የከምባታ፣ ሐድያ፣ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የነበሩት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዐረፉ፡፡
ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በደረሰባቸው ሕመም ሳቢያ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 13 ቀን 2002 ዓ.ም ዐርፈዋል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸው ሰኔ 15 ቀን 2002 ዓ.ም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት አባቶችና ምእመናን በተገኙበት በምሁር ኢየሱስ ገዳም ተፈጽሟል፡፡ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ያስተዳድሩት በነበረው ሀገረ ስብከት ውስጥ በሚገኘው እዣና ወለኔ ወረዳ /ምሁር ኢየሱስ ገዳም አካባቢ/ ከአባታቸው ከመምሬ ክንፈ ሚካኤልና ከእናታቸው ከወ/ሮ አስካለ ማርያም በ1951 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የምሁር ኢየሱስ ገዳም ቄሰ ገበዝ የነበሩት አባታችው በዚያው ፊደልና የቁጥር ትምህርት አስተማሯቸው፡፡