View in English alphabet 
 | Friday, March 29, 2024 ..:: ክርስቲያናዊ ህይወት ::.. Register  Login
  

ምሥጢረ ቁርባን /ክፍል ሁለት/

የምሥጢረ ቁርባን አመሠራረት
ምሥጢረ ቁርባንን ጌታችን ከሕማማቱና ከሞቱ በፊት በዋዜማው ኀሙስ ማታ መሥርቷል። ይህም ሰዓት በአይሁድ የቀን አቆጣጠር ወደ ዓርብ ይታሰባል። በዚያም ወቅት የኦሪት የፋሲካ በግ የሚሠዋበት ጊዜ በመሆኑ ጌታችን ከደቀመዛሙርቱ ጋር የኦሪትን መሥዋዕት አሳልፎ መሥዋዕተ ወንጌልን መሥርቷል። በዚያችም ምሽት የኦሪቱን በግ መሥዋዕትነት አበቃ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እውነተኛው የእግዚአብሔር በግ ይሠዋል። እርሱም የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው። ስለዚህ በማዕዱ ዙሪያ ለተሰበሰቡት ሐዋርያቱ በብሉይ ኪዳን ምሳሌ የተመሰለለትን: ትንቢት የተነገረለትን አዲሱን ቃል ኪዳን ጌታ በራሱ ሥጋና ደም መሠረተ። የእውነተኛው መሥዋዕት ምሳሌ የሆነው የኦሪቱን ማዕድ እየበሉ ሳለ “ኢየሱስ እንጀራና ኅብስትን አንስቶ ባረከ ቆርሶ ለደቀመዛሙርቱ ሰጠና እንካቹ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” በማለት ምሥጢረ ቁርባንን መሠረተ /ማቴ ፳፮፣፳፮-፳፰/። ኪዳን ማለት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገባው ቃል ኪዳን የሚያመለክት ነው።

በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት ከቤተ እሥራኤል ጋር ቃል ኪዳን የገባው በእንሰሳት ደም ነበር /ዘፀ ፳፬፣፩-፲፩/። ያን ጊዜ ቤተ እሥራኤል ቃል የገቡት ሕገ ኦሪትን ሊፈጽሙ አሠርቱ ትእዛዛትን ሊጠብቁ ሥርዓቱን ሊያከብሩ ነበር። እግዚአብሔር ደግሞ በበኩሉ አምላካቸውና ጠባቂያቸው ሊሆን፣ ምድረ ርስትንም ሊያወርሳቸው ተሰፋ ሰጣቸው፣ ቃል ገባላቸው። በወንጌል ግን እግዚአብሔር ቃል ኪዳን የገባው በልጁ ደም ነው። እግዚአብሔርም የፈጸመልን አዲሱ ኪዳን ከብሉይ ኪዳን እጅግ የላቀ ነው። ምክንያቱም በክርስቶስ የሐዲስ ኪዳን ደም ኃጢአታችን ተወግዶልናል፤ ከእግዚአብሔር ታርቀናል፤ የእግዚአብሔርን ልጅነት አግኝተናል፤ እግዚአብሔርም አባት ሆኖን የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን አብቅቶናል። ስለዚህ ይህን ወሰን የሌለው እስከ ሞት ድረስ የወደደንን የክርስቶስን ፍቅር እያሰብን እግዚአብሔርን በልጁ ስም ዘወትር ለማመስገን፣ ወንድሞቻችንንም ለማፍቀርና ችግረኞችንም ለመርዳት የወንጌልንም ትእዛዝ ለመፈጸም እኛም በበኩላችን ቃል መግባት ይኖርብናል።

ቃል ኪዳን ከገባንበት ዋናው ነገር በቆረብንና ቅዳሴ ባስቀደስን ቁጥር የበደላችንንና የኃጢአታችንን ሥርየት ያገኘንበትን፣ ከእግዚአብሔር የታረቅንበትን የክርስቶስን ሕማምና ሞት ማሰብና ማስታወስ ነው። ስለዚህ ነው ጌታችን ኅብስቱን አንስቶ ባርኮና ቆርሶ ለሐዋርያቱ ከሰጣቸው በኋላ  “ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ያላቸው /ሉቃ ፳፪፣፲፱/። መታሰቢያዬ የተባለው ስለ ሕማምና ሞቱ መሆኑንና ይህንንም የሞቱን ዜና የመስቀሉን ነገር ጌታ እስኪመጣ ድረስ በምሥጢረ ቁርባን አማካኝነት እንደሚነገር ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎሰ እንማራለን /፩ኛ ቆሮ ፲፩፣፳፫፡፳፮/። ዛሬም በጸሎተ ቅዳሴ “ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ” የተባለውን እያዜምን እናስታውሰዋለን። በምንቆርብበትም ጊዜ የምናየው የተፈጥሮ ኅብስትና ወይን ብቻ መስሎን እንዳንሳሳት የማይታየው መለኮት የተዋሐደው የጌታ ሥጋና ደም መሆኑን አምነን መቀበል አለብን። አለበለዚያ በራሳችን ላይ ፍርድን እናመጣለን። ሳይገባው ራሱን ሳይፈትን ሳይመረምር የሚቆርብ ፣የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፣ በማለት ይኸው ሐዋርያ ያስጠነቅቀናል።

“ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ ኅብስት የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፣ እንዲሁም ከእንጀራው ከኅብስቱ ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፣ ይጠጣልምና። ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል። ራሳችንን ብንመረመር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን” /፩ኛ ቆሮ ፲፩፣፳፯-፴፪/።


ምንጭ፦ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት
/ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ/
ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ

ይቀጥላል

Written By: admin
Date Posted: 1/26/2014
Number of Views: 9677

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement