View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

፭ኛው ዙር ዐውደ ርእይ በአሜሪካ ሀገር በተለያዩ ግዛቶች ለሕዝብ እይታ ቀረበ::

‹‹የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ›› በሚል ርእስ የተዘጋጀው ፭ኛው ዙር የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ በአሜሪካ ሀገር በተለያዩ ግዛቶች መቅረቡን የአሜሪካ ማእከል አስታወቀ፡፡ በዳላስ ፣ በናሽቪል ፣ በቦስተን ፣ በችካጎ እና በሎሳንጀለስ ንዑስ ማዕከላት ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የቀረበው ይሄው ዐውደ ርእይ በበርካታ ካህናት እና ምእመናን ተጎብኝቷል።

ዐውደ ርእዩ በዋናነት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን መሠረተ እምነት ለምእመናን ለማስጨበጥ፣ በየጊዜው ለሚነሱ ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች ምእመናን እንዳይፈተኑና እንዲጠነቀቁ ለማድረግ ፣ ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው የገጠሟትን ተግዳሮቶች እንዴት ባለ ድል አድራጊነት እና ሰማእትነት እንደተወጣችው ለማስታወስ እና የቤተ ክርስቲያን ተእልኮ ለመፈጸም ምን ላድርግ የሚልና ድርሻውን የተረዳ እና በተግባር የሚፈጽም ምእመን ለማፍራት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

ከየአጥቢያው የተገኙ ምእመናንም ዐውደ ርእዩን ከጎበኙ በኋላ በሰጡት አስተያየቶች ዐውደ ርእዩ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አሰተምህሮ በጥልቀት የተዘጋጀ እና እያንዳንዱ ምእመን የድርሻውን እንዲወጣ የሚያተጋ አቀራረብ እንደነበረው ገልጸዋል። በተለይም ዐውደ ርእዩ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ጭምር መዘጋጀቱ ብዙ አዳጊ እና ወጣቶች ስለቤተ ክርስቲያናቸው የበለጠ ለመማር ጉጉት እንዲያድርባቸው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ከብዙ ወላጆች አስተያየት መረዳት ተችሏል።

በሁሉም ከተሞች ለሁለት ቀናት ዐውደ ርእዩ በቀረበበት ወቅት የአውደ ርእዩ ታዳሚዎች የአብነት ተማሪዎችን በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አንድ ለአንድ ድጋፍ ለመርዳት እና ለማስተማር እንዲሁም ማኅበሩ በገጠር እና ጠረፋማ አከባቢዎች ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት የጀመረውን ፕሮጀክት በገንዘብ ለመደገፍ ቃል ተገብቷል። በዐውደ ርእዩ ዝግጅት ለተባበሩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ፣ ለሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ፣ ለምእመናንና ዝግጅቱን በመደገፍ (ስፖንሰር) በማድረግ ለተባበሩ ባለሃብቶች የአሜሪካ ማዕከል ምስጋናውን አቅርቧል።

ይሄው ዐውደ ርእይ በዚሁ የበጀት ዓመት በአሜሪካ ሀገር በአትላንታ ፣ በሲያትል ፣ በካሮላይና ፣ በእንዲያናፖሊስ እና በሚኒሶታ ከተሞች መቅረቡ ይታወሳል።

 


Written By: us.ict
Date Posted: 5/16/2018
Number of Views: 2933

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement