View in English alphabet 
 | Saturday, April 20, 2024 ..:: ስብከተ ወንጌል ::.. Register  Login
  

"ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን” (መዝ.46፥5)

(ዲ/ን ዮሐንስ ልሳነወርቅ)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማታ ማታ እየወጣ የሚያድርባት፣ሐሙስ ሌሊት በይሁዳ በኩል ለአይሁድ ተላልፎ የተሰጠባት፣ሐዋርያት ስለ ነገረ ምጽአት ጠይቀው የተረዱባት፣ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን ጌታችን ያረገባት ተራራ -ደብረ ዘይት። ዐርገ የሚለው የግዕዝ ግስ ዐረገ፣ወጣ በሚሉት የአማርኛ ቃላት የሚፈታ ሲሆን ዕርገት የሚለው ስምም ማረግን፣ መውጣትን፣አወጣጥን ያመለክታል።(አ.ኪ.ክ መ.ቃ)

አስቀድሞ ክቡር ዳዊት እንደተናገረው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱ እያዩት ወደ ሰማይ ዐርጓል። ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ፤ወእግዚእነ በቃለ ቀርን - እንዲል መዝ. 46፥5። ጌታችን በእውነት እንዳረገ ይኽም ሊታመን የማይችል እንዳልሆነ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ያስረዳል። ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሄደ፡ ዛሬ ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፤ሥጋው አልተለወጠምና። ሃይ.አበው ዘዮሐ.አፈ.ክፍል 13 ቁጥር 15

አንቃዕድዎተ ዐይን

ወዘንተ እንዘ ይብሎሙ ተለዐለ ወነሥአቶ ደመና ወዐርገ ሰማየ እንዘ እሙንቱ ይኔጽሩ ኀቤሁ ወተሠወረ እምአዕይንቲሆሙ። የሐዋ. 1፥9


አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ የወጣው በርህቀት(በመራቅ) እንጂ በርቀት (ቀ-ጠብቆ ይነበብ፤ረቂቅ በመሆን) አይደለም።ይኽም ማለት አስቀድሞ የተዋሐደውን ሥጋ አርቅቆ ፣ግዙፍነቱን አጥፍቶ ሳይሆን ከመለኮቱ ጋር በተዋሕዶ አንድ የሆነው ግዙፍ ሥጋ ግዝፈቱን ሳይለቅ ከዐይን በመራቅ፣ከፍ ከፍ በማለት፣ ወደ ሰማይ በመውጣት ነው።


በትምህርቱ የተጽናኑ፣በተአምራቱ የተማረኩ፣ ትዳራቸውን፣ ወላጆቻቸውን፣ ሃብታቸውን፣ ሥልጣናቸውን፣… የተዉለት ሐዋርያት ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር አብሮአቸው የቆየ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ሲለያቸው በናፍቆት ተይዘው ወደ ሰማይ ሲወጣ ትኩር ብለው ተመለከቱት። ያሳያቸውን ፍቅር፣ሑሩ ወመሃሩ በማለት ያዘዛቸውን አገልግሎት እንዴት እንደሚወጡት እያሰቡ ትኩር ብለው ተመለከቱት።


ነቢር በየማነ አብ


ነቢር በየማን -በቀኝ መቀመጥ በመጽሐፍ ቅዱስ አገባብ መሠረት ዕሪናን(በሥልጣን አንድ መሆንን) ያመለክታል።በመለኮቱ የእግዚአብሄር አብ ልጅ፣ በትስብእቱ(ሥጋን በመዋሐዱ) የማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በአብ ቀኝ ተቀመጠ።ማር.16፥19


ይኽ ስለ መለኮት የተነገረ አይደለም፤በመለኮቱስ ከአብ ሥልጣን ዝቅ ያለበት የዐይን ጥቅሻ ያህል ጊዜ የለምና።ነገር ግን ከተዋሕዶ በፊት ደካማ፣በደለኛ እና ውርደት ይስማማው የነበረው የእኛ ሥጋ ከተዋሕዶ በኋላ ጸጋን የሚያድል፣እውነተኛ ፍርድን የሚያደርግ፣ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ለመግለጽ ነው።


ዕርገተ ልቡና


ሲጸልዩም ሆነ ሲናገሩ፣ሲጾሙም ሆነ ሲመገቡ፣ሲሠሩም ሆነ ሲያርፉ የአምላክዎን ውለታ በማሰብ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ለምን ያህል ደቂቃቆች ያርጋሉ(ይመሰጣሉ)?


ሐዋርያት ጌታችን በአካለ ሥጋ አብሮአቸው እያለ ያዘዛቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ በመታመን አደራቸውን እንደተገበሩ ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ያለን ምዕመናንም ጌታችን በበረት በመወለድ፣የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ የሰጠንን የትሕትናን አደራ፤ወደ ግብፅ በመሰደድ፣በመስቀል በመቸንከር ያሳየንን መከራን የመቀበል አደራ፤አልአዛርን ከሙታን በማንሣት፣ራሱም በገዛ ሥልጣኑ ከሙታን በመነሣት የነገረንን ትንሣኤ ዘጉባኤን ተስፋ የማድረግ አደራ በሐሳባችን እያረግን ፣ልባችንን ከፍ ከፍ እያደረግን ክርስቲያናዊ ምግባራትን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረን በመያዝ ልንጠብቀው ይገባል።


በዕርገቱ ዕርገተ ልቡናን ያድለን።


Written By: host
Date Posted: 5/13/2010
Number of Views: 7797

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement