View in English alphabet 
 | Thursday, April 25, 2024 ..:: መቅድም ::.. Register  Login
  

የአዳም ውድቀት ስንል ምን ማለታችን ነው?

አዳም ወደቀ ስንል ጸጋው ተገፈፈ ባሕርይው ጐሰቆለ ማለታችን ነው፡፡

አዳም ወደቀ ስንል ጸጋው ተገፈፈ ባሕርይው ጐሰቆለ ማለታችን ነው፡፡

1.   ጸጋው ተገፈፈ
ራቁቱን ሆነ
ለአዳምና ለሔዋን የጸጋ ልብስ ነበራቸው፡፡ ዕፀ በለስን በልተው ትእዛዙን ሲሽሩ ግን ራቁታቸውን ሆኑ «የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ እነርሱም ራቁታቸውን እንደሆኑ ዐወቁ» ዘፍ. 3፤7፡፡ ተፋፈሩ፡፡
 
ኃይልን አጣ
ፈቃድ ነፍስ በፈቃደ ሥጋ ላይ የነበራትን ኃይል አጣች፡፡ የሰው ልጅ ለመብላት ባማረ፤ ለዓይን በሚያስጐመጅ ለጥበብ መልካም መስሎ በሚታይ ነገር /ዘፍ.3፤6/ ተሸፈነ፡፡ ሰው እንስሳትን መሰለ ለፈቃደ ሥጋም ድል ሆነ፡፡
 
«ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ፡፡» መዝ. 48፤12፡፡
 
ለእንስሳት ስም ያወጣ የነበረው አዳም ስም ያወጣላቸውን እንስሳት ፈራ፡፡ ከእግዚአብሔር ከአምላኩም ሸሸ፡፡ የፍቅር ድምፁን የሚያዳምጥበት መንፈሳዊ ኃይል አጣ፡፡ ኃጥእ ነውና ማንም ሳያሳድደው ሸሸ፡፡ ምሳሌ 28፤1 «የኃጥእ ሰው ፍርሃት በላዩ ይመጣበታል፡፡» ምሳሌ 1ዐ፤24፡፡
 
እንግዳ ሆነ
የገነት ባለርስት የዚህ ዓለም ጌታ የነበረው የሰው ልጅ ርስቱን በማጣት እንግዳ ሆነ፡፡ ርስቱን የሚናፍቅ፡፡ ለዚህም ነበር በብሉይ ዘመን የነበሩ አበው እንግዶች ነን ያሉት፡፡
 
ፈርኦንም ያዕቆብን የዕድሜህ ዘመን ስንት ዓመት ነው? አለው ያዕቆብም ለፈርዖን የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው. . .አለው፡፡ ዘፍ. 47፤8፡፡
 
«እኔ በምድር መጻተኛ ነኝና እንደ አባቶቼም እንግዳ ነኝ» መዝ. 38፤13፡፡
 
2.    ባሕይርው ጐሰቆለ
ሰላሙ ንአጣ
አዳም ሰላማዊ ሆኖ ነበር የተፈጠረው፡፡ ሕገ እግዚአብሔር ሲሽር ግን ሰላሙን አጣ፡፡ ተጨነቀ፡፡ ደነገጠ፡፡ ተሸሸገ፡፡ ኃጥእ በሰላም መኖር አይቻለውምና መደበቂያ ፈለገ፡፡

 ነጻነቱን አጣ

አዳም በነፃነት የሚኖር ነፃ ፍጡር ነበር፡፡ ሕይወትንም ሞትንም የመምረጥ መብት ነበረው፡፡ አሁን ግን ሞትን መርጦ በሞት ቀንበር ሥር ተያዘ፡፡ ሞት ሠለጠነበት፡፡ የሞት ባርያም ሆነ፡፡ «ከአዳም እስከ ሙሴ ሞት ነገሠ» ሮሜ. 5፤14፡፡ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ የአዳም ንጉሥነት ቀርቶ ባርያ ሆነ፡፡
 
ሕያውነትን አጣ
አዳም ሕያው ሆኖ ይኖር ዘንድ ቢፈጠርም ሞትን በገዛ እጁ በመጋበዙ ሟች ሆነ፡፡ እንደ እንስሳት መሞት መበስበስ ግድ ሆነበት፡፡ ፈቃዱን እንደ ፈጸመለት እንደ ዲያብሎስ በነፍስ ወደ ሲዖል መውረድን ተቀበለ፡፡ ይሠዋው የነበረው መሥዋዕትም ሟች፤ ሕይወትን በማያመጣ፤ ሞት የሚያሸንፈው የእንስሳት መሥዋዕት ሆነ፡፡
 
እግዚአብሔርን መምሰልን አጣ
«እኔ ግን አማልክት ናችሁ አልሁ፤ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፡፡ ነገር ግን እንደ ዲያብሎስ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ» መዝ. 81፤6፤ ዮሐ. 1ዐ፤3፡፡ ሰው አምላክ ዘበጸጋ ነበር ነገር ግን እንደዲያብሎስ/ከአለቆች አንዳንድ/ በመውደቁ እግዚአብሔርን የመምሰል ክብር አጣ፡፡
 
ባለ ዕዳ ሆነ
አዳም በባሕርይው ነጻ ሰው ነበር፡፡ አሁን ግን ዕዳን በገዛ እጁ አመጣ፡፡ ሞትን ያህል ዕዳ ተሸከመ፡፡ ደግሞም ዕዳውን መክፈል አልቻለም፡፡
 
ገነትን አጣ

አዳም የነበረችውን ርስት አጥቶ ተባረረ፡፡ ገነት ተዘጋችበት፡፡ ስደተኛም ሆነ፡፡ እግዚአበሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፡፡ ማቴ. 22፤32፡፡ አዳምና ሐዋን ግን ሞትን ተሸከሙ፡፡ ስለዚህም ከሕያዋን አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተቋረጠ፡፡


Written By: host
Date Posted: 12/19/2007
Number of Views: 11146

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement