View in English alphabet 
 | Tuesday, April 23, 2024 ..:: ንቁ ::.. Register  Login
  

የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣን የማገድ ሙከራ አንድምታ

“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።” የማርቆስ ወንጌል 16፥15 

ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በ ኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ በሰንበት  ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ከጳጉሜን 1985 ዓ. ም ጀምሮ ለ18ዓመታት በየወሩ አሁን ደግሞ በየሁለት ሳምንቱ  በመታተም የቤተክርስቲያንን ዜናዎችን፣ ትምህርተ ወንጌልን፣የአባቶችን ሕይወት፣ ከምዕመናን የሚነሱ መንፈሳዊ ጥያቄዎችን ምላሽ በመስጠት፣ የገዳማት እና አድባራት እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንቅስቃሴ በመዘገብ ምዕመናን በማስተማር፣በማሳወቅ እና መንፈሳዊ ችግር/ፈተና ፈቺ በመሆን አገልግሎት ስትሰጥ የኖረች የቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ነች::

ስምዐ ጽድቅ መታተም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ባቀረበቻቸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት የሚጻረር ጽሁፍ አቅርባ አታውቅም:: ይህም የሆነበት ምክንያት ማንኛውም ጽሁፍ በጋዜጣዋ ላይ ከመውጣቱ በፊት ቅዱስ ሲኖዶስ ለማኅበሩ በሰጠው ስልጣን መሰረት ማኅበሩ ባቋቋመው የነገረ ሃይማኖት እና የጋዜጠኝነት ሙያ ጥልቅ ዕውቀት ባላቸው የኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት ተደጋግሞ ስለሚገመገም ነው፣ በተጨማሪም የታወቁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን  በነፃ ሓሳባቸውን እና ምክራቸውን በመለገስ ለማስተካከል ስለሚተባበሩ ነው::

ጋዜጣዋ  የምትታወቀው እና በብዙ ምዕመናን ዘንድ የምትናፈቀው በይዘት ስፋቷ እና የስርጭት አድማሷ ነው። ይህ በእንዲህ እያለ ለ 18 ዓመት ያለማቋረጥ አገልግሎት ስትሰጥ የነበረችው ጋዜጣ ያለአንዳች ምክንያት እንዳትታተም ለማድረግ ተሞክሯል፤ ይህም የተደረገው በወቅቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ በሆኑት በአባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ለማተሚያ ቤቶች በተጻፈ ደብዳቤ ነው:: ይህ ድርጊት በአንድ የመምሪያ ኃላፊ ብቻ የተቀነባበረ እና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለመግታት በሳቸው ብቻ የሚደረግ እንቅስቃሴ እንዳልሆነ የሚያመለክተው ማኅበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ከ 10 በላይ ከሚሆኑ የመምሪያ  ኃላፊዎች ጋር በመመካከር አገልግሎቱን ሲፈጽም ቆይቷል፣ ነገር ግን እኝህ ሰው የመምሪያው ኃላፊ ከሆኑ በኋላ እሳቸውን እጅ በማድረግ ከውስጥም ከውጭም ቤተክርስቲያኒቱን ለማፍረስ የሚፈልጉ ወገኖች እንደመጀመሪያ የቤት ስራቸው አድርገው የያዙትን የማኅበሩን አገልግሎት ለማዳከም ከቻሉም ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ለመግታት ነው::

 

በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የሚተላለፈውን ትምህርት እና የቤተ ክርስቲያን መረጃ ለማስተላለፍ አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ጋዜጣዋን ለማገድ መሞከር የማኅበሩን ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማዳከም ብሎም ለመግታት የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል በትክክል ይገነዘባል:: ስለሆነም፣ ይህ ለብዙዎች የነፍስ ምግብ የሆነውን የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት ለማደናቀፍ  የሚደረገውን ሙከራ ሁሉ ለማክሸፍ እና ለመቋቋም ማኅበሩ የበኩሉን በማድረግ ላይ ቢገኝም ጉዳዩ  የቤተክርስቲያን ልጆች የሆኑ ሁሉ የሚመለከት በመሆኑ ይህንን ድርጊት በተቻለው ሁሉ በመቃወም በፍጥነት የመፍትሄው አካል መሆን  እንደሚጠይቅ ማዕከሉ ያምናል::

 

በተደጋጋሚ ህገ ቤተ ክርስቲያንን በማፍረስ  የሚታወቁት የማደራጃ መምሪያ  ኃላፊው ማኅበሩን በተለያየ ጊዜ አገልግሎቱን ለማዳከም ከሲኖዶሱ እና ከመምሪያው ሊቀ ጳጳስ እውቅና  ውጪ የተለያዩ  መግለጫዎችን፣ መሰረት የሌላቸው ክሶችን በማቅረብ የጀመሩትን እንቅስቃሴ አሁን ደግሞ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ላይ ያለችውን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ለማገድ በመሞከር የተደበቀ ቤተክርስቲያንን የማፍረስ ስራቸውን ቀጥለውበታል:: ማኅበሩ በግለሰቡ ህገ ወጥ አሠራር አገልግሎቱ  እየተደናቀፈ በመሆኑ በ 2003 ዓ ም ግንቦት ወር በተካሄደው የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ መፍትሄ እንዲሰጠው በደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ በጠየቀው መሰረት፤ ቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳውን አጽድቆ ጉዳዩ ን በመመርመር ችግሩን አጣርቶ  የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ ብጹአን ሊቃነ ጳጳስት እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያሉበት አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋሙ ይታወሳል። የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ስራውን ከመጀመሩ በፊት፣ የማደራጃ መምሪያው ኃላፊ ሕግ እና ሥርዓት ባልጠበቀ መልኩ በማን አለብኝነት የማኅበሩን አገልግሎት የሚያደናቅፉ ተግባራትን በፍጥነት መፈጸማቸውን በመቀጠል ላይ ይገኛሉ:: ይህ ዓይነቱ በግለሰቦች የሚመራ አሠራር በቶሎ እርምት ካላገኘ ለአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ መስፋፋት ምቹ እድል ከመፍጠሩም በላይ ለቤተ ክርስቲያንቱ ህልውና  እጅግ አደገኛ ነው::

 

በማኅበሩ የአገልግሎት ዘመን የተለያዩ ፈተናዎች  የታዩ ሲሆን በእግዚአብሄር ጥበቃ እና በአባቶች ጸሎት  ማኅበሩን ለበለጠ አገልግሎት እያተጋው አልፏል:: ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት  መሳካት የምናስብ ሁላችን ይህንን በመረዳት ቤተክርስቲያን ከተደቀነባት የተቀነባበረ ፈተና ለመታደግ ከመቼውም በበለጠ ተግተን በማገልገልና ከእኛ የሚጠበቅብንን ሁሉ አስተዋጽኦ እንድናደርግ እያሳሰብን፤አሁንም ይህ ፈተና በእግዚአብሔር ቸርነት እንደሚያልፍ በማመን በጸሎት የቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎት እንድናስብ እና የመፍተሄው አካል እንድንሆን በእግዚአብሔር ስም እናሳስባለን::


የቅዱሳን አምላክ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት ከፈተና ይጠብቅ!!!

በማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል

 


Written By: host
Date Posted: 6/8/2011
Number of Views: 8330

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement