View in English alphabet 
 | Thursday, April 25, 2024 ..:: ነገረ ቅዱሳን ::.. Register  Login
  

ቅድስት አርሴማ ሰማዕት ዘአርማንያ

የቅድስት አርሴማ ወላጆች አባቷ ቴዎድሮስ እናቷ አትናትያስ ይባላሉ:: በፈሪሃ እግዚአብሔር  በአምልኮ ጸንተው በሕጉ ተመርተው የኖሩ ደጋግ ሰዎች ናቸው:: ልጅ አጥተው መካን ሆነው ሲኖሩ ዘር እንዲሰጣቸው ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር:: እግዚአብሔርም  ጸሎታቸውን ሰምቶ ደም ግባቷ ያማረ መልከ መልካም የሆነች እንደ ጸሐይ የምታበራ ልጅ ሰጣቸው:: ቅድስት አርሴማ የነበረችበት ዘመን ዘመነ ሰማዕታት ይባላል:: ዲዮቅልጥያኖስ የሮም ቄሳር ሆኖ የነገሰበት (እኤአ ከ284ዓ/ም - 305 ዓ/ም) : አብያተ ክርስቲያናት የተዘጉበትና አብያተ ጣኦታት ተከፍተው ክርስቲያኖች በክርስቶስ ስም ልዩ ልዩ መከራና ሰማዕትነት የሚቀበሉበት ዘመን ነበር::  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤  ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤  በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ” እንዳለ  ዕብ  11:35-37

ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ መልኳ ውብ የሆነ ብላቴና ድንግል ሊያገባ ፈልጎ ሔደው መርጠው ያመጡለት ዘንድ ሠራዊቱን በየሀገሩ ሰደደ። ይህች ቅድስት አርሴማ በሮሜ ሀገር በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ከሌሎች ማኅበረ ደናግል ጋር ነበረች:: እየፈለጉ ሲሄዱ እሷን አይተው ሥዕሏን ሥለው ወስደው ሰጡት። መልካም ብላቴና አግኝታችሁልኛል ሄዳችሁ አምጡልኝ አላቸው። እርሷም በመንፈስ አውቃ እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ እንጂ ከአረማውያን ጋር አንድነት የለኝም ብላ ከ39 ደናግል ጋር ወደ አርማንያ ተሰደደች::

ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ የከበረች አርሴማን በፈለጋት ጊዜ አላገኛትም: ግን በአርማንያ አገር እንዳለች ሰምቶ ለአርማንያ ንጉሥ ለድርጣድስ አስፈልገህ ላክልኝ ብሎ ላከበት። ንጉሥ ድርጣድስ ደናግሉ ከተሰወሩበት አስፈልጎ አገኛት። እሱም  የቅድስት አርሴማን መልከ ቀናነቷን አይቶ ይህችንስ አሳልፌ አልሰጥም ብሎ መሪያቸው አጋታን አባብላ እሺ ታሰኝለት ዘንድ አዘዛት። እሷም አይሆንም ያልሁ እንደሁ ጸብ አጸናለሁ ብላ እሺ አለችው እሷን ግን ለመንግሥተ ሰማያት የታጨሽ ነሽና ይህ ዕልው እንዳያረክስሽ እወቂ ብላ ልቧን አስጨከነቻት። ንጉሡም ይዞ ወደ እልፍኙ ሊአስገባት ከአደባባይ መካከል ተነሥቶ  ድንግል አርሴማን ያዛት። ኃይል መንፈሳዊ ተሰጥቷታልና ጎትታ ከመሬት ቀላቀለችው። እርሱ ግን በጦርነት እጅግ የጸና አርበኛ ስለነበር በታናሽ ብላቴና ስለተሸነፈ ያን ጊዜ አፈረ::  ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧት:: ከዚህ በኋላ ደናግሉን ሁሉ ከእናታቸው (እመምኔት) አጋታ ጋር በሰይፍ አስመትቷቸዋል። ሥጋቸውም በተራራ ጫፍ ላይ እንዲጣል ተደረገ:: ይህም የሆነው በመስከረም 29 ነው::

ሰማዕታት ከተገደሉ በኋላ በንጉሡ ላይ ጋኔን ተጫነበት: መልኩም ተለውጦ እንደ እርያ ሆነ:: ወዳጆቹም በዳነልን እያሉ ሲጨነቁ የታዘዘ መልአክ መጥቶ እኅቱን ከጎርጎርዮስ በቀር የሚያድነው የለም አላት። ንጉሥ ድርጣድስ የአርማንያውን ሊቀጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስን በሃይማኖት ምክንያት ተጣልቶ ከአዘቅት ጉድጓድ ውስጥ አስጥሎት ነበርና የሞተ መስሏቸው ደነገጡ። እርሱ ግን መልአኩ ለአንዲት መበለት ነግሮለት ምግቡን እየጣለችለት ይኖር ነበርና ምናልባት አምላኩ ጠብቆት ይሆናል ብለው ገመድ ቢጥሉ መኖሩን ለማሳወቅ ገመዱን ወዘወዘው። ቢጎትቱት በ15ዓመቱ ከሰል መስሎ ወጥቷል። የንጉሡ እኀት ወንድሜን አድንልኝ አለችው። ቅዱስ መጀመሪያ አጽመ ሰማዕታትን አሳዩኝ ብሎ አሳይታው ያን አስቀብሮ ካለበት ሄዶ ባድንህ በፈጣሪዬ ታምናለህን? አለው። ግዕዛኑን ፈጽሞ አልነሳውም ነበርና በአዎንታ ላሱን ነቀነቀ። የተደረገለትን እንዳይዘነጋ ከእጁ ከእግሩ የእርያ ምልክት ትቶ ጸልዮ አድኖታል። አመንኩ አጥምቀኝ አለው ለማጥመቅስ ሥልጣን የለኝም አለው። በአንጾኪያው ሊቀጳጳስ ተጠመቀ። እሱንም ሊቀጳጳስነት አሹሞት ብዙ ተግሳጻት ጽፎ ብዙ ድርሳናትን ደርሶ ብዙ የቱሩፋትን ሥራ ሠርቶ አርፏል። ዕረፍቱ ታሕሣስ 15 ቀን ነው።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን: እኛንም በእናታችን በቅድስት አርሴማ አማላጅነት በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን: በረከታቸውም ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን ::

Written By: admin
Date Posted: 11/5/2013
Number of Views: 9613

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement