View in English alphabet 
 | Thursday, March 28, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

የአዳም አወዳደቅ

እግዚአብሔር አምላክ አምስት ቀን ሙሉ ዓለምን በሥነ ፍጥረት እያስጌጠ ካዘጋጀ በኋላ በ6ኛው ቀን ታላቁን የሥነ ፍጥረት እንግዳ ሰውን ፈጠረ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዱ «አንድ ደግ ሰው እንግዳ ሲጋብዝ አስቀድሞ ቤቱን፤ መብል መጠጡን ሌላውንም ነገር እንዲያዘጋጅ እግዚአሔር አስቀድሞ የሚተነፍሰውን አየር፤ የሚጠጣውን ውኃ፤ የሚበላውን ምግብ፤ የሚኖርባትን ገነት እንዲሁም ለአንክሮ ለተዘክሮ የሆኑትን ሁሉ ካዘጋጀ በኋላ አዳምን ፈጠረው፡፡»

እግዚአብሔር አምላክ አምስት ቀን ሙሉ ዓለምን በሥነ ፍጥረት እያስጌጠ ካዘጋጀ በኋላ በ6ኛው ቀን ታላቁን የሥነ ፍጥረት እንግዳ ሰውን ፈጠረ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዱ «አንድ ደግ ሰው እንግዳ ሲጋብዝ አስቀድሞ ቤቱን፤ መብል መጠጡን ሌላውንም ነገር እንዲያዘጋጅ እግዚአሔር አስቀድሞ የሚተነፍሰውን አየር፤ የሚጠጣውን ውኃ፤ የሚበላውን ምግብ፤ የሚኖርባትን ገነት እንዲሁም ለአንክሮ ለተዘክሮ የሆኑትን ሁሉ ካዘጋጀ በኋላ አዳምን ፈጠረው፡፡»

አዳም የተፈጠረው በነጻነት የዚህ ዓለም ገዥ፤ ናዛዥ ሆኖ ሊኖር ነው፡፡ በእግዚአብሔር አርአያና መልክ የተፈጠረ ብቸኛ ፍጡር ነው፡፡ «ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን እንስሳትንና ምንድርን ሁሉ፤ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ፡፡» ዘፍ. 1፤26፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም ያለውን ፍቅር በሥነ ፍጥረቱ፤ አክብሮ አልቆ በአርአያው በምሳሌው በመፍጠሩ፤ ከርሱ በታች በሰጠው የገዥነት ሥልጣን ታውቋል፡፡

 
ዕፀ በለስ ለምን ተፈጠረች?
1.  አዳም ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር እንዲገለጥ ነው፡፡
አንዳንድ የዋሐን «ዕፀ በለስ ባትፈጠር ኖሮ አዳም ባልተሳሳተም ነበር፡፡» እያለ የሞኝ ቁጭት ይቆጫሉ፡፡
 
ዕፀ በለስ የተፈጠረችው፡
1.  እግዚአብሔር ለአዳም ያለው ፍቅር ከመፍጠር እስከ መግቦት ባለው ተገልጧል፡፡ የአዳምስ? የአዳም ፍቅር የሚታወቀው ደግሞ የፈጣሪውን ሕግና ትእዛዝ በማክበር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው፤ የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው» ዮሐ. 14፤21፡፡ በማለት እንዳስተማረን፡፡ የእግዚአብሔር ወዳጅ ለመባል ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡
2.  «ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው» የእግዚአብሔር ትእዛዝ ያለው
3.  «የሚጠብቃትም» የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጠብቅ
 
እግዚአብሔርም የአዳም ፍቅር ይታወቅ ዘንድ ትእዛዝ መስጠት፤ አዳምም መጠበቅ ነበረበት፡፡ በመሆኑም ዕፀ በለስ የሕግ ዛፍ ሆና ተሰጠችው፡፡ «ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና» ዘፍ. 2፤16፡፡ ይህን ትእዛዝ በማክበር አዳም ከክብሩ ሳይጎድልበት ከጸጋው ሳይቀነስበት ለሰባት ዓመታት መኖሩን ሊቃውንት
ያስተምሩናል፡፡ «ትእዛዙን የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም ይኖርበታል፡፡» 1ዮሐ. 3፤24፡፡ እንደተባለ አዳም በእግዚአብሔር ቤት እግዚአብሔርም በአዳም ልቡና ኖሩ፡፡
 
2. ፍጡርነቱ ይታወቅ ዘንድ
ዲያብሎስ ፍጡርነቱን ረስቶ ፈጥሬያለሁ በማለቱ «ጥንቸል በሬን አክላለሁ» ብላ ፈንድታ እንደሞተችው እርሱም በትዕቢቱ ወደቀ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ለአዳም ፍጡር መሆኑንና ፈጣሪ እንዳለው የምታሳውቅ ምልክት/የተገዥነት/ ሰጠው፡፡ ትእዛዝ ሰጭ እንዳለው ትእዛዝ ተቀባይ በመሆኑ ታወቀ «ሁሉን ግዛ» ቢባልም «ሁሉን ካስገዛለት ከእግዚአብሔር» በታች መሆኑ አድርግ አታድርግ በሚለው ሕግ ታወቀ፡፡
 
3. ነፃ ፈቃዱ ይገለጥ ዘንድ
የአንድ ሰው ነፃ ፈቃዱ የሚታወቀው የመምረጥ መብት ሲኖረው ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን መመሪያ እንጂ ነፃ ፈቃድ አይሆንም፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም «ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና» ዘፍ. 2፤17፡፡
 
አዳም ሁለት ምርጫ ተሰጠው፡፡ የሚበላቸው ሌሎች ዛፎች የማይበላት ዕፀ በለስ፡፡ ሌሎችን ዛፎች ቢበላ በሕይወት ይኖራል፡፡ ዕፀ በለስን ቢበላ ግን ይሞታል፡፡ እሳትና ውኃ በፊቱ ቀርቦለታል ወደ ወደደው እጁን መዘርጋት የአዳም ድርሻ ነው፡፡
 
«ተመልከት፤ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፤ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ፡፡ በሕይወትም እንድትኖር እንድትበዛም፤ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር ትወድድ ዘንድ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ፡፡ ልብህ ግን ቢስት አንተም ባትሰማ፤ ብትታለልም ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድ ብታመልካቸውም ፈጽማችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ እነግራችኋለሁ፡፡»/ዘዳ. 3ዐ፤15-18/፡፡ በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይና ምድርን በአንተ ላይ እመሰክራለሁ፡፡ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው፤ ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ ዘዳ.3ዐ፤19-2ዐ፡፡
 
በመሆኑም ዕፀ በለስ የተፈጠረችው በነዚህ ሦስት ምክንያቶች እንጂ አዳምን ለማሳሳት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ይሳሳት ዘንድ አሳልፎ አልሰጠውም፤ አስተማረው መከረው እንጂ፡፡ የዕፀ በለስን የመፈጠሯን ምክንያት ባይነግረው ኖሮ አዳም ባለማወቅ ተሳሳተ ባልን ነበር፡፡
 
አዳም ወዶ ፈቅዶ እግዚአብሔርን እንዲያገለግል ለትእዛዙም እንዲገዛ እግዚአብሔር መብት ይሰጠው ዘንድ ዕፀ በለስን ባይፈጥርለት ኖሮ ወዶ ፈቅዶ መርጦ መታዘዙን ማወቅ ባልቻልን ነበር፡፡
 
ለምሳሌ አንድ አባት ልጆቹ ሥጋ ብቻ እንዲበሉለት ይፈልጋል፡፡ ጠንካራ ሆነው ማየት ስለሚፈልግ፡፡ ከሁለቱ ልጆቹ አንደኛው የሆድ በሽታ ስለያዘው ከሥጋ በቀር ሌላ ሊስማማወ ባለመቻሉ ሥጋ ይበላ ነበር፡፡ ሁለተኛው ልጁ ግን የአትክልት ምግብ በጣም ይወድ ነበር፡፡ ሥጋ በመብላቱ አባቱ እንደሚደሰት ስላወቀ ሥጋ መብላት ጀመረ፡፡ ከሁለቱ አባቱን ያስደሰተው ማነው?
 
የመጀመሪያው ልጅ ሥጋ የሚበላው አማራጭ ስላጣ ነው፡፡ ሁለተኛው ልጅ ግን ከራሱ ፍላጐት የአባቱን፤ ከራሱ ፈቃድ የአባቱን መርጦ ፈቃዱን ትቶ ነው፡፡
 
አዳምም እንዲሁ ነው፡፡ ዕፀ በለስ ባትኖር ኖሮ በፈቃዱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸሙ ባልታወቀ ነበር፡፡

Written By: host
Date Posted: 12/19/2007
Number of Views: 9996

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement