View in English alphabet 
 | Thursday, April 18, 2024 ..:: ክርስቲያናዊ ህይወት ::.. Register  Login
  

ንስሐ

ንስሐ የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ጸጸት ነው፡፡ ጸጸትነቱ ሰው በሠራው ኃጢአት ተጸጽቶ ኃጢአቱ ይሰረይለት ዘንድ እግዚአብሔርን በሐዘን በለቅሶ ሲለምን እንጂ የጐልማሳ ሚስት ሳልቀማ፣ የሰው ገንዘብ ሳልሰርቅ ቀረሁ … በማለት የሚጸጸተው ጸጸት አይደለም፡፡

ንስሐ ለተጠመቁ ሰዎች ከጥምቀት በኋላ የተሰጠች ሀብት ናት። በጥምቀት ከእግዚአብሔር የምትገኝ የልጅነት ሁለተኛ ማዕረግ ናት፡፡ በሃይማኖት ገንዘብ ያደረግነው የመንግሥተ ሰማያት አራቦን ማለትም መግዣ ናት። ንስሐ ለሚሿት ሰዎች የተከፈተች የይቅርታ በር ናት፡፡ በንስሐ በርነት ከፈጣሪ ወደሚገኝ ቸርነት እንቀርባለን።

ምሥጢረ ንስሐ ማለት አንድ ሰው ከጥምቀት በኋላ የፈጸመውን ጥፋት አውቆ ሁለተኛ ጥፋቱን ላለመድገም ወስኖ በእግዚአብሔርና በካህኑ ፊት ተንበርክኮ ከልቡ ተጸጽቶ ኃጢአቱን በመናዘዝ ከኃጢአቱ እስራት የሚፈታበትና ከእግዚአብሔር ይቅርታን የሚያገኝበት ታላቅ የይቅርታ ምሥጢር ነው።


የምሥጢረ ንስሐ አመሠራረት


ምሥጢረ ንስሐን የመሠረተ ራሱ ጌታችን ነው። ለሰው ልጆች አዛኝ የሆነው መፍቀሬ ሰብ ክርስቶስ የኛን ኃጢአት ሁሉ በሰውነቱ ተሸክሞ በሕማምና በሞቱ አንድ ጊዜ አድኖናል። ይህንንም ጸጋ በምሥጢረ ጥምቀት አግኝተነዋል። ከዚህ በኋላ ለምንፈጽመው በደል ማስተስረያ እንዲሆነን ለሐዋርያትና እነሱን ለሚከተሉት ካህናት ሥልጣንን በመስጠት ምሥጢረ ንስሐን መሥርቶልናል። ኃጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን የእግዚአብሔር ብቻ ሲሆን ለእኛ ጥቅምና ደህንነት ሲል ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለጴጥሮስና ለሐዋርያት ተከታዮች ሰጥቷል። ቅዱስ ጴጥሮስ ስለእውነተኛ እምነቱ ከመሰከረ በኋላ ሥልጣነ ክህነትን ማለትም የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፍ ክርስቶስ ሰጥቶታል። እንዲህም ብሎታል «የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል» /ማቴ. ፲፮፥፲፱/።

እንደዚሁም ይህን ሥልጣን ለሌሎች ሐዋርያትም ሰጥቷቸዋል። /ማቴ ፲፰፥፲፰/። ከትንሣኤው በኋላም ለሦስተኛ ጊዜ ኃጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። «አብ እኔን እንደላከኝ እኔም ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።» /ዮሐ. ፳፥፳፩-፳፫/። ስለዚህ ኃጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን ለነሱ የተሰጠ ስለሆነ በሐዋርያት እግር ለተተኩ ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት ኃጢአትን መናዘዝ ይገባል።


ንስሐ በሦስት ነገሮች ይፈጸማል

እንግዲህ ንስሐ ገብተን፣ የኃጢአትን ስርየት አግኝተን፣ ከሰውና ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን በጽድቅ ጎዳና ለመራመድና በደህንነት ጸጋ ለመኖር እንድንችል ቢያንስ ሦስት ነገሮችን መፈጸም አለብን። የመጀመሪያው የንስሐ ሃዘን ማለትም እውነተኛና ልባዊ ጸጸት በቅድሚያ እንዲኖረን ያስፈልጋል። ሁለተኛው ኑዛዜ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ስለኃጢአታችን የሚሰጠንን የንስሐ ቅጣት የሚያመለክት የቀኖናን ሥርዓት መፈጸምና እንደዚሁም በካህኑ በኩል የምናገኘው የፍትሐት ጸጋ ነው።


የንስሐ ሃዘን /ጸጸት/

ንስሐ የሚገባ ሰው በመጀመሪያ ኃጢአቱን እያስታወሰ ሰውና ፈጣሪውን መበደሉን እያሰበ የሚያደርገው ሃዘን ወደ ንስሐ የሚወስድ እውነተኛ ሃዘን ስለሆነ ሃዘኑን እግዚአብሔር ይቆጥርለታል። «የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና» /ማቴ. ፭፥፬/ የተባለው የራሳቸውንና የሌላውን ኃጢአት እያሰቡ የሚያዝኑትን ተነሳሒያን ያመለክታል። ንስሐ ማለት ጸጸትን የሚያመለክት ቢሆንም ቁጭትና ቅንዓት የሞላበት የዓለማዊ ጸጸት ሳይሆን እውነተኛው ሃዘንና መመለስ መሆኑን በቅድሚያ መገንዘብ ይኖርብናል።

ስለእውነተኛው ሃዘን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚከተለው ያስተምረናል። «አሁን ስለንስሐ ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም፤ በምንም ከእኛ የተነሳ እንዳትጎዱ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና። እንደእግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሃዘን ጸጸት የሌለበትን፣ ወደ መዳንን የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ሃዘን ግን ሞትን ያመጣል።» /፪ኛ ቆሮ. ፯፥፱-፲/። እንግዲህ እውነተኛውን ሃዘን ከእንባ ጋር አድርጎ በንጹህ ልቦናና ጸሎት ለእግዚአብሔር በማቅረብ ተነሳሒው እንደገና ላለመበደል መወሰን ይኖርበታል። ውሳኔውንም ለመፈጸም የሚያስችለውን የመንፈስ ቅዱስን ረድኤት በማግኘት ሁልጊዜ ተግቶ መጸለይ አለበት።


ኑዛዜ

ከዚህ ቀጥሎ ተነሳሒው ኃጢአቱን ሥልጣነ ክህነት ላለው ካህን ይናዘዛል። ኑዛዜ ማድረግ በቅዱሳት መጻሕፍት የታዘዘ ነው። «ከነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ቢሆን፥ የሠራውን ኃጢአት ይናዘዛል። ስለሠራው ኃጢአት ለእግዚአብሔር የበደልን መስዋዕት ያመጣል፤ … ካህኑ ስለኃጢአቱ ያስተሰርይለታል። … እርሱም ይቅር ይባላል።» /ዘሌ. ፭፥፭-፮፣፲/። ከዚህ ጥቅስ የኃጢአትን ስርየት ለማግኘት ለካህን መናዘዝ እንደሚገባ እንማራለን። ስለዚህ ኃጢአታችንን ለአናዛዡ ካህን ከበደሉ ዓይነትና ሁኔታ ጋር ማስረዳት ይገባናል። ስንናዘዝም ከእንባና ከጸጸት ጋር ሆነን ከካህኑ ጋር አብሮ እግዚአብሔር እንደሚሰማን አምነን በእውነት መናገር ያስፈልገናል። በሽታውን የሰወረ መድኃኒት አያገኝም ተብሏልና ለነፍስ ቁስል ሐኪም ለሆነው ለካህኑ ኃጢአታችንን ከሰወርን ለነፍስ የሚሆነውን ፈውስ ለማግኘት አንችልም።

«ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።» /ምሳ. ፳፰፥፲፫/ ተብሎ ተጽፏልና ስለዚህ እርስ በርሳችን በቂም በቀል ሳንያያዝ የበደልነውን እየካስን፣ የበደለንን ይቅር እያልን ብንናዘዝና የሰማዩን አባታችን በጸሎት ብንጠይቀው ምሕረትና ፈውስን ይሰጠናል። ነገር ግን እኛ ማንንም አልበደልንም ኃጢአትም የለብንም ብንል እግዚአብሔርን ሐሰተኛ ማድረጋችን ስለሆነ እንጠንቀቅ። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዳለው «ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በኛ ውስጥ የለም።» /፩ኛ ዮሐ. ፩፥፰-፲/።


ፍትሐትና ቀኖና

እንግዲህ ተነሳሒው በእውነት ኃጢአቱን አውቆ ለካህኑና በስውር ለሚያየውና ለሚሰማው ለእግዚአብሔር ከተናዘዘ በኋላ ከካህኑ ሁለት ነገሮችን ይቀበላል። እነሱም ፍትሐትና ቀኖና ናቸው። ፍትሐት ማለት ከኃጢአት እስራት የሚፈታበት ነው። ቀኖና ማለት ለኃጢአቱ ምክርና ተግሳጽ የሚያገኝበትን፣ በንስሐ ቅጣት የሚቀበልበትን፣ ካሳ መቀጫ የሚከፍልበትን ሁኔታ የሚያመለክት ነው። ፍትሐት የሚሰጠው ካህኑ የንስሐውን ጸሎት ሥነ ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ «እግዚአብሔር ይፍታህ» ሲል ተናዛዡ ወይም ተነሳሒው ከኃጢአቱ እስራት ይፈታል። ከእግዚአብሔርም ይቅርታን ያገኛል። ንስሐ የገባው ሰው ከኃጢአቱ ተፈትቶ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቁ ታላቅ ጸጋ ነው።

ለኃጢአታችን ስርየት እንደዚህ ዓይነቱን ቀላል መንገድ ስላዘጋጅልን ክርስቶስን ማመስገን ይገባናል። ብዙ ሳንደክም ወንድማችንና አባታችን ለሆነው ካህን በመናዘዝና ምክሩንና ቀኖናውን በመቀበል በኃጢአት ከሚመጣብን የዘላለም ቅጣት መዳናችን እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው። ይህንንም ሥልጣን ለካህናት የሰጣቸው እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከላይ ተገልጿል። እንግዲህ ፍትሐት የተቀበለ ተነሳሒ ሁሉ ኃጢአቱ የተሰረየለት ስለሆነ ከዘላለም የሞት ቅጣት ነፃ ይሆናል።

ምንም እንኳን ተነሳሒው ከዘላለም የሞት ቅጣት ቢድንም ዓይነቱና መጠኑ የተለያየ ጊዜያዊ ቅጣት መቀበል ይገባዋል። ይህም የንስሐ ቀኖና ይባላል። ጊዜያዊ ቅጣት ወይም ቀኖና ያስፈለገበት ምክንያት ኃጢአትን መሥራት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ለተነሳሒው ለማሳሰብና ዳግመኛ እንዳይበድል ለማስጠንቀቅ እንዲሁም ደግሞ ሥጋን በመገሰጽ ለነፍሱ የጽድቅንና የደህንነትን ጎዳና ለማስተማር ነው።

ምንጊዜም ፍቅሩና ምሕረቱ ከኛ ጋር ቢሆንም እግዚአብሔር በአባትነቱ ላጠፋነው ጥፋት በጊዜያዊ ቅጣት ይቀጣናል። መልካም አባት ልጁን እንደሚገስጽና እንደሚቀጣ ዓይነት ይቀጣናል። /ዕብ. ፲፪፥፭-፲፩/። እንግዲህ ያልተገራ ልቦና ካለን ለእግዚአብሔር በማስገዛት የኃጢአታችንንም ቅጣት በደስታ በመቀበል የበለጠ ጸጋና ረድኤትን እናገኛለን። «በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፣ የኃጢአታቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ እኔ ለያዕቆብ የማልኩትን ቃልኪዳኔን አስባለሁ … ምድሪቱንም አስባለሁ።» ተብሎ ተጽፏልና /ዘሌ. ፳፮፥፵፩-፵፪/።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዝሙት የተከሰሰውን የቆሮንቶሱን ሰው በሥጋው እንዲቀጠፍ ፈርዶበታል። «እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ … መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ሰው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።» /፩ኛ ቆሮ. ፭፥፩-፭/። ይኸው ሐዋርያ ለሁለተኛ ጊዜ በጻፈው መልእክቱ ከላይ የተጠቀሰው የቆሮንቶስ ሰው ቅጣቱ የሚበቃው ስለሆነ ማኅበረ ክርስቲያኑ ይቅርታ እንዲያደርጉለት ጠይቋል።

«እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ሃዘን እንዳይዋጥ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። ስለዚህ ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና፤ … » /፪ኛ ቆሮ. ፪፥፮-፲፩/። እንግዲህ የሐዋርያውን ምክር ሰምተን ዛሬ የምንገኘው ክርስቲያኖችን በበደላችን ምክንያት ካህኑ የሚሰጠንን ምክርና ተግሳጽ አዳምጠን የንስሐውንም ቅጣት ማለትም ቀኖናውን ተቀብለን በደስታ ብንፈጽመው መንፈሳዊ ደህንነታችን ይጠበቃል። መንፈሳዊ ግዴታችንንም እንወጣለን።

በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና የሚሰጠው እንደተነሳሒው የኃጢአት ዓይነትና ሁኔታ ታይቶ ነው።  ካህኑ የተነሳሒውን የኑሮ ሁኔታና ያጋጠመውን ፈተና በማስመልከት ምክርና ትምህርት ይሰጠዋል። እንደመልካም የነፍስ ሐኪምም እንደበሽታው ሁኔታ ካህኑ አስፈላጊውን የነፍስ መድኃኒት ይሰጠዋል። የቀኖና አሰጣጥ መንገዱና ዓይነቱ ብዙ ነው። ለአንዳንዱ ተነሳሒ የቃል ምክርና ተግሳጽ ብቻ የሚበቃው አለ። ለሌላው ጾም ብቻ ወይም ከስግደት ጋር ቀኖና ይሰጠዋል። ልዩ የንስሐ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ለተበደለው ወገን ካሳ መክፈል፣ ለችግረኞች አገልግሎት መስጠት አስፈላጊም ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከቁርባን መለየት ወይም ልዩ ልዩ አስቸጋሪ ነገሮችን መፈጸም ወይም ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኑሮ የሚጠቅሙ የጉልበትም ሆነ የአዕምሮ ሥራ መሥራትና የመሳሰሉት ሁሉ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይቆጠራሉ።

እንግዲህ የሚሰጠንን ቀኖና ሁሉ በደስታ ተቀብለን ብንፈጽመው ለነፍሳችንም ሆነ ለሥጋችንም የሚጠቅም ጸጋና በረከትን እናገኛለን። እንዲያውም «ሞት የማይገባውን ኃጢአት» ያደረጉትን ዘመዶቻችንና ባልንጀሮቻችን ሁሉ እያሰብን፣ በጸሎት እየማለድን እነርሱም ንስሐ እንዲገቡ እየመከርን በገዛ ፈቃዳችን ካህኑ ለራሳችን ከሰጠን ቀኖና በመጨመር ብንፈጽመው በኃጢአት ለተጎዱት እህቶችና ወንድሞች የእግዚአብሔርን ምሕረት እንደሚያስገኝላቸው አያጠራጥርም። እንደዚህ አድርጎ ስለባልንጀራው ደህንነት እግዚአብሔርን ለሚለምን ሰው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዳለው «ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉ ሕይወትን ይሰጥለታል» /፩ኛ ዮሐ. ፭፥፲፮/።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን


ምንጭ፦ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት በሊቀ ጉባዔ አባ አበራ በቀለ

Written By: admin
Date Posted: 12/3/2011
Number of Views: 12907

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement