View in English alphabet 
 | Friday, March 29, 2024 ..:: ክርስቲያናዊ ህይወት ::.. Register  Login
  

የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ

የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት ሲባል ምን ማለት ነው? የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም የከበረ በመሆኑ እንደተገኘ የሚጠሩት፣ እንደአጋጠመ የሚናገሩት አይደለም፡፡ ይልቁንም በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በትሕትና ሆነው ሊጠሩት የሚገባ ክቡር ስም ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም ያለአግባብ በነገራቸው ሁሉ ውስጥ ሲያስገቡት፣ ሥፍራም ጊዜም ሳይመርጡ እንደፈለጉት ሲጠሩት ይስተዋላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች እምነትና ፊሪሃ እግዚአብሔር አላቸው ለማለት አያስደፍርም፤ ምክንያቱም የሚያምኑና

 

ከዚህ ቀጥለን ሰዎች ስሙን በከንቱ የሚጠሩባቸውን ሁኔታዎች ባጭር ባጭሩ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

 

ሀ. መሐላ፡- መሐላ ስመ እግዚአብሔር በከንቱ ከሚጠራባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ የአምልኮ ጣዖትን ከንቱነት ለመግለጥ እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡ በስሙ እንዲምሉ ያዝዝ ነበር (ዘዳ 6&13፤ ኢሳ 45&23)፡፡ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በእግዚአብሔር መማል ብቻ ሳይሆን መሐላ በጠቅላላው የተከለከለ መሆኑን መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ ይህ የሐዲስ ኪዳን ዘመን አረማዊነትና አምልኮ ጣዖት ጠፍቶ ወንጌል የተሰበከበት፣ ክርስትና በዓለም ሁሉ የታወቀበት ነውና መማል አላስፈለገም፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ #ከቶ አትማሉ፤… ቃላችሁ አዎን፣ አዎን ወይም አይደለም፣ አይደለም ይሁን፣ ከዚህም የወጣ ከክፉው ነው$ በማለት መሐላን ከልክሏል (ማቴ 5&34-37)፡፡ ስለሆነም በየሰበቡ የእግዚአብሔርን ስም፣ የቅዱሳንን ስም፣ የመላእክትን ስም ሁሉ እየጠሩ መማል የተከለከለ ነውና ከዚህ መቆጠብ ይገባል፡፡ በተለይም በየአጋጣሚው ስመ እግዚአብሔርን እየጠሩ መማል የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት መሆኑን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡  

 

ለ. የእግዚአብሔርን ስም ማቅለል

ይህም የእግዚአብሔርን ስም በሚገባው ክብር ሳይሆን እንደዋዛ መጥራት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ስም ከስድባቸውና ከእርግማናቸው፣ ከቀልዳቸውና ከጨዋታቸው፣ ከብስጭታቸውና ከኃዘናቸው ጋር አስተባብረው የሚያለሡ ሁሉ በከንቱ እየጠሩት ነው፡፡ በዚህ መልክ ያቃለሉትን ስም በዚያው አንደበታቸው በጸሎት ጊዜ ደግሞ #ስምህ ይቀደስ$ ይሉታል፡፡ ማር ይስሐቅ ስለ ስመ አጠራሩ ሲናገር #የእግዚአብሔርን ስም በሚነድ እሳት ፊት እንደመቆም ሁሉ በሚገባው ክብርና የእግዚአብሔርን ስም በሚነድ እሳት ፊት እንደቆምን ሁሉ በሚገባው ክብርና ልዕልና፤ በመፍራትና በመንቀጥቀጥም ልንጠራው ይገባል$ ብሏል፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔርን ስም መቼ፣ የትና እንዴትም ሆነን ልንጠራው እንደሚገባን ማስተዋል የክርስቲያኖች ሁሉ ግዴታችን ነው፤ እርሱ ስሙን በከንቱ የሚጠራውን አይተወውምና፡፡

 

በርግጥ የእግዚአብሔርን ስም አክብረን ብንጠራው ለእርሱ ክብር የሚጨመርለት ሆኖ አይደለም፤ እርሱ በባሕርዩ የከበረ ስለሆነ የምንከብረው እኛ ነን እንጂ እርሱ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ስም ዕቃ በወደቀባችው፣ ውሻ በጮኸባችው ቁጥር የሚጠሩ ሁሉ እያቃለሉትና በከንቱም እየጠሩት መሆናቸውን በመረዳት ከዚህ መቆጠብ ያሻል፡፡ በዚህ መልክ ስሙን መጥራት ወደ እርሱ ለመቅረባችን ወዳጁም ለመሆናችን ማስረጃ ተደርጎ ተቆጥሮ ከሆነም ስህተት ነው፤ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ማለት የእርሱን ባሕርይና የዚህን ክብር ወደ ማወቅ መድረስና በትሕትና ሆኖ በተገቢው ጊዜ መጥራት እንጂ ስሙን ከክብሩ በመለየት እንደተፀውዖ ስም /ሎቱ ስብሐት / በየአጋጣሚው ሁሉ የመዘንጠል መብት ማግኘት ማለት አይደለም፡፡

 

ስለሆነም አንደበትን ከልማድ በመቆጠብ የእግዚአብሔርን ቸርነቱን ከኃያልነቱ፣ ትሕትናውንም ከባሕርይ ክብሩ ጋር እያነፃፀሩ በማስተዋልና በትሑት ልቡና ሆኖ ስሙን መጥራት ያስፈልጋል፡፡

 

ሐ. እግዚአብሔርን ማማረር

አንዳንድ ሰዎች በተቸገሩና ፈተናም በገጠማቸው ጊዜ እያንጐራጐሩ በእግዚአብሔር ላይ ያመካኛሉ፡፡ እርሱንም ይከሳሉ፡፡ በፊቱ ቆመው ላለመጸለይና ከእርሱም ለመለየት መወሰናቸውን እያወሱ ስሙን ይጠራሉ፡፡ ይህ ሁሉ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ስመ አምላክን በከንቱ መጥራት ነው፡፡ በዚህ መልክና ሁኔታ ግን ክቡር ስሙን እንድንጠራ አልተፈቀደልንም፡፡ በመጽሐፍ እንደተነገረ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ የገሃነም እሳት የሚፈረድበት ከሆነ በእግዚአብሔር ላይ የሚያጉረመርም ደግሞ ምንኛ የባሰ ቅጣት ይጠብቀው ይሆን? (ማቴ 5&22)፡፡ ለክርስቲያኖች በሚሆነው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ከማመስገንና ሥራውን ከማድነቅ በስተቀር ማማረርና ሌሎችም እንዲያማርሩት ምክንያት መሆን አልተፈቀደም፡፡ በዚህም ስሙን በከንቱ ከመጥራት መቆጠብ ይኖርብናል፡፡

 

መ. ኑፋቄ

ይህም የእግዚአብሔርን ክብር በማቃለልና መለኮታዊ ባሕርዩን ካለማወቅ የተነሣ በሚመጣ ትዕቢት ስሙን በከንቱ መጥራት ነው፡፡ ለምሳሌም፡- እንደ አርዮስና የዘመኑ ውሉደ አርዮስ የይሖዋ ምስክሮች ነን ባዮች ክርስቶስን ፍጡር /ሎቱ ስብሐት/ ማለት፣ እንደ መቅዶንዮስና የዘመኑ መቅዶንዮሳውያን መንፈስ ቅዱስን ሕፁፅ /ሎቱ ስብሐት/ ማለት፣ እንደ ሉተርና የዘመኑ ሉተራውያንና መሰሎቻቸው ክርስቶስን አማላጅ /ሎቱ ስብሐት/ ማለት የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ባሕርይ ካለማወቅ፤ ምሥጢረ ሥላሴንም ካለመጠንቀቅ የመጣ ከንቱ አምልኮ ነው፡፡ በዚህ መልክ ስሙን መጥራት በከንቱ ስመ አምላክን ከመጥራት የሚቆጠር ነውና ከዚህ ይሰውረን፡፡

 

ሠ. ጥንቆላና መሰሎቹ

ልብን ለአጋንንት ሰጥቶ፣ ለዲያብሎስ ግብር ገብቶ በሰው ፊት ግን ስሙን በመጥራት ማታለል የዋሁን ሕዝብ ማሞኘት ነው፡፡ በእዚአብሔር ስም የሚፈጸመውም ይህ ኃጢአት ስሙን በከንቱ መጥራት ነው፡፡ በራሳቸው ፍጡራን ወደሆኑትና በአጋንንት እየተገዙ ወደሚኖሩት ወደ ጠንቋዮችና መሰሎቻቸው ሁሉ በመሄድ አንዳች መፍትሔ የሚያገኙ የሚመስላቸው ሁሉ በስመ እግዚአብሔር ከለላ የሚፈጸም የዚህ ኃጢአት ተባባሪዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም በመጽሐፍ #…ሟርተኛም፣ ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ መተተኛም፣ በድግምት የሚጠነቁልም፣ መናፍስትንም የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም፣ ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው$ እንደተባለ እያስታወስን በዚህ ተሳትፈን ስመ አምላክን በከንቱ ከመጥራት ልንቆጠብ ይገባል (ዘዳ 18&9-12)፡፡

 

ረ. ማስታወቂያዎች

ብዙ ሰዎች በተለይ በከተማዎች አካባቢ ሱቆቻቸውን፣ ድርጅቶቻቸውንና የንግድ ቤቶቻቸውን በእግዚአብሔር ስም ይሰይማሉ፡፡ ምናልባት ይህን ማድረጋቸው #የእግዚአብሔር ወዳጆች መሆናቸውን$ ለማሳወቅ ወይም ደግሞ በንግዱ ብዙ ትርፍ እንዲያገኙ በማሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሥራቸውን እንዲባርክላቸው ከመጸለይ በስተቀር በዚህ መንገድ ለመጠቀም መፈለጋቸው ትክክል ካለመሆኑም በላይ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት ነው፡፡

 

ለምሳሌ መድኃኔዓለም ሥጋ ቤት፣ መድኃኔዓለም ጠጅ ቤት ክርስቶስ ብረታ ብረት፣ አልፋና ዖሜጋ የቁንጅና ሳሎን፣ ወዘተ… የሚሉትን መመልከት ይቻላል፡፡ በአብዛኛው ማስታወቂያው መንፈሳዊ ሁኖ በውስጥ የሚሠራው ሥራ ግን ሌላ ነው፡፡ እንግዲህ ክርስቲያኖች ሁሉ ክርስትናችን በልቡና እምነትና በምግባር የሚገለጥ ሊሆን ከሚገባው በቀር በዚህ ዓይነት ተግባር እንዳይሆን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄደው ደግሞ የክርስቶስን ስም በተለያዩ አልባሳት ላይ በመጻፍና በማተም ለማስታወቂያ መጠቀም የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ ከመጥራት ጋር የሚደመር ነው፡፡

 

ሰ. መጠሪያ ስም

አንዳንዶች ደግሞ የልጆቻቸውን ስም የሚሰይሙት ባለማስተዋልና በግድ የለሽነት ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ስም ሊጠራ አይገባውም፣ የእግዚአብሔር ስም የእርሱ ብቻ ነውና፡፡ ነገር ግን የልጆቻቸውን ስም ለምሳሌ አማኑኤል፣ ኤልሻዳይ፣ አዶናይ፣ ኢየሱስ ወዘተ… በማለት የሚሰይሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ እየጠሩ ናቸው፡፡ #አማኑኤል$ ማለት የወልደ እግዚአብሔር የተዋሕዶ ስሙ ነው፣ #እግዚአብሔር ከእኛ ጋር›› ማለት ነው፡፡ የሚገልጠውም እግዚአብሔር ሰው የመሆኑን ምሥጢር ነው፡፡ ታዲያ ይህ ስም ልንጠራበት ይገባናል? #ኤልሻዳይ$ ማለት ‹‹ሁሉን ማድረግ የሚችል›› ማለት ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ከሐሊነት የሚያመለክት ነው፡፡ ማነው #ከሐሌ ኩሉ$ በዚህ ስም ሊጠራ የሚደፍር? ማንም ከቶ ሊኖር አይገባም፡፡ አዶናይም እንዲሁ፡፡ ወልደ አማኑኤል (የአማኑኤል ልጅ)፣ ገብረ ኢየሱስ (የኢየሱስ አገልጋይ)፣ ገብረ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር አገልጋይ) እያሉ መሰየም ግን ስመ ክርስትና በመሆኑ ተገቢና የሚደገፍም ጭምር ነው፡፡ እንግዲህ በስማችን ኃጢአት እንዳንሠራ፣ የእግዚአብሔርንም ስም በከንቱ እንዳንጠራ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡

 

ቀ. ፍልስፍናና ሥነ ጽሑፍ

አንዳንድ ፈላስፎች ነን ለማለት የሚቃጣቸው ሰዎች ‹‹ዐውቀን ተጠበብን›› የሚሉበትን ፍልስፍናቸውን ተደማጭና ተቀባይነት ያለው ለማድረግ፣ የሰሚን ወይም የአንባቢን ቀልብ ለመሳብ ሲሹ #እግዚአብሔርም እንዲህ ብሏል$ እያሉ የእርሱን ሕያው ትምህርት ምውት ለሆነ ፍልስፍናቸው ይጠቀሙበታል፡፡ ይህንኑ ፈሊጥ ብለውት በተራ ዲስኩራቸውና የፖለቲካ መነባንባንባቸው እንደቀልድ ስመ እግዚአብሔርን የሚጠሩ፣ የእርሱንም ቃል የሚጠቅሱ ሰዎችም በየሬድዮው ይናገራሉ፡፡ በየጋዜጣው ይጽፋሉ፡፡ እነዚህም ሁሉ ስመ እግዚአብሔርን በከንቱ እየጠሩ ናቸው፡፡

 

በሥነ ጽሑፍ ዓለም የምናውቃቸው አንዳንድ ደራሲያንና ገጣሚያንም የሚጽፏቸው ድርሰቶችና ሥነ ጽሑፎች ጆሮ ገብና ተነባቢ እንዲሆንላቸው ከሚያውቋቸው መጻሕፍት የተቆነፃፀሉ ጥቅሶችን ከቃለ እግዚአብሔር ይጠቅሳሉ፣ ስመ እግዚአብሔርንም ለማሾፊያና ለመሳለቂያ ሲጠቀሙበት ይስተዋላሉ፡፡ ይህም ሁሉ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት ነውና ሳያስጠይቅ አይቀርም፡፡ በራሱ ባሕርያዊ ውበትና ማራኪነት የሌለውን ደረቅና ባዶ ጽሑፍ በቃለ እግዚአብሔርና በስሙም ለማጣፈጥና ለማስዋብ መሞከር ስመ እግዚአብሔርን በከንቱ ከመጥራት የሚመደብ ነውና፡፡

 

የእግዚአብሔር ስም በከንቱ መጥራት ቅጣት አለው

ሰማይ ዙፋኑ፣ ምድርም የእግሩ መረገጫ በመሆናቸው በሰማይም፣ በምድርም እንዳንምል የታዘዝን ከሆነ በእግዚአብሔር ስም መማል ደግሞ የበለጠ በመሆኑ የማይገባና ቅጣትም የሚያስከትል ነው፡፡ በፍጥረቱ እንዳይምል የተከለከለ ሆኖ ሳለ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ስም የሚምል ሰው የሚቀጣ መሆኑን መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ #የእግዚአብሔርንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል$ በሚለው ምንባብ እንደተገለጠው ክብር ምሥጋና የሚገባውን ቅዱስ ስም በማይገባ ሥፍራ መጥራትና ልዕልናውን ዝቅ ማድረግ ስሙን በከንቱ መጥራትና እንደስድብም የሚቆጠር ነው፡፡

 

በነቢዩ በሕዝቅኤል #እግዚአብሔር ስለ ቅዱስ ስሙ ይቀናል$ የተባለውም የፈጣሪአችንን ስሙ በከንቱ እንዳንጠራ የሚያስተምር ነው (ሕዝ 39&25)፡፡ እግዚአብሔርም #ወደመጡባቸውም ወደ አሕዛብ በመጡ ጊዜ ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ እኔ ግን የእሥራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስለአረከሱት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ስለራራሁላቸው፤…በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም$ በማለት ስለ እሥራኤል ልጆች የተናገረው ለዚህ ነው (ሕዝ 36&20)፡፡ የእግዚአብሔርን ስም ማርከስ ማለትም ሊሰጠው የሚገባውን ክብር መንሳትና ማቃለል ነው፡፡ ከዚህ መራቅና ስሙን በከንቱ ጠርቶ ከመከሰስ ለመዳን ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በነቢዩ በዘካርያስም #በሐሰት የሚምል ሁሉ ይጠፋል፣… እኔ አስወጣዋለሁ$ ያለው የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ የሚጠሩ ሁሉ የሚቀጡ፤ ቅጣቱም ከገጸ ምድር የሚያጠፋ መሆኑን የሚያስረዳ ነው (ዘካ 5&3)፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ እኛ ይህን ስም እንዴት እንደምንጠራው ራሳችንን ልንመረምርና የእግዚአብሔርን ስም በተገቢው ክብር መጥራትን ልንለምድ ያስፈልጋል፡፡

 

ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር #ለስሜ ክብርን ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፤ በልባችሁም ባታደርጉት ይላል ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ርግማን እሰድድባችኋለሁ፣ በረከታችሁንም እረግማታለሁ$ በማለት አስጠንቅቋል (ሚል 2&2)፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ስም ክቡርና ገናና በመሆኑ በከንቱ የሚጠራውን ሰው እግዚአብሔር እንደሚቀጣው የሚያመለክት ነው፡፡ ስለዚህ ስሙን በማክበር የሚገኘውን በረከት እንዳናጣና እንዳንጠፋም፤ በጊዜው ሁሉ የእርሱን ስም በማክበር እንኑር፡፡ በዚህ ጸንተን ክብሩን ለመውረስ እንዲያበቃን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን

ወለእግዚአብሔር ስብሐት

Written By: host
Date Posted: 5/18/2008
Number of Views: 19608

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement