View in English alphabet 
 | Thursday, March 28, 2024 ..:: ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ::.. Register  Login
  

-

የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዴት ይሾማሉ?

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካህናት አባቶችን ለአገልግሎት የምትሾምበት ሰማያዊ ሥርዓት አላት፡፡ እነዚህን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማብራራት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡

ጠቅለል ባለ መልኩ ግን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚሾሙ አባቶች መንጋውን ለመጠበቅ፣ ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለመስጠት፣ ለመለየት፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ፊት ቃል ይገባሉ፡፡ ቃል ኪዳናቸውም በእግዚአብሔርና በሰማያውያን ፊት መሆኑ ይታወቅ ዘንድ በሰማያዊው መሰዊያ ፊት በአባቶች አንብሮተ እድ ፀጋ መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ፡፡ በዚህ መልኩ ይህን ሰማያዊ የአገልግሎት ሹመት ይቀበላሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያን አባቶች አገልግሎታቸውን በአግባቡ እንዲፈጸሙ ምን ያስፈልጋቸዋል?

1. የቤተ ክርስቲያን ጸሎት
እያንዳንዳችን ክርስቲያን ሆነን ለመኖር፣ ዓለምን አሸንፈንና ፈተናን ተቋቁመን ለመኖር ምን ያህል የእግዚአብሔር እርዳታ እንደሚያስፈልገን በእውነተኛው የክርስትና ጠባብ ጐዳና ትንሽ የተጓዘ ሰው ሁሉ ያውቀዋል፡፡ ጻድቁ ኢዮብ እንዳለው «የሰው ሕይወቱ በምድር ላይ ብርቱ ሰልፍ ነው፡፡» ስለዚህ በየሰዓቱ «አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን» እያልን እንጸልያለን፡፡ /ማቴ 6፥13/

የራስን ሕይወት ለማዳን ይህን ያህል የእግዚአብሔር ጸጋና ጸሎት የሚያስፈልግ ከሆነ ከራስ አልፎ ሰዎችን ለማዳንማ ምን ያህል ጸሎትና የእግዚአብሔር እርዳታ ያስፈልግ ይሆን? ሰው የራሱን መዳን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የሚፈጽም ከሆነ፣ ብዙ መከራን መቀበል የሚጠበቅበት ከሆነ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ ተሹሞ ለማገልገል የተነሳ፣ ብዙ ነፍሳትን ከዲያብለስ ነጥቆ ወደ ክርስቶስ በረት ለማስገባት የሚዋጋ የክርስቶስ ወታደርማ ምን ያህል መከራን መቀበልና ፈተናን መጋፈጥ ይጠበቅበት ይሆን? ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ«ለሌሎች ከሰበኩ በኋላ እኔ ደግሞ የተጣልኩ እንዳልሆን ራሴን በመጐሰም አስገዛለሁ»ይላል።/1ኛ ቆሮ 9፥27/

ይህንን የምታውቅ ቤተ ክርስቲያን ሁለት መሠረታዊ መመሪያዎች አሏት፡፡ የመጀመሪያው ለክህነት የሚመረጡ ሰዎች ጠንካራ ክርስቲያኖች፣ ዲያብሎስን የመዋጋትና በእግዚአብሔር ኃይል ድል የማድረግ ልምድ ያላቸው እንዲሆኑ ያስፈልጋል ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ «አዲስ ክርስቲያኖች አይሁኑ በማለት ጠቅለል አድርጐ ተናግሮታል።/1ኛ ጢሞ 3፥6/ በተለይ ከፍተኛው የክህነት ደረጃ /ለጵጵስና/ የሚመረጡ ሰዎች ከመነኮሳት መካከል እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሰርታለች፡፡ እውነተኞች መነኮሳት ጌታ በምድረ በዳ ድል ያደረገውን ዲያብሎስ በምድረ በዳ ድል የሚያደርጉ፣ ለኃጢአት ሁሉ ስር የሆነውን ዓለምን መውደድን አሸንፈው በምድር ሰማያዊ ኑሮ የሚኖሩ፤ ለክህነት አገልግሎት የተመቹ ናቸው፡፡ ለክህነት አገልግሎት ከሚመረጡት በኩል የሚጠበቅ ነው፡፡

ከምዕመናንስ ምን ይጠበቃል? እነዚህ አባቶች ሕይወታቸውን ለምዕመናን ጥበቃ መስዋዕት እንዳደረጉ ምዕመናንም ስለነዚህ አባቶች አዘውትረው ሊጸልዩ ይገባል፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው «ወንድሞች ሆይ ስለእኛ ደግሞ ጸልዩ» ያለው፡፡ /2ኛ ተሰ 5፥25/

ቤተ ክርስቲያናችን በእያንዳንዱ ሥርዓተ ጸሎት ለአበው እንጸልይ ዘንድ ታሳስበናለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ሲቀደስ «ጸልዩ በእንተ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ስለሊቃነ ጳጳሳት ጸልዩ» ይላል ዲያቆኑ፤ እኛም እንጸልያለን፡፡ በቅዳሴአችን ጊዜ «አቤቱ ለቤተ ክርስቱያን አባቶች ፍቅርን ስጥ።» እያልን እንጸልያለን። ስለዚህ ኢያሱና ሆር ሙሴን ይጸልይ ዘንድ ሁለት እጁን ደግፈው እንደያዙት እኛም አባቶቻችን በጸሎታቸው፣ በአገልግሎታቸው ይጸኑ ዘንድ ኢያሱና ሆርን በጸሎት ልንደግፋቸው ይገባል፡፡ ኢያሱና ሆር ሲደክሙ የሙሴ እጅ ይታጠፍ ነበር፤ እስራኤልም ይሸነፉ ነበር፡፡ እኛም በጸሎታችን መደገፋችንን ካቆምን የአባቶች የአገልግሎት፣ የጸሎት እጅ ሊታጠፍ ይችላል፡፡ በዚህም የእስራኤል ዘነፍስ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን በአማሌቅ (የዲያብሎስ ሠራዊት) ትታወካለች፡፡

2. አስራት በኩራት ማውጣት ፦
በብሉይ ኪይን ከአስራ ሁለት ነገዶች አንዱ የሌዊ ነገድ ርስት አልተሰጠውም ነበር፡፡ ምክንያቱም የሌዊ ነገድ የካህናት ነገድ በመሆኑና ለካህናት ደግሞ ርስታቸው እግዚአብሔር በመሆኑ ነበር፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ለእግዚአብሔር ከሚያመጡት አስራት በኩራት ለካህናቱ ይሰጣቸው ነበር፡፡

ይህም ለአዲስ ኪዳን ካህናትም ይሰራል፡፡ ካህናት አባቶች ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፣ የተሰጣቸውን የአገልግሎት ሥልጣን በአግባቡ እንዲወጡ ከፈለግን እኛ በገንዘባችን፣ በዕውቀታችን፣ በጉልበታችን ልናግዛቸው ይገባል፡፡

አስራት በኩራት ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ትንሹ ስጦታ ነው፡፡ አያሌ ክርስቲያኖች ከዚህ ያለፈ ነገር ለቤተ ክርስቲያን ሲሰጡ ኑረዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ለራስ መስጠት መሆኑን ስለሚያውቁ ነው፡፡ እግዚአብሔርማ መች የኛን ገንዘብ ይፈልጋል፤ እኛው እንገለገልበት ዘንድ፣ ካህናቱ በዚያ እየተደገፉ መንጋቸውን በሰላም ይጠብቁ ዘንድ ነው እንጂ፡፡

በፈተና ቢወድቁስ?

ከላይ እንዳየነው በክርስትና ፈተና መምጣቱ አይቀርም፡፡ በተለይም ይህ ፈተና በአባቶት ዘንድ ጠንከር ማለቱ አይቀርም፡፡ «መንጋው ይበተን ዘንድ» ዲያብሎስ «እረኛውን» ለመምታት መጣሩ አይቀርም፡፡

ይህ ፈተና በአባቶች ላይ ውጤቱ የተለያየ ነው፡፡ ደገኞቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዲያብሎስን ድል አድርገው፣ አላውያን ነገሥታትን ድል ነስተው፣ ሩጫቸውን በታላቅ ድል ፈጽመው፣ እግዚአብሔርን አስደስተውና ምዕመናንን አገልግለው ያልፋሉ፡፡

ሌሎቹም እንደየአቅማቸው በተሰጣቸው ጸጋ አገልግለው ያልፋሉ፡፡ እስከዚህ ድረስ መልካሙን ጦርነት ተዋግተው ያሸነፉትን ጠቅሰን ተናገርን እንጂ፡፡

በዚህ ፈተና ድል የሚነሱ፣ መንጋው ይበተን ዘንድ ዲያብሎስ መትቶ የሚጥላቸው፣ ከዚያም በኋላ ከራሳቸው አልፎ ምዕመናንንም የሚያሰናክልባቸው አባቶችም ጥቂት አይደሉም፡፡


የአባቶች በፈተና መውደቅ ክብደቱ የተለያየ ነው፡፡ አባቶቻችን እንደኛው ሥጋ ለባሽ ፍጡር ናቸውና የጋራ ድካማችን ይጋራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በየዕለቱ ጥቃቅን ስህተቶችን መፈጸማቸው አይቀርም፡፡ ቅዱሳን አባቶች እንደሚሉት «ማንም በዚህች ምድር ላይ ለአንድ ቀን ቢውል እግዚአብሔርን ሳይበድል የሚውል የለም»፡፡

ስለዚህ አባቶችም በፈተና ቢወድቁ አይገርምም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ንስሐን ለሁሉም ትፈቅዳለች፡፡ እያንዳንዳቸው ካህናት አባቶች ለሌሎች የንስሐ አባት ቢሆኑም ለራሳቸው ደግሞ የንስሐ አባት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ስለዚህ አባቶቻችን በትንሽም በትልቅም ኃጠአት ቢወድቁ ንስሐቸውን እግዚአብሔር ይቀበላል፤ ምዕመናንም የኃጢአትን አስቸጋሪነት እያወቁ ያዝኑላቸዋል ይጸልዩላቸዋል እንጅ አይፈርዱባቸውም፡፡

ነገር ግን ክህነትን የሚያስነጥቁ ኀጢአቶች አሉ፡፡ አባቶች በእነዚህ ኃጢአቶች ቢወድቁና ንስሐ ቢገቡ ኃጢአታቸው ይቅር ይባላል፤ ክህነታቸው ግን አይመለስም፡፡ በእነዚህ ኃጢአቶች የተሰነካከሉና ንስሐ የገቡ አባቶች እንደምዕመናን ሆነው ወደ ቅድስና የማደግ ፀጋ ሳይነፈጋቸው በቤተ ክርስቲያን በጾም በጸሎት በሰላም ይኖራሉ፡፡

ከዚህ የከፋው የአባቶች ፈተና ግን ታላላቅ ኃጢአቶችን /ለምሳሌ፡- እንግዳ ትምህርት ማስተማር፣ ምንፍቅና፣ ዝሙት.../ ሰርተው ንስሐ አለማግባት ነው፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው የተወሰኑ የዋሃን ምዕመናንን ተከታይ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያውኩ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይታወቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የከፋፈሉት ታላላቆቹ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን የክህነት ማዕርግ የነበራቸው /አርዮስ ቄስ ነበር፤ ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ ነበር.../ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸው፡፡

በክፉ ኃጢአታቸው ጸንተው የሚኖሩትን፣ ይባስ ብለውም ምዕመናንን የሚከፋፍሉትን አባቶች ቤተ ክርስቲያን ከማኅበሯ ስትለያቸው /ስታወግዛቸው/ ኖራለች፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት» እንዳለ የቤተ ክርስቲያንን ማኅበር የሚያውኩትን፣ የንጉሠ ሠላም የክርስቶስን አደራ ተቀብለው በምዕመናን መካከል መለያየትን የሚዘሩትን «አባቶች» ቤተ ክርስቲያን ስትለያቸው ኖራለች፡፡

እንግዲህ በቤተ ክርስቲያን አባቶች ላይ ያለው ፈተና ሥጋ ለባሽ ሁሉ ከማያመልጣቸው ጥቃቅን ኃጢአቶች ከቤተ ክርስቲያን እስከሚለዩት ከባድ ኃጢአቶች ይደርሳል ማለት ነው፡፡

ምዕመናንና የአባቶች ፈተና

ከላይ ስለፈተናዎቹ ተነጋግረናል፡፡ አሁን ደግሞ ለእነዚህ ፈተናዎች የምዕመናን አጸፋ ምን መሆን አለበት? የሚለውን እናያለን፡፡
1. ለአባቶች በፈተና መውደቅ የእነርሱ እጅ ሊኖር እንደሚችል ማወቅ አለባቸው፡፡
ከላይ ቀደም ብለን እንደጥቀስነው አባቶች ጠንክረው የአገልግሎት ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ የምዕመናንም ጸሎት የእነርሱም ብርታት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም በመረዳት በቤተ ክርስቲያን በሚከናወነው ጸሎት ሁሉ ለአበው እንጸልይ ዘንድ ሥርዓት ሰርታለች፡፡

ስለዚህ አበው በፈተና ሲወድቁ ምዕመናን ራሳችንን መፈተሽ ይገባናል፡፡ «በየቅዳሴው ለአባቶች የምንጸልየው ጸሎት የት ሄደ? እግዚአብሔር ጸሎታችንን ለምን አልሰማም?» ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባል፡፡ በህዝበ እስራኤል ኃጢአት ታቦተ ጽዮን ተማርካ እንደነበር፣ ነቢያቱም በባቢሎን ተማርከው እንደነበረ አሁንም አባቶቻችን የተማርኩት በእኛ ኃጢአት ምክንያት ይሆንን? ብሎ ራስን መጠየቅ ይገባል፡፡

አባቶች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ ገዳማት ተጠናክረው ለጸሎትና መልካም አባቶችን ለማፍራት እንዲተጉ ረድተናቸዋል ወይ? አባቶች በፈተና ሲወድቁ እጃችን በእነርሱ ላይ የምንቀስር ሁላችን ወደ ፈተና እንዳይገቡ በምን ረዳናቸው? በጸሎታችን እናስባቸዋለን ወይ? አስራት በኩራት እናወጣለን ወይ?

«የሚያስተምሩንና አርአያ የሚሆኑን አባቶች ብናገኝ እናደርግ ነበር» ልንል እንችላለን፡፡ ነገር ግን ይህ ግማሽ ምክንያት እንጅ ሙሉ ስላልሆነ እኛም እነርሱም /ካህናቱም/ ከበደል አናመልጥም፡፡«ሁላችንም በድለናል»ማለት ይሻለናል።

2. መፍረድ አይገባም
«እንዳይፈረድብህ አትፍረድ» ይላል ጌታ፡፡ /ማቴ 7፥1/ ለመፍረድ ማንም ስልጣን አልሰጠንም፡፡ ኧረ ለመሆኑ አባቶች የተሸከሙትን ፈተና ሞክረን አይተነዋል ወይ? እኛ ብንሆን እንደነርሱ እንደማንሆን ምን ማረጋገጫ አለን? አባቶቻችን ዓለምንና ክብርን ንቀው፣ ራሳቸውን ለምንኩስናና ራስን የመካድ ኑሮ አሳልፈው ሰጡ፡፡ ከእነርሱ መካከል የተውትን ክብር የናፈቁ፣ የካዱት እኔነታቸው እያሸነፋቸው ይኖራሉ፡፡

በእነዚህ አባቶች ላይ እጆቻችን የምንቀስር ስንቶቻችን ይህንን ክብርንና ራስን የመካድ ኑሮ ሞክረነው እናውቃለን፡፡ አብዛኞቻችን የምዕራባውያንን የተንደላቀቀ ኑሮ የለመድን፣ የምንኩስናንና የተጋድሎን ኑሮ እንኳን የምንሞክረው ቀርቶ ስንሰማው የሚያንገሸግሸን፣ አንዳንዴም የምንቀላለድበት አይደለምን? ታዲያ እንዴት ሞክረውት የተሸነፉትን ለመውቀስና ለመኮነን እንፈጥናለን?

ምናልባት «ብንማርና አባቶች የሚገባውን ሁሉ ቢያደርጉልን እንደተባለው እንሆን ነበር» እንል ይሆናል፡፡ አይሁድም «በአባቶቻችን ዘመንስ በነበርን ኑሮ ነቢያትን ባልገደልን ነበር» ሲሉ ጌታ ገሠጻቸው እንጅ በዚያ አላመሰገናቸውም፡፡ /ማቴ 23፥30/ ይህንን ፍርድ ለእግዚአብሔር ትተን ለራሳችን መዳን ብንሠራ ግን መልካም ይሆናል፤ ፍርዱን ግን ለእርሱ እንተወው «በቀል የእኔ ነው» ብሏልና፡፡ / /

ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ሲታወኩ ዝም ትላለች ማለት አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ለምዕመናን መገልገል እንቅፋት የሚሆኑና የሚፈጥሩ አባቶች ከቤተ ክርስቲያን የሚለዩበት ሥርዓት አለ፡፡ ምዕመናን በአገልግሎት ተዋረድ አማካኝነት ችግራቸውንና አቤቱታቸውን ለሚመለከተው አካል ማድረሳቸውም ችግር አይደለም፡፡ ችግሩ በየመንገዱና በየቀልዱ አባቶችን በመስደብና በእነርሱ ላይ ለማላገጥ የውሸት «መንፈሳዊነታችን» ለመግለጥ ስንጥር ነው፡፡ ከእውነት ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆር ሰው የአባቶችን ውድቀት እየከፋውና ልቡ እያዘነበት በግድ ያወራዋል እንጅ፤ የካም ልጅ በኖህ ስካር እንደሳቀው በአባቶቹ «ስካር» አይዝናናም፤ አይቀልድም፡፡

3. ችግር ያለባቸውንና ቤተ ክርስቲያን የለየቻቸውን አባቶች አለመከተል
እውነተኛ ክርስቲያን ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሠላም የሚታዘዝ ነው፡፡ አንዳንድ አባቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን በንስሐ ተመልሰው በሰላም መኖር ሲያቅታቸው ምዕመናንን መከፋፈልና የራሳቸውን «ቡድን» በመሰብሰብ ተከታይ ማፍራት ይጀምራሉ፡፡ በዚህም አንዳንድ የዋሃን ምዕመናንን ከቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲለዩና እንዲወጡ መክፈል ይሞክራሉ፡፡

በዚህ ጊዜ ምዕመናን ከሁሉም በላይ ለቤተ ክርስቲያን ልንታዘዝ ይገባል፡፡ ማንም ቢሆን አባትነትን የሰጠችው ቤተ ክርስቲያን እስከሆነች ድረስ አባትነቱን የመንጠቅ መብት አላት፡፡ ቤተ ክርስቲያን አባትነቱን የነጠቀችውን ሰው መከተል ግን የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊ ስልጣን መናቅ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Written By: host
Date Posted: 12/18/2010
Number of Views: 14438

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement