በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
“ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን”
/ጸሎተ ሃይማኖት/
ጥምቀተ ክርስቶስ
ለጌታችን ሠላሳ ዓመት ሊሆነው ስድስት ወር ሲቀረው ፣ የሊቀ ካህናቱ የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ ከምድረ በዳ ወጥቶ ማስተማር ጀመረ:: ይህንንም ትምህርት የጀመረው ከፈጣሪው ባገኘው መልእክት ነው:: ሉቃ ፫፥፩ ዮሐንስም ከቆሮንቶስ ምድረ በዳ ወጥቶ በዮርዳኖስ ዙርያ “መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ በማስተማር የንስሐን ጥምቀት ማጥመቅ ጀመረ :: ሉቃ ፫፥፫ ሕዝቡም ትምህርቱን በመቀበል ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ በንስሐ ጥምቀት ይጠመቁ ነበር:: ማቴ ፫፥፫ የትምህርቱን እውነተኛነት ባወቁ ጊዜ ዮሐንስን ክርስቶስ ነው ብለው ጠረጠሩ:: ሉቃ ፫፥፲፭ ዮሐንስም እንዲህ ሲል እውነቱን ነገራቸው " እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።" ዮሐ ፩፥፳