View in English alphabet 
 | Friday, March 29, 2024 ..:: ክርስቲያናዊ ህይወት ::.. Register  Login
  

ምሥጢረ ቁርባን /ክፍል አንድ/

ምሥጢረ ቁርባን ማለት ክርስቶስ ስለ እኛ ኃጢአት በመስቀል ላይ መሥዋዕት ሆኖ በሥጋው በመሞቱ የዓለምን ኃጢአት ያስወገደበት፣ የዘላለም ሕይወትን ያሰገኘበት፣ የመዳናችን መሠረት፣ የጸጋችን ሁሉ ምንጭ የሆነውን የቅዱስ ሥጋውንና የክቡር ደሙን የማዳን ጸጋ የሚያመለክት ታላቅ የክርስትና ሃይማኖት ምሥጢር ነው። ክርስቶስ እንደ መሥዋዕትም እንደ ዐቢይ ሊቀ ካህናትም በመሆን ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ፈጽሟል (ዕብ ፯፣፳፡፳፰)። እንደ ዐቢይ ሊቀ ካህናትነቱ በመስቀል ላይ የተቆረሰው ሥጋውን የፈሰሰው ደሙን የኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር በማቅረቡ ሰውን ከራሱና ከእግዚአብሔር ጋር አስታራቀ፣ የጥልንም ግድግዳ አፈረሰ፣ የተራራቀውን አቀራረበ።

ይህም ነገር የቁርባንን የምሥጢር ትርጉም ያስረዳናል። ቁርባን ማለት በአንድ በኩል ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበትን፣ የምንቀራረብበትንና የምንዋሐድበትን ሁኔታ ያሳየናል። ልንቀርብና የመለኮታዊውንም ጸጋ ተሳታፊ ልንሆን የምንችለው በምሥጢረ ቁርባን አማካኝነት ኅብስቱና ወይኑ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም ተለውጦ ስንቀበለው ነውና ምሥጢር መሆኑን ከዚህ ላይ እናስተውላለን።

“ቁርባን” የሚለው ቃል መሠረቱ ከዕብራይስጥ ቋንቋ የመጣ ሲሆን የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም “ስጦታ” ማለት ነው። ይህም ማለት እንደ ኦሪቱ ቁርባን ሰው ለእግዚአብሔር ያቀረበውን ስጦታ ብቻ የሚያመለክት ሳይሆን እግዚአብሔርም በተለየ ሁኔታ ለሰዎች ደኅንነት ለዓለም ሁሉ የሰጠውን በሥጋና በደም የመጣውን የልጁን ስጦታ ያስገነዝባል። ስለዚህም ለዓለም መድኃኒት ሆኖ የተሰጠው በጸሎተ ኀሙስ ማታ ወደ ጌታ ሥጋና ደም የተለወጠው ኅብስትና ወይን ዛሬም በጸሎተ ቅዳሴ የጌታን ሥጋና ደም ሆኖ የሚቀርበው ቅዱስ ቁርባን ይባላል። እርሱም ከእግዚአብሔር የተሰጠ የተቀደሰ ስጦታና መሥዋዕት ነው። እንግዲህ ለኃጢአታችን መሥዋዕት ሆኖ ከእግዚአብሔር የተሰጠንን እኛ ደግሞ ከምስጋና ጋር መልሰን ለእርሱ እናቀርባለን።


ቅዱስ ቁርባን በምሳሌና በትንቢት

በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ ለሥጋውና ለደሙ ማለት ለምሥጢረ ቁርባን የተመሰሉ ምሳሌዎች አሉ። በጠቅላላ የኦሪት መሥዋዕት ሁሉ ለወንጌሉ መሥዋዕት ምሳሌነት ቢኖራቸውም ዋና ዋናዎቹን ብቻ እንጠቅሳለን። መጀመሪያ የልዑል እግዚአብሔር ካህንና የሳሌም ንጉሥ ያቀረበው የኅብስትና የወይን መሥዋዕት ለክርስቶስ ዘላለማዊ ሊቀ ካህናትነትና ለሥጋው ወደሙ ዓይነተኛ ምሳሌ ሆኖ ይነገራል (ዘፍ ፲፬፤፲፰ ዕብ ፭፣፮ እና ፲፣፯፥፲፯)። ሁለተኛው ከቀሳፊ የሞት መልአክ አድኖ ከግብጽ ባርነት ነፃ ያወጣቸው የፋሲካ በግ ደም መረጨትና ሥጋውም ተጠብሶ መበላቱ የእግዚአብሔር በግ ለተባለው ለክርስቶስ አዳኝነትና ለምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ ሆኗል (ዘፀ ፲፪፤፩፡፶፩ ፩ኛ ቆሮ ፭፣፯)። ሦስተኛው እሥራኤላውያን በምድረ በዳ ይመገቡት የነበረው ከሰማይ የወረደው መና ዛሬ ምእመናን ለነፍሳቸው ምግብ የሚቀበሉት የሥጋውና የደሙ ምሳሌ ነው(ዘፀ ፲፮፣፲፮፥፳፫ ዮሐ ፮፣፵፱፥፶፩)። አራተኛው ጥበብ ያዘጋጀችው ማዕድ፣ ያረደችው ፍሪዳ፣ የጠመቀችው የወይን ጠጅ፣ የላከቻቸው አገልጋዮቿ የተጠሩት ሰዎች ሁሉ ምሳሌነት እንዳላቸው ይነገራል። ጥበብ የክርስቶስ፣ ማዕድ የሥጋው የደሙ፣ አገልጋዮች የካህናት፣ ተጋባዦች የምእመናን ምሳሌ ናቸው ተብሎ ይተረጎማል (ምሳ ፱፤፩፥፭)። ይህን የመሳሰሉ ሌሎች ምሳሌዎችም አሉ (ዘሌዋ ፪፤ ፳፫፣፲፫፥፲፬ ሲራክ ፳፬፣፲፱፥፳፩)።

ትንቢትም ስለ እውነተኛው ቁርባን ተነግሯል። “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፤ በየሥፍራውም ለስሜ እጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቁርባን ያቀርባሉ” (ሚል ፩፣፲፩)። ይህ ስለ ወንጌል መሥዋዕት የተነገረ እንጂ ስለ ኦሪት መሥዋዕት አይደለም። ምክንያቱም የኦሪት መሥዋዕት በኢየሩሳሌም ከተማ በቤተመቅደስ ብቻ እንጂ በሌላ ቦታ እንዳይፈጸም በሕግ የተከለከለ ነው። እንግዲህ ነቢዩ ሚልክያስ ንጹሕ ቁርባን ያለው እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ለአሕዛብ ወንጌል በተሰበከበት ሥፍራ ቤተ ክርስቲያን በተቋቋመበት ቦታ ሁሉ የሥጋውና የደሙ ንጹሕ መሥዋዕት መቅረቡን የሚያመለክት ነው። ሌላው ደግሞ የኢሳይያስ ትንቢት ነው። “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፣ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ በረከትንም ብሉ” (ኢሳ ፶፭፣፩፥፪)። ይህ የነቢዩ ቃል በመብልና በመጠጥ ስለሚመጣው ስለ ምሥጢረ ቁርባን በትንቢትና በምሳሌ እንደ ተነገረ ይታመናል።

ምንጭ፦ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት
/ሊቀጉባኤ አባ አበራ በቀለ/
ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ

ይቀጥላል

Written By: admin
Date Posted: 11/17/2013
Number of Views: 10565

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement