View in English alphabet 
 | Thursday, April 18, 2024 ..:: ንቁ ::.. Register  Login
  

በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሕገ ወጥ ተግባር ሲፈጽም የተገኘ ሙስሊም በቁጥጥር ሥር ዋለ

(አዲስ አበባ)፡- ዕለተ ዓርብ መስከረም 30/2001 ዓ.ም ነው፡፡ ሰዓቱም ከጠዋቱ 2 ሰዓት፡፡ እንደተለመደው ሃይማኖታዊ ተግባር ሁሉ በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተ ክርስቲያን ኪዳን ከተደረሰ በኋላ ምእመናን ወደየቤታቸው ሊሄዱ ሲዘጋጁ ነበር፤ ከቤተመቅደሱ አቅራቢያ ያልተለመደ አስደንጋጭ ድምፅ የተሰማው፡፡


ከነጫማው ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባ አንድ ግለሰብ ወለል ላይ ነጠላ አንጥፎ የሙስሊም የእምነት ሥርዓት በሚመስል መልኩ እየሰገደ «አላህ ወአክባር፣ አላህወአክባር፣ ሥዕል ይውረድ፣ መስኪድ ይሠራ .. አላህወአክባር» እያለ ይጮሃል፡፡ ባልተለመደው ክስተት የተደናገጡት ምእመናን ዝም አላሉም ግለሰቡን ይዘው የደብሩን ጥበቃ ሠራተኛ ጠርተው ከቤተ መቅደስ እንዲወጣ አደረጉት፡፡

በዚህ ግለሰብ ተግባር የተቆጡት ምእመናን ፖሊስና ጋዜጠኛ ሳይመጣ ግለሰቡ ከግቢ እንዳይወጣ የሙጥኝ ይላሉ፡፡ አንዳንድ እማኞች እንደሚሉት ይህ ሲሆንም ግለሰቡ ‹‹አላህ ወአክባር ይህ ቦታ የመስኪድ እንጂ የቤተ ክርስቲያን አይደለም፡፡ ሥዕሎቹ ይውረዱ፣ መስኪድ ይሠራ» እያለ በያዘው ትልቅ መፋቂያ ጥርሱን እየፋቀ ምራቁን በግቢው ውስጥ ሲተፋ ነበር፡፡


ከዚህ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰቡ፤ ከበርካታ ምስክሮች ጋር ወደ አራዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ተወሰደ፡፡ በግለሰቡ ላይ ምንም ጉዳት ሳያደርሱ በሕግ እንዲጠየቅ ያደረጉት ምእመናን ስለ ድርጊቱ ያዝኑ፣ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይቆጩ፣ አንዳንዶቹም ያለቅሱ እንደነበር ተስተውሏል፡፡


«ድርጊቱ እንደ ተፈጸመ የሕግ አካልን ጠርተን ጉዳዩ እንዲታይ አድርገናል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሃይማኖት ነፃነት እንዳለ መደንገጉ ይታወቃል፤ ይህ ተግባር ግን ክርስቲያኑን ያሳዘነ ነውር በመሆኑ ስለ ድርጊቱ መንግሥት አፋጣኝ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ እና እንደሚያሳውቀን እምነት አለን» ይላሉ ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የደብሩ ዋና ጸሐፊ ዲያቆን አምባዬ ዓለሙ፡፡


እንዲህ ዓይነት የቤተ ክርስቲያንን ሕግ፣ ሥርዓትና ደንብ የሚጥሱ ግለሰቦች ሲያጋጥሙ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ራስ በተማሩት ትዕግሥት ለሕግ አሳልፎ የመስጠት ባህልን በማዳበር ቤተ ክርስቲያኒቱን መጠበቅ እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡


«ጉዳዩን ከሕግና ሥርዓት አኳያ ካየነው ግለሰቡ ቤተ ክርስቲያን መግባቱ ሳይሆን መስገዱና ምእመናንን አስፈላጊ ባልሆነ ጩኸት ማወኩ ወንጀል ነው» የሚሉት ደግሞ የደብሩ ጥበቃ አቶ ታዬ ብርሃኑ ናቸው፡፡


«ድርጊቱ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ግለሰባዊ ነው፡፡ እጅ ከፍንጅ መያዙ የምርመራውን የፍርድ አሰጣጥ ሁኔታ የተፋጠነ ያደርገዋል የሚል እምነት አለን» ያሉት አቶ ታዬ በሀገሪቱ በሃይማኖት መካከል ያለውን መቻቻል ለማደፍረስ የሚጥሩትን ለይቶ ለሕግ ማቅረብ ይገባል ባይ ናቸው፡፡


በአራዳ ክፍል ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ዋና ሳጂን ካሱ ጠዋፊ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ኑር ሐሰን ከማል የተባለ ግለሰብ በዕለቱ ጠዋት ሁለት ሰዓት ላይ በቤተ ክርስቲያን መቅደስ ውስጥ ገብቶ እየሰገደ «አላህ አክበር ቤተ ክርስቲያን ይፍረስ፣ መስኪድ ይሠራ» እያለ የምእመናንን ጸሎትና ሠላም ሲያውክ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ጠቅሰው ጉዳዩ ጥብቅ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡


ተከሳሹ በእምነት ክህደት ቃሉ ከጉመር መምጣቱን እና ይህንን ድርጊት የፈጸመውም ‹‹ከአላህ ተልኮ›› መሆኑን እንደተናገረ የገለጹት ዋና ሳጂን፤ በአሁኑ ወቅት ግለሰቡ በእሥር ላይ እንደሚገኝና የምርመራ መዝገቡ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለፍርድ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡


በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ምእመናን በድርጊቱ ክፉኛ ማዘናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ «የወቅቱ አገልግሎቴ ፍሬ ሰሞን ነበር፤ ግለሰቡ እየጮኸ ቤተ ክርስቲያኑን ሲያውክ እኔም ሆነ ምእመናን ክፉኛ አዝነናል፡፡ ግለሰቡ ተልዕኮ ሳይኖረው በድፍረት መቅደስ ውስጥ አይገባም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን የቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊዎችም ሆኑ የሕግ አካላት አጥብቀው ሊከታተሉት ይገባል» ያለው ዲያቆን ዳዊት ገብረ ማርያም ነው፡፡


ዲያቆን ዓባይነህ ዋቅጅራ በበኩሉ «ከአሁን ቀደምም ሌሎች የእስልምና እምነት ተከታዮች በተመሳሳይ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ገብተው ፎቶ አንስተው ሲወጡ የተስተዋሉ መሆኑን ጠቅሶ፤ ቅጥር ግቢው ጥንቃቄና ጥበቃ ካልተደረገበት ድርጊቱ ቀጣይ ይሆናል የሚል ስጋት እንዳለው ይገልጻል፡፡»

 

የዕለቱ የዓይን እማኞች ወ/ት አጥናፍ፣ ወ/ት ጽጌ፣ አቶ ኃይሉ እና ወጣት መስፍን በሰጡት አስተያየት፤ በቤተክርስቲያን የንቀት ተግባር የፈጸመው ይህ ግለሰብ ተልዕኮ ይኖረዋል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በሕግ አካል ተገቢው መቀጣጫ ሊሰጠው ይገባል ይላሉ፡፡


በሀገሪቱ በእምነት ረገድ ተቻችሎና ተከባብሮ የሚኖረውን ሕዝብ ለማጋጨት ሆን ተብሎ የተፈጸመ ስለመሆኑ የግለሰቡ ተግባር ምስክር ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ቤተ ክርስቲያኗ እንዲህ ያለውን ድርጊት ልታወግዝ ይገባታልም ብለዋል፡፡


ከአሁን ቀደም ሦስት ግለሰቦች በግቢው ውስጥ ትምህርት በመሰጠት ላይ እያለ በማን አለብኝነት ገብተው በሞባይላቸው ቪዲዮ ቀርጸው መውጣታቸውን እንዳስተዋሉ የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ በዛን ወቅት ተገቢው እርምጃ ቢወሰድ ይህ ድርጊት ባልተደገመ ነበርም ብለዋል፡፡


ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የቅዱስ ፖትርያርኩ ረዳት እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሣሙኤል እንደተናገሩት በአንዳንድ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደረሰው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ነው፡፡


በቅርቡ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በሙዳይ ምፅዋት ቆጠራ ወቅት በሙዳይ ምፅዋት ሳጥን ውስጥ «ስማችን አይታወቅም ግን ሁላችሁም ኢትዮጵያዊያን እስላም ካልሆናችሁ እንገድላችኋለን» የሚል ጽሑፍ መገኘቱን ከደብሩ በቃለ ጉባኤ ሪፖርት መደረጉን ተናግረዋል፡፡


ከዚህም ሌላ በአንዳንድ አካባቢዎች የአክራሪነት ስሜት ባላቸው አንዳንድ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሕፃናትና በሴቶች ላይ ማተባችሁን በጥሱ የሚል ዛቻ እንደሚደርሳቸውም ብፁዕነታቸው አስረድተዋል፡፡


ሀገረ ስብከቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ይሄን ድርጊት የመንግሥት አካላት እንዲያውቁት እያደረጉና ድርጊቱም ወደ ሌላ አቅጣጫ ከመሄዱ በፊት እርምት እንዲወሰድበት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ምእመኑን በክርስቲያናዊ ትዕግሥትና ፍቅር አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅም ሊቀ ጳጳሱ ጥሪ አድርገዋል፡፡

 

 


Written By: host
Date Posted: 11/14/2008
Number of Views: 14327

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement