View in English alphabet 
 | Thursday, April 25, 2024 ..:: ስብከተ ወንጌል ::.. Register  Login
  

የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ

በቀሲስ ፋሲል አስረስ


“ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ” ማር. ፫፥፲፫-፲፮።

የተመረጡት አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ናቸው። ሐዋርያ ማለት ሖረ፣ ሄደ ካለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን የተላከ፣ ሂያጅ፣ ልዑክ ማለት ነው። ሐዋርያት በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠርተው እነርሱም ጥሪውን ተቀብለው እንደሔዱ እንረዳለን። ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው።


በዚህ አጭር ጽሑፍ የሚከተሉትን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች እንመለከታለን፦
• መጠራት
• ከእርሱ ጋር መኖር /ከእግዚአብሔር ጋር መኖር/
• ለመስበክ መላክ /ለአገልግሎት መላክ/


መጠራት

ፈታሔ በጽድቅ ኩናኔ በርትዕ ተብሎ የሚነገርለት አምላካችን እግዚአብሔር ድሃ ሃብታም፣ የተማረ ያልተማረ ሳይል ለሁሉም ጥሪ ያደርጋል። ጥሪውን የተቀበሉ በስሙ ያመኑት የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው የሚጠሩበት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ዮሐ. ፩፥፲፪። የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ በማለት ቅዱስ ማርቆስ እንደነገረን ከድሆች እነ ቅዱስ ጴጥሮስ /ማቴ. ፬፥፲፱-፳/፣ ከሃብታሞች እነ ቅዱስ ማቴዎስ /ማቴ. ፱፥፱/፣ ከተማሩ እነ ቅዱስ ናትናኤል /ዮሐ. ፩፥፵፮/፣ ካልተማሩ እነ ቅዱስ ዮሐንስና ያዕቆብ /ማቴ ፬፥፳፩-፳፪/ ተጠርተው ዓለምን ዙረው በማስተማር ተልዕኳቸውን ተወጥተዋል።

ዛሬም በተለያየ ሁኔታ የምንገኝ እኛን እግዚአብሔር ወደ ተራራ ይጠራናል። ተራራ መውጣት አድካሚ፣ አሰልቺና አስቸጋሪ ነው፤ ትዕግስትን ይጠይቃል፣ ጥንካሬን ይፈልጋል፣ ተራራው ላይ ሲደረስ ግን ፍጹም ዕረፍትና ደስታ አለ። የቀድሞ ድካም ይረሳል፣ አልፈነው የመጣነውን ዳገት በመመልከት ሐሴት እናደርጋለን። ወደ ተራራዋ ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ሲጀመርም እንዲሁ ነው። ከተራራው /ከቤተ ክርስቲያን/ ድምጽ ሰምተን ጉዞ ስንጀምር በርካታ እንቅፋቶች ይገጥሙናል። ለብዙዎች ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዳይቀርቡ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ወደ ተራራው መድረስ ከባድ አድርጎ መቁጠርና እንቅፋቶችን መቋቋም እንደማይችሉ ለራሳቸው ማሳመን ነው። ይህ ደግሞ ሜዳውን ገደል፣ ገደሉን ሜዳ፣ ጨለማውን ብርሃን፣ ብርሃኑን ጨለማ በማስመሰል ከእግዚአብሔር ቤት የሚያርቀን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን በኅሊናችን የሚስለው ማሳሳቻ ነው። የዝሙት መሰናከልን፣ የስርቆት እንቅፋትን፣ የተንኮል እሾህን ድል በማድረግ እውነተኛ ሰላምና ዕረፍት ወደምናገኝባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ጥሪን ከማክበር በተጨማሪ ከኃጢአት ዝናብ ወደምንጠለልበት ቦታ ማምራት ነው። ከመቅበዝበዝ ድኖ የነፍስ እረኛ ወደሚገኝበት መሄድ ነው። “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤  በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።” ፩ኛ ጴጥ. ፪፥፳፩-፳፭።

ከእርሱ ጋር መኖር /ከእግዚአብሔር ጋር መኖር/
 

በቤተ ክርስቲያን መኖር ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው። እግዚአብሔር የነገሥታት ንጉሥ፣ የገዢዎች ገዢ፣ የኃያላን ሁሉ ኀያል የሁሉም ፈጣሪ ነው። ለመንግሥቱ ወሰን ገደብ የሌለው ሁሉን ማድረግ ከሚችል እግዚአብሔር ጋር ከመኖር የበለጠ ምንም ትልቅ ነገር የለም። ልበ አምላክ ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ያስተዳደረ ታላቅ ሰው ነው፤ ይልቁንም እግዚአብሔር እንደ ልቤ ብሎ ተናግሮለታል። ዳዊት ከእግዚአብሔር ጋር የመኖር ጥቅሙን ሲናገር “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝ የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል። ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም” መዝ. ፳፪፥፩-፬።

 

በዚህ ውጣ ውረድ በበዛበት ዓለም የምንኖር ሰዎች ምንጊዜም የእግዚአብሔር ጥበቃ ያስፈልገናል። ዓለም በሰላም እጦት ስትጨነቅ ማየት ከተጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል። በሰለጠነው ዓለም ሰዎች ተስፋ በማጣት ሲቅበዘበዙ በጭንቀት ተወጥረው የሚሰሩትን ሲያጡ መረጋጋት ጠፍቶባቸው በስቃይ ሲኖሩ ማየት የዕለት ተዕለት ክስተት ሆኗል። ትዳርን እንደ እስር ቤት የሚቆጥሩ ወገኖች መበራከትና ዘመናቸውን ደስታ በሌለው ብቸኝነት የሚገፉ ሰዎች ቁጥር መጨመር መተሳሰብ፣ መደማመጥና መግባባት ጠፍቶ እንደ ደባል የሚኖሩ ባለትዳሮች መታየታቸው ከእግዚአብሔር ጋር ያለመኖር ያስከተለው ውጤት ነው። ጥረው ደክመው ያገኙትን ደስ ብሏቸው የማይበሉ በረከት የሌለው ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ባለመኖራቸው የተፈጠረ ችግር ነው። ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸው ለኅሊናቸው እረፍት ለአእምሯቸው ሰላም ያጡ ሰዎች ምክንያቱ አሁንም ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የላላ መሆኑ ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ማቴ. ፲፩፥፳፰። ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ ከእርሱም ጋር ስንቀርብ የከበደን ሸክም ሁሉ ይቀልልናል። የኃጢአት ሸክም ያለብን መግደላዊት ማርያምን እናስታውስ፤ ወደ እርሱ በመቅረቧ ኃጢአቷ ተወገደላት። ሉቃ. ፰፥፪። የበሽታ ሸክም ያለብን እነ መጽአጉን እንመልከት የሠላሳ ስምንት ዓመት ደዌ በደቂቃ ንግግር ተወግዷል። ዮሐ. ፭፥፪-፱። የችግር ሸክም ያለብን በአምስት እንጀራ በሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ህዝብ እንዳጠገበ እናስብ። ማቴ. ፲፭፥፴፬-፴፱። ከእግዚአብሔር ጋር ስንኖር የምናገኘው ጥሩ ነገር እንጂ የምናጣው ነገር የለም። ከሰይጣን ጋር /በዓለም/ ሆነን ከምናገኘው ከእግዚአብሔር ጋር ሆነን የምናገኘው ይሻለናል፤ እግዚአብሔር የሚበጀንን አይነሳንምና።

ለመስበክ መላክ /ለአገልግሎት መላክ/
 

ሐዋርያት ወደ ተራራ ከወጡ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር ኖረው ነው ለአገልግሎት የተሰማሩት። የቃሉን ትምህርት ሰምተው፣ የእጁን ተዓምራት አይተው፣ በዋለበት ውለው፣ በአደረበት አድረው ለኃላፊነት በቅተዋል። ይህን ዓለም በወንጌል ጨውነት አጣፍጠዋል። “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” /ማቴ. ፳፰፥፲፱/ በተባሉት መሠረት ዓለምን በዕጣ በመከፋፈል የእግዚአብሔርን አምላክነት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን  አስተምረዋል። “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ” /ማቴ. ፲፥፴፪/ የሚለውን አምላካዊ ቃል እያሰቡ የሚጠፋውን ሳይሆን ዘለዓለማዊውን በመምረጥ ማንንም ሳይፈሩና ሳያፍሩ እውነት የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ሰብከዋል።

ዛሬም ጥሪውን አክብረን በተራራዋ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተገኘን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል እየተመገብን በመኖር በቃሉ ከረሰረስን በኋላ ሲገባን እግዚአብሔር በሚያሰማራን የአገልግሎት መስክ እንደጸጋችን ማገልገል ይጠበቅብናል። የቤተ ክርስቲያን  የአገልግሎት ዘርፉ ብዙ ነው። ወንበር ከማስተካከልና የጽዳት አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ የሚከናወኑ ተግባራት በእግዚአብሔር ቤት መኖርንና ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን የሚጠይቁ ናቸው።

እንግዲህ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጸንቶ ለመኖር በአገልግሎታችን በርትተን ለመጨረሻው የድል አክሊል ለመብቃት የሚከተሉትን ልናደርግ ይገባናል፦

በጸሎት መበርታት
 

ቅዱስ ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን ሊቅ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልዩ ጥሪ የወንጌል ሰባኪና በመጽሐፍ ቅዱስ አሥራ አራት መልዕክታትን በመጻፍ የሚታወቅ ነው። ይህ ሐዋርያ ተሰሎንቄ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በላከው ክታቡ የተሰሎንቄ ሰዎች እንዲጸልዩለት ጠይቋል። ፩ኛ ተሰ. ፭፥፳፭። የሮም ሰዎችንም ለእግዚአብሔር የተመቸ ሕይወት እንዲኖራቸው ከመከረና ካስጠነቀቀ በኋላ በጸሎት እንዲጸኑ ነግሯቸዋል። ሮሜ. ፲፪፥፲፪።

በተራራ በቤተ ክርስቲያን የሚኖር ሁልጊዜም ይጸልያል ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገርበት ቋንቋው ስለሆነ ነው። በዚህም ብርታትንና ጥንካሬን ይጎናጸፋል፤ ለምንና ማንን እንደሚያገለግል ያውቃል። የእግዚአብሔር ሰው ከሌላው የሚለየው እግዚአብሔርን ማነጋገር መቻሉ ነው፤ እርሱም ጸሎት ነው። የሚጸልይ ሰው ሃይማኖት ያለው ነውና። የጎደለብንን እንዲሞላ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ እንዲጠቀምብን ከፈለግን ሳናቋርጥ በትጋት ልንጸልይ ያስፈልጋል። ሐዋ. ሥራ ፪፥፩-፬።

በፈተና መጽናት
 

መንፈሳዊ አገልግሎት /ክርስትና ሕይወት/ የጦር ሜዳ እንጂ የምቾት አዳራሽ አይደለም። በጉዟችን ልዩ ልዩ ፈተና ሊገጥመን ይችላል። ለፈተናው ሳንንበረከክ ይልቁንም በእምነታችን የሚመጣብንን ፈተና እንደሙሉ ደስታ በመቁጠር ልንጠነክር ይገባናል። ያዕ. ፩፥፪። በሃይማኖት ስንኖር ውጊያው ከደምና ከሥጋ ጋር ባለመሆኑ በመከራ በመታገስ ጸንተን ልንቆም ጠላታችን ሰይጣንን ልናሳፍር ግድ ይለናል። ኤፌ. ፮፥፲፪፤ ሮሜ. ፲፪፥፲፪።

ከቃለ እግዚአብሔር አለመለየት
 

የሰው ልጅ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነግሮናል። ማቴ. ፬፥፬። አገልጋይ ምንጊዜም ቢሆን ከቃለ እግዚአብሔር ሊለይ አይገባውም። አስተማሪም ሆነ ተማሪ፣ አገልጋይም ሆነ ተገልጋይ፣ አማኝ የሆነ ሀሉ ዘወትር ከቃሉ ጋር ሊኖር ያስፈልገዋል። የእግዚአብሔር ቃል ዘወትር አዲስ ነው። የጉዞ ስንቃችን፣ የእውቀት ብርሃናችን፣ የጽድቅ መንገዳችን የእግዚአብሔር ቃል ነው። አበው “ከቃለ እግዚአብሔር የተለየ ክርስቲያንና ከባህር የወጣ ዓሳ አንድ ናቸው” ይላሉ፤ ከባህር የወጣ ዓሣ ሕይወት እንደሌለው ሁሉ ከቃለ እግዚአብሔር የተለየ ክርስቲያንም ሕይወት የለውም። የሚጠቅመንና የማይጠቅመንን የምንለይበት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምንረዳበት ቁልፍ ያለው በእግዚአብሔር ቃል ነው። ምንም የምናውቅ ቢመስለንም እንኳን ገና ብዙ ልናውቅ የሚገባን እንዳለ ቅዱስ  ጳውሎስ እንዲህ በማለት ገልጾልናል። “ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም” ፩ኛ ቆሮ. ፰፥፪።

ከላይ እንደተገለጸው ከገማልያል እግር ሥር ቁጭ ብሎ በመማር የብሉይ ኪዳን ሊቅ የሆነው ከራሱ ከክርስቶስ በደረሰው አስደንጋጭ ጥሪ ወንጌላዊ የሆነውና በስብከት ሕይወቱን ያሳለፈው ምሑርና ሐዋርያዊ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ከቃለ እግዚአብሔር አልተለየም ነበር። መጻሕፍትን ይመረምርም ነበር። የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን ስትመጣ በጢሮአኖ ከአክርኛ ዘንድ የተውኩትን በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ በማለት አዝዞታል። ቅዱስ ጳውሎስ ሌላውን እያስተማረ ራሱንም በቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምር እንደነበርና ከቃለ እግዚአብሔር አለመለየቱን እንረዳለን። እኛም ሳንወደው ወዶን የጠራን አምላካችንን ስናገለግል ከቃለ እግዚአብሔር ባለመለየት ከሆነ አገልግሎታችን በፍቅርና በትጋት ይሆንልናል።


በትህትና መኖር

 

አንድ የእግዚአብሔር ሰው የሚያስደንቅ ዓለምን ያስጨበጨበና ያስገረመ ተግባር ቢፈጽም ይህ ከእግዚአብሔር ነው እኔ ብቻዬን ምንም ማድረግ አልችልም ካላለ አወዳደቁ ይከፋል። የትኛውንም ያህል ብንበረታ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ማወቅ አለብን፤ በሥራችንም እግዚአብሔር ከፍ ከፍ እንዲል እንጂ የራሳችንን ዝናና ታላቅነት ለማንጸባረቅ አለመሞከር አዋቂነት ነው። በቃለ እግዚአብሔር መብሰላችን የሚረጋገጠው ትህትናን ገንዘብ ስናደርግ ነው። ፍሬ ያፈራ ዛፍ ዘንበል ይላል፤ በእግዚአብሔር ቃል ሙሉ የሆነ ሰው ራሱን ዝቅ ያደርጋል /ዘንበል ይላል/ ሙሉ  ፍሬ አለውና።

መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው ነቢይ ነው። በዚህ ላይ በመልአከ ብስራት የተወለደ፣ በበርሃ ያደገና እግዚአብሔር ወልድን ለማጥመቅ የተመረጠ ታላቅ ሰው ነው። አንተ ክርስቶስ ነህን ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ሲመልስ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ /ማቴ. ፫፥፲፩/ በማለት በትህትና ተናግሯል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ጭንጋፍ ነኝ ከሐዋርያት የማንስ ነኝ በማለት ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና እንደተናገረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ሉቃ. ፭፥፰፤ ኤፌ. ፫፥፰-፱፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፰።

ትህትናን ገንዘብ ያደረገ ክርስቲያን መሳሪያ ከታጠቀ ወታደር ይበልጣል ጠላት ሰይጣንን ድል ማድረግ ይችላልና። በተጠራንበት በተራራ በተመሰለች ቤተ ክርስቲያን ጸንተን ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን በአገልግሎት ጠንክረን ስሙን ቀድሰን ክብሩን ለመውረስ ያብቃን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ምንጭ፦ ሐመረ ኖኅ ኤሌክትሮኒክስ መጽሔት ፯ኛ ዓመት ቁጥር ፩ ታኅሣሥ ፳፻፫ ዓ.ም.


Written By: admin
Date Posted: 7/3/2011
Number of Views: 8071

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement