View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ::.. Register  Login
  

የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ፤ዐለትን የሚሰነጥቅ

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ራሷን ከቻለችበት ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ በመደበኛነት ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ የቅዱስ ሲኖዶስን ምልዓተ ጉባኤ ታደርጋለች፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪና ሕግ አውጪ አካል በመሆኑ ባለፉት ዘመናት መልካም ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ መመሪያዎችንም አውጥቷል፡፡ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽቤት ሁሉም አካላት በመመሪያውና በውሳኔው መሠረት ሙሉ ለሙሉ እየፈፀሙ ነው ባይባልም፤ ቤተ ክርስቲያናችንን አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ አድርሰዋታል፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት ከቅዱስ ሲኖዶስ ብዙ የሚጠበቅ ነው፡፡ ሥልጣኔና ዘመናዊነት በበረታበት በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ ብዙ ፈተናዎች ይከሰታሉ፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ የምትመራው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በዓለም ላይ ያለች በመሆኗ በዘመኑ የመጡ ፈተናዎችና ችግሮች ሁሉ ይጋረጡባታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለአደራው አካል ቅዱስ ሲኖዶስ በመሆኑ በዙሪያው ያሉትን ሁኔታዎች በማጥናት፣ የአፈጻጸም ጉድለቶችን በመለየት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ውሳኔዎችን በመወሰን መመሪያ እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ በርካታ ችግሮች የተከሰቱ በመሆናቸው የሚከተሉት ጉዳዮች አንገብጋቢና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡

1) ሰንበት ት/ቤቶችና መንፈሳዊ ማኅበራት

ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑና አፈጻጸ ማቸው ምን ላይ እንደሆነ መታየትና መፈተሽ አለበት፡፡ ሊቆጣጠርና ሊመራ የሚችለው አካል ተገቢው ዕውቀትና ችሎታ ያለው ሆኖ እንዲመራ ማድረግ የማይቻል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን ተከታዩን ትውልድ ልታጣ እንደምትችል መገመት አያስቸግርም፡፡ በመሆኑም የሰንበት ት/ቤቶች ጉዳይ በቸልታ ሳይሆን ልዩ ትኩረት የሚያሻው ተቋም ነው፡፡

2) ተሐድሶን በተመለከተ

በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያንን እየፈተናት የሚገኘው የውጭ ጠላት ሳይሆን በውጭ ተገዝቶ ወደ ውስጥ የሰረገው የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ ጉዳይ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለኦርቶዶክሳዊ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት ሥርዓትና ቀኖና አዲስ ሕግ እንዲያወጣ የሚጠበቅ ባይሆንም የነበረው ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮና ሥርዓትም እንዳይጣስ ጥብቅ መመሪያ በመስጠት አቅጣጫ ሊያሲዝ ይገባል፡፡ በየቦታው የሚሰጡ መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የሚዘመሩ መዝሙሮች፣ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያላዩትና ያልመረመሩት በየጓዳው የሚጻፉ መጻሕፍት፣ ወዘተ ተፈትሸው ሥርዓት እንዲይዙ መደረግ አለበት፡፡

3) ሹመትን በተመለከተ፡-

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የተከበረና ቅዱስ በመሆኑ ስለሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት የመጀመሪያው ተጠያቂ በመሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ለሢመት የሚቀርቡ እጩዎች በሙሉ ከመንፈሳዊነታቸው በተጨማሪ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፣ የተመሰከረላቸው፣ ብቃት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ዓመት ለመሾም ሳይሆን ለወደፊቱ እጩዎችን ለማግኘትና ለማዘጋጀት ከወዲሁ መወሰን አለበት፡፡ ወቅቱ በተሐድሶዎች አማካይነት ግርግር የበዛበትና ለሰርጐ ገቦች አመቺ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል እንላለን፡፡

4) መዋቅራዊ አሠራርን መጠበቅ፡-

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠራር በአብዛኛው ወቅቱ በሚጠይቀው ሒደት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ዘመናዊ ባለመሆኑ ግልጽ የሆነ የሓላፊነትና የተጠያቂነት ይዘት አይታይበትም፡፡ በመዋቅር ውስጥ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ አብረው ያሉት ግለሰቦችም ጭምር በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ ገብተው የራሳቸውን ዓላማ እንዲያራምዱ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱን አሠራርና አደረጃጀት በተመለከተ የሚያጠና የባለሙያዎች አካል በማቋቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናና እንዲወሰን ማድረግ ይኖርበታል፡፡

5/ ነጋ አድራሶችን እና አጭበርባሪዎችን በተመለከተ፡-

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተለይም በመንበረ ፓትርያርክ አካባቢ አንዳንድ ግለሰቦች ወሬ በማመላለስና በማጭበርበር ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የአባቶቻችንን የዋህነት እንደጸጋ ቆጥረው ከእግራቸው ሥር በመውደቅ በረከት ማግኘት ሲገባቸው የተጭበረበሩ የሐሰት ሰነዶችን በማቅረብ የቤተ ክርስቲያን አካላት እርስ በራሳቸው እንዲጋጩ፣ አባቶች ልጆቻቸውን እንዲጠሉ፣ ልጆች በአባቶቻቸው ላይ ጥርጣሬ እንዲኖራቸው እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ዋና ማሳያ የሚሆነው በሐሰት በማኅበረ ቅዱሳን «ስም» የተዘጋጀው የሃያ አምስት ዓመት ስትራቴጅክ ሰነድ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የዚህን ሰነድ አዘጋጆችና አሠራጮች ማንነት በመመርመር ከያዙት ተግባር እንዲቆጠቡ፣ የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ለወደፊቱም ድርጊቱ እንዳይደገም በማያገባቸው የሚገቡ ወሬ አመላላሾች ቦታ ሊያጡ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ በላይ ከአንድ እስከ አምስት የተዘረዘሩትን እና ሌሎች ጉዳዮችን በአሁኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶአቸው ቢታዩ ቤተ ክርስቲያንን አንድ ርምጃ ወደፊት ለማስጓዝ አመቺ ሁኔታዎች ይፈጠራል ብለን እናምናለን፡፡ ውሳኔው የአባቶቻችን ቢሆንም የእኛ ድርሻ እንደ አካልነታችን የተሰማንን ማቅረብና በሀሳብ መደገፍ በመሆኑ ሓላፊነታችንን ተወጥተናል ብለን እናምናለን፡፡

ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ዕድገት የሚ ጋደሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትንም ሆነ ሌሎች መሆን አለባቸው የሚሉትን ሀሳብ ለአባቶች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከታች እስከ ላይ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ለተከፈሉ ምዕመናንና ለቤተ መቅደስ አገልጋዮች ካህናት ጥንካሬ የቤተ ክርስቲያን ጤናማ አስተዳደር ወሳኝ ነው፡፡ ጠንካራ ዐለት በመዶሻ እንዲሰነጠቅ ጠንካራ ውሳኔ ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልኮ ወሳኝ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንደ ዐለት ለጠጠረው የቤተክርስቲያኒቱ ሁሉ አቀፍ ችግር የሚሰነጥቅ መዶሻ ነው እንላለን፡፡በመጨረሻም እግዚአብሔር በአባቶቻችን አድሮ መልካም የሆነውን ሁሉ እንፈጽም ዘንድ በጸሎት ልንበረታ ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


Written By: admin
Date Posted: 5/17/2011
Number of Views: 7094

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement