View in English alphabet 
 | Thursday, March 21, 2019 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

“ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፣ድርሻችንን እንወቅ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው ልዩ ዐውደ ርእይ በአሜሪካ ለምእመናን ቀረበ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል “ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ ፣ ድርሻችንን እንወቅ” በሚል ርእስ በኢትዮጵያ ያዘጋጀውና በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም ለምዕመናን ያቀረበው 5ኛ ዙር ልዩ ዐውደ ርእይ በአሜሪካ ማዕከል ሥር ከሚገኙ ንዑሳን ማዕከላት አንዱ በሆነው በአትላንታ ንዑስ ማዕከል አዘጋጅነት የአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች ማኅበራትና ምዕመናንን በማሳተፍ ሰኔ 10 እና ሰኔ 11፣2009 June 17 and 18, 2017)፣ በከተማው በሚገኘው ደብል ትሪ ሆቴል ለምዕመናን ቀርቦ በስኬት መጠናቀቁን የንዑስ ማዕከሉ ጽ/ቤትና የዝግጅት ኮሚቴው አስታወቁ።

በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይም በርካታ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ካህናት፣ዲያቆናትና ምዕመናን የተገኙ ሲሆን የዐውደ ርእዩ መክፈቻ ሥነሥርዓት በጸሎተ ወንጌል ከተጀመረ በኋላ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት የብጹእ አቡነ ፋኑኤል መልእክትና ቃለ ምእዳን በመጋቢ ሃዲስ ይልማ ቸርነት የአትላንታ ዳግማዊ ቁልቢ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ቀርቧል። በመልዕክቱም ይህን መሰል ተግባር ተጠናክሮ በሌሎች ከተሞች እንዲሠራበት አሳስበው በዚህ ሂደት ውስጥ የሀገረ ስብከቱ ድጋፍም እንደማይለይ ገልጸዋል:: በተለይ ዐውደ ርእዩን ለእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች በሚችሉት ቋንቋ ተተርጉሞ ለማቅረብ የተደረገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ሥራ እንደሆነ ጠቁሟል። በመቀጠል በንዑስ ማዕከሉ በኩል የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ከተላለፈ በኋላ ዐውደ ርእዩ ለተመልካች በአባቶች ቡራኬ ተከፍቷል።

በመክፈቻው ላይ የነበሩ ተመልካቾች ቁጥር ከመብዛቱ የተነሳ ለሁለት በመክፈል የተጀመረው ዐውደ ርእይ በሁለቱም ቀናት ያለማቋረጥ የተካሄደ ሲሆን በአጠቃላይ በርካታ ካህናትና ምእመናን እንዲሁም አዳጊ ሕጻናትና ወጣቶችበእንግሊዝኛ ቋንቋጎብኝተውታል። በተጨማሪም በአቅራቢያ ከሚገኙ ክፍለ ግዛቶች (ስቴቶች) ጭምር ዐውደ ርእዩን ለመመልከት ከ4 እስከ 10 ሰዓት በመንዳት የተገኙ እንደነበሩ  ለማወቅ ተችሏል። በዐውደ ርዕዩ የተገኙ ጎብኝዎች በሰጡት አስተያየት ዝግጅቱ የቤተ ክርስቲያንን አስተዋጽዖ ፥ ፈተናዎችና የምእመናንን ድርሻ በግልጽ እንዳመለከታቸው ገልጸው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሁሉንም ምእመን እንደሚመለከት መገንዘባቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ቀናት በአጠቃላይ 103 የአብነት ተማሪዎችን በአንድ ለአንድ ድጋፍ ትምህርት ለመርዳትና ለማስተማር ቃል የተገባ ሲሆን አንዳንድ ምእመናን ከ4 እስከ 10 የአብነት ተማሪዎችን ለማስተማር ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም $2,628 ለጎንደር በአታ የቅኔ ጉባኤ ቤት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ተለግሷል።

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ከአባቶች መልእክት የተላለፈ ሲሆን አገልግሎቱ ያማረ ነበር። እግዚአብሔር ይመስገን። ስለዚህ የኛ ድካም እንዳለ ሆኖ እኛ ሠራን ብለን እንዳንታበይ በማለት አባታዊ ምክራቸውን የለገሱት የአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቀሲስ ያዕቆብ “ለዚህ ሁሉ መሳካት ምክንያቱ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ስለሆነ ነው” በማለት ገልጸው በዚህ ሥራ ብቻ ንዑስ ማዕከሉ እንዳይወሰን ያሳሰቡ ሲሆን የአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ ማንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ቀሲስ እርገተቃልም በበኩላቸው “የአገልግሎቱ በር ተከፍቷል አሁን ታሪክ ተቀይሯል ማኅበሩ በአትላንታ ሰፋፊ ሥራዎች መስራት ይጠበቅበታል ፤ ከሕዝቡ ጥያቄና አስተያየት የተረዳነው ይህንን ነው ስለዚህ በርቱ” በማለት አባታዊ ምክራቸውን በመለገስ መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል።

ለዚህ መርሐ ግብር መሳካት ትብብር ላደረጉት የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳደር አካላት ፥ የአካባቢው ሰንበት ት/ቤት አባላት ፥ ድጋፍ/ስፖንሰር/ በማድረግ ለተባበሩ የግል ድርጅቶች፤ እንዲሁም ለተለያዩ የሚዲያ አካላት ላቅ ያለ ምስጋና አዘጋጅ ክፍሉ አቅርቧል።

በተያያዘ ዜና ይኸው ዐውደ ርእይ በሚቀጥለው ቅዳሜና እሑድ ሰኔ 17 እና ሰኔ 18 ቀን 2009 ዓ/ም June 24 and June 25, 2017) በዋሽንግተን ስቴት ሲያትል ከተማ እንደሚቀርብ የአሜሪካ ማዕከል አስታውቋል።


Written By: useducation
Date Posted: 6/22/2017
Number of Views: 8164

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement