View in English alphabet 
 | Monday, April 29, 2024 ..:: ዜናዎች ::.. Register  Login
  

የአሜሪካ ማዕከል 13ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ፤ የማኅበሩን አገልግሎት ለማጠናከር ዕቅዶችን አጸደቀ

  •   የተጀመረውን የማኅበሩን ሕንጻ ለማስፈጸም የሚሆን ከሐምሳ ስድስት ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ፤
(አትላንታ፤ ጆርጂያ)፦ ባለፈው ቅዳሜ እና እሑድ ማለትም ግንቦት 20 እና 21/ 2003 ዓ.ም ሲካሔድ የቆየው በማ/ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ እሑድም ቀጥሎ በመዋል ውሳኔዎችን በማሳለፍ እና የ2004 ዓ.ምሕረትን ዕቅድ በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

ለ13ኛ ጊዜ በተካሔደው እና የዲሲ እና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አበው፣ ዲያቆናት ወንድሞች፣ የማኅበሩ አባላት ወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የተካሔደው የዕለተ እሑድ ጉባኤ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚተላለፍ ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም ጉዳይ በሰፊው ተወያይቷል። የተዋሕዶ ድምጽ/ ድምፀ ተዋሕዶ በመባል ስለተሰየመው እና በሳምንት ሁለት ቀን ወደ ኢትዮጵያ መተላለፍ ስለሚጀምረው የሬዲዮ ጣቢያ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አባላት ያጠኑት ጥልቅ ጥናት ከቀረበ በኋላ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
 ማኅበሩ ከዚህ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል የሬዲዮ ዝግጅት በአጭር ሞገድ ሲያስተላልፍ ቆይቶ በሥርጭቱ የሞገድ ጥራት ማነስ ምክንያት ዝግጅቱን በማቋረጥ ጉዳዩን ሲያጠና ቆይቷል። ከረዥም ጊዜ ጥናት በኋላ በተሻለ የሬዲዮ ሞገስ ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ቴክኒካዊ እና ሌሎች መሰል ዝግጅቶችን ሲያከናውን ቆይቶ አሁን ዝግጅቱን ለመጀመር ከመጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱን ማኅበሩአረጋግጧል። ለዚህ አገልግሎት ሁነኛ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኘው የአሜሪካ ማዕከል አባላትም ስለ ሬዲዮው የተደረገውን ገለጻ በመከታተል ከእነርሱ የሚፈለገውን ነገር በመቀበልና ለተግባራዊነቱ ውሳኔ በማለፍ አጀንዳው ተጠናቋል።
 የ2004 ዓ.ምሕረትን የአገልግሎት ዕቅድ ያደመጠው ዕከሉጠቅላላ ጉባኤ በመጪው ዓመት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ ለኢትዮጵያ” የሚል ዐውደ ርእይ ይካሔድ ዘንድ የቀረበውን ዕቅድ እንዲሁም ስለ ሕጻናት ትምህርት፣ ስለ ስብከተ ወንጌል፣ ስለ ድረ ገጾች መጠናከር፣ በአሜሪካ የሚገኙትን አህጉረ ስብከት ስለመርዳት፣ ቃለ እግዚአብሔርን በመጻሕፍት፣ በጋዜጦችና በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች ስለማሰራጨት፣ ሰንበት ት/ቤቶችን ስለመርዳት ወዘተ በጠቅላላው በየአገልግሎት ክፍሎቹ የቀረቡለት ዕቅዶች ላይ ተወያይቶ አጽድቋቸዋል።
 ከማዕከሉ አገልግሎት ክፍሎች በተጨማሪ ማዕከሉ ባሉት 11 “ቀጣና ማዕከላት” የተዘጋጁትን ዕቅዶች ተመልክቶ ማሻሻዎችን በማድረግ አጽድቋቸዋል። የ2003 ዓ/ምሕረት አገልግሎትን በተመለከተ የኦዲት እና ኢኒስፔክሽንን ሪፖርት አድምጧል። በዚህም ድክመት በታየባቸው የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ጉባኤው ለግሷል።
በዕለቱም በእንግድነት ከአዲስ አበባ በመጡት በመልአከ ሰላም ጌታቸው ደጀኔ ትምህርት ከመሰጠቱም በላይ የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መልእክትም በተወካዩዋ አማካይነት በንባብ ተሰምቷል።
 ጉባኤውን በታላቅ ንቃት የተከታተሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃምም በሰጡት ቃለ ምዕዳን በስጋት እና በፍርሃት መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች ከመሥራት ወደ ኋላ ማለት እንደማይገባ መክረው ማዕከሉ የጀመረውን አገልግሎት አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ሰጥተዋል። ጉባኤው በሚከናወንባቸው ጊዜያት በሙሉ እንደማይለዩ፣ ጉዳዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እስከሆነ ድረስ በተልዕኮው ከማኅበሩጎን እንደሚቆሙበማስረዳት ጉባኤተኛውን አበረታተዋል።
 የዚህ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ ሲጠናቀቅም 14ኛውን ጉባኤ በዴንቨር ለማካሄድ ባለተራው ጽዋውን ሲወስድ የሜኔሶታ ቀ/ማዕከል በበኩሉ 15ኛውን ለማዘጋጀት “ማነህ ባለ ሣምንት” የሚለውን ጥሪ ተቀብሏል። “ያብጽዐነ አመ ከመ ዮም …” በሚለው ተስፋ አዘል መዝሙር በቀነ ቀጠሮ ጉባኤተኛው ስብሰባውን አጠናቆ ወደየመጣበት በሰላም ተመልሷል።  

Written By: admin
Date Posted: 5/31/2011
Number of Views: 4750

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement