View in English alphabet 
 | Friday, March 29, 2024 ..:: ኅብረ ነገር ::.. Register  Login
  

እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ አሸጋገራችሁ!

በስመ  አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ  አሐዱ አምላክ አሜን !

                           እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ አሸጋገራችሁ!

"የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ::"
ሕዝ 36፥26

እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ በእጆቹ አበጃጅቶ በአርአያው ከፈጠረው ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የአባትነት ፍቅሩን ፣የፈጣሪነት ርኀራኄውን፣ የማያልቀውን ትዕግስቱን አላጓደለበትም:: ምክንያቱም እረኛችን ነውና በጎቹን፣ አምላካችን ነውና ፍጡሮቹን ፣ንጉሳችን ነውና ሕዝቦቹን አይተወንምና ነው።

ይሁንና የሰው ልጅ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (በሮሜ 15፥20) ላይ እንደገለጸው "የማደርገውን አላውቅምና የምጠላውን ያን አደርጋለሁ፤ የምወደውን እርሱን አላደርገውም የማልወደውን ግን አደርጋለሁ። ፈቃድ አለኝና መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም፤ የማልወደውን የማደርግ ከሆንኩ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም በእኔ የሚኖር ኃጢያት ነው እንጂ። " በማለት የሰው ልጅ ዝንባሌ ከጽድቅ ይልቅ ኃጢያትን፣ ከሕይወት ይልቅ ሞትን፣ ከሰላም ይልቅ ሁከትን፣ ለአምላኩ ከመታዘዝ ይልቅ እንቢተኝነትን፣ እርስ በእርስ ከመፋቀር ይልቅ መጣላትን፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከመተሳሰብ ይልቅ ምቀኝነትን፣ ከቁም ነገር ይልቅ ቧልትን፣ ከመታመን ይልቅ አስመሳይነትን፣ ከእውነት ይልቅ ሐሰትን፣ ከሃይማኖተኛነት ይልቅ ከሃዲነትን እየመረጠ መላ ሕይወቱን እያናወጠ የሚጓዝ መሆኑን ያስገነዝበናል። ታዲያ የሰው ልጅ ማሰብ ሲገባው ከድካሙ ማስተዋል ሲኖርበት ከለገመ የድንጋይ ልብ አለው የሚባለው የዛን ጊዜ ነው።

ለዚህ ነው የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር እየራቁ መቅረታቸው፣ እየወደቁ መድቀቃቸው በሞላ ቁጥር እየጎደለባቸው ሲንገፈገፉ በጭንቀት አለንጋ ሲገረፉ እነሆ ወደእግዚአብሔር ጩኸት ጀመሩ፣ ማልቀስ ጀመሩ፣ መማጸን ጀመሩ "ልበ ንፁሐ ፍጥር ሊተ እግዚኦ መንፈሰ ርቱዐ ኃድስ ውስተ ከርስየ ኢትግድፈኒ እምቅድመ ገጽከ" መዝ 50፥10 "አቤቱ ንፁህ ልብን ፍጠርልን የቀናውንም መንፈስ በውስጣችን አድስልን ከፊትክም አትጣለን" እያሉ ለመኑ . የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትንም የማይነሳ ቸሩ አምላክ ስለፍጡሮቹ ይገደዋልና ርኀራኄው የባሕርዩ ነውና ስለ ቅዱስ ስሙ ሲል የራቅነው እንድንቀርብለት፣ የወደቅነው እንድንነሳለት፣ ማስተዋል ያቃተንም እንድተጋለት እነሆ "አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትዕዛዜም አስኬዳችኋለሁ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ"           (ሕዝ 36፥26) በማለት "በውኑ ኃጢያተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን" (ሕዝ 18፥23) ብሎ የማጽናኛ ቃልኪዳኑን የአባትነት ፍቅሩን ገለጸልን።
ታዲያ ቃልኪዳኑን ሊፈጽምልን፣ ቅዱስ መንፈሱንም ሊያድለን እነሆ ከሰማየ ሰማያት ወረደልን ከቅድስተ ቅዱሳን ከንጽህተ ንጹሐን ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ተወለደን:: በዚህ አለም ወጥቶ ወርዶ፣ ራሱን አዋርዶ፣ መከራ መስቀልን ተቀብሎ፣ በሞት አደባባይ ውሎ፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሦ ሞታችንን ሞቶ፣ በመቃብርና በሲዖል ገብቶ ሞትን ደመሰሰልን፣ ሲዖልን በረበረልን፣ ገነትን ከፈተልን፣ ጨለማውን አበራልን፣ ንፁህ ልብ ፈጠረልን የቀናውንም መንፈስ አደሰልን፣ አሮጌውን ሰውነት (ማንነት) አስወገደልን፣ ቅዱስ መንፈሱንም ሞላን፣ የመንግስተ ሰማያት ዜግነትን ከእርሱም ጋር የመኖር ሕይወትን ዳግመኛ ሰጠን። ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን!!
ዛሬስ ያለንበት ሁኔታ ምን ይመስል ይሆን? ከዚህ ሁሉ ካሳ በኋላ ለመሆኑ እግዚአብሔር የሚደሰትበት፣ ነፍሳችን የምትጠቀምበት ሕይወት አለን ይሆን? ለመሆኑ ዘመን አልፎ አዲስ ዘመን ሲተካ "እንኳን ለአዲስ ዓመት አደረሳችሁ" ስንባባል በእርግጥ የዘመን አሮጌ ኖሮ ይሆን?  ደራሲ ከበደ ሚካኤል በግጥም መድብላቸው እንደገለጹት
“በዘመን ግስገሳ እድሜያችን ተማርኮ
ያለፍነው እኛ ነን እርሱ አይደለም እኮ" እንዳሉት
በዑደት (በዙረት) የሚታደስ ዘመን ባይኖርም ነገር ግን በተሰጠው የጊዜ ርዝመት ውስጥ እንደሚገባው ሊመላለስ ያልቻለና ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ጸጋ መጠቀም ያቃተው በሕይወቱ ውስጥ በኃጢያት ያረጀና የጽድቅ ፍሬ ማፍራት የተሳነው ሊታደስም የሚያስፈልገው የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ውለታ የዘነጋውና ዛሬም እንደገና ወደ ድንጋይነት የተመለሰው የሰዎች ልቡናና ውሳጣዊ ሀሳባቸው ነው።

ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ "አሮጌውን ሰውነት አስወግዱ የልቦናችሁን አሳብ አድሱ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰውነት ልበሱ" (ኤፌ 4፥22) ብሎ በመናገር የሰውን ውሳጣዊ ባህሪይ የሚያሳድፉትን፤ የተቀደሰ ሕይወቱን የሚያረክሱትን፤ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሙዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለያያት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት ወ.ዘ.ተ (ገላ 5፥19-21) ከሕይወታችን በማስወገድ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደመከረን በዚህ ሁሉ የተመላለስንበት "ያለፈው ዘመን ይብቃ" (1ጴጥ 4፥3) ብለን በመወሰን አሮጌው ጸባያችንን፣ያረጀ ሕይወታችንን ከምናልፈው ዘመን ጋር ወደኋላ ጥለን በንስሐ ታጥበን፣ በሥጋውና በደሙ ተቀድሰን ርምጃችንን ብናስተካክልና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አባታችን፣ ከድንግል ማርያም እናታችን፣ ከቅዱሳን ረዳቶቻችን ሁሉ ጋር ብንሆን። "ሥለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው አሮጌው ነገር አልፎአል ሁሉም አዲስ ሆኖአል" (2ቆሮ 5፥17) የሚለው የእግዚአብሔር ቃል በሕይወታችን ሲፈጸምልንና በ40 እና በ80 ቀናችን የተቀበልነውን ቅዱሱን መንፈስ ዳግም በሕይወታችን ሲያድስልን እናገኘዋለን።

ስለሆነም የደከሙትን እጆቻችንን አበርትተን፣ የላሉትንም ጉልበቶች አጽንተን መጪውን ዘመነ ማርቆስን በአዲስ ሕይወት በአዲስ መንፈስ በአዲስ ልብ ለመቀበል ያብቃን::  

የእግዚአብሔር ቸርነት :
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት በረከት :
የቅዱሳን ምልጃ ጸሎት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን!
       

ወስብሐት ለእግዚአብሔር !



አዘጋጅ፡-

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ማኅበረ ቅዱሳን
የአሜሪካ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል
መስከረም ፳፻፮ ዓ.ም


Written By: host
Date Posted: 9/10/2013
Number of Views: 6590

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement