪዎቹ ገለጹ።

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት በቋሪት ወረዳ ቤተ ክህነት ልዩ ስሙ ፈንገጣ በሚባል ቀበሌ በጨጎዴ ሐና የተቋቋመው፤ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ሲያፈራ የኖረውና እስከ አሁን ድረስም ሊቃውንትን የመተካት ተልእኮውን በመወጣት ላይ የሚገኘው የሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው የቅኔ ምስክር ጉባኤ ቤት ጥር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ረፋድ ላይ ድንገት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ሁለት መቶ ሃያ አምስት የደቀ መዛሙርት መኖሪያ ጎጆዎች፣ ልዩ ልዩ መጻሕፍት፣ ምግብ እና አልባሳት በአጠቃላይ ከሰባት መቶ ስልሳ ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመ ቀደም ሲል በማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ መዘገቡ ይታወሳል፡

ጉባኤ ቤቱን ወደ ነበረበት ህልውና ለመመለስ፤ ደቀ መዛሙርቱን ከመበተንና የጉባኤውን ወንበርም ከመታጠፍ ለመታደግ፥ እንዲሁም ይህንን የቅኔ ምስክር ቤት መልሶ በዘላቂነት ለማቋቋም እንዲያስችል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል ፥  በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የማኅበረ በዓለወልድ እና በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ በተለያዩ መንገዶች ምእመናንን የሚያሳትፍ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በማዘጋጀት ከ $65,000 በላይ መሰብሰቡን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በዲሲና በሲያትል ከተሞች በተደረገው የሕዝብ ጉባኤ $34,358.02 የተሰበሰበ ሲሆን፥ በድረ ገጽ (GoFundme and https://gedamat.org/ ) በተደረገው የምእመናን ልገሳ ደግሞ ከቀረጥ መልስ $17,229.24 ተገኝቷል። እንዲሁም በአሜርካ የማኅበረ ቅዱሳን ቅርንጫፎች በኩል ከአትላንታ፥ ችካጎ ፥ ዳላስ ፥ ሎሳንጀለስ ፥ ሚንሶታ  ንኡስ ማእከላት  $4,360 እንዲሁም በማኅበረ በዓለወልድ አስተባባሪነት  በሚኒያፖሊስ ካሉ ምእመናን $7000 ፥ ከችካጎ ደግሞ $1050 የተለገሰ ሲሆን በአጠቃላይ $65,588.71 ለጉባኤ ቤቱ መርጃ ተሰብስቧል።

በሶስቱም አካላት በአንድነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተደረገው ጥረት ወደፊትም መቀጠል እንዳለበት በአስተባባሪዎቹ የተጠቆመ ሲሆን ጉባኤ ቤቱን የመልሶ ማቋቋም ሂደትን በተመለከተ ለምእመናን ወቅታዊ መረጃ እንደሚሰጡ ጨምረው ገልጸው በሁሉም መልክ አስተዋጽዖ ላደረጉ ካህናትና ምእመናን ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

 

በእነዚህ ሶስቱ አካላት ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የእሳት ሰደድ ጉዳት ለደረሰበት በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ለደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ለመልሶ ማቋቋሚያ ከ20ሺ ዶላር በላይ እገዛ ማድረጋቸው ይታወሳል።


Written By: useducation
Date Posted: 6/8/2017
Number of Views: 8074

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement