View in English alphabet 
 | Thursday, May 2, 2024 ..:: ዜናዎች ::.. Register  Login
  

ዜና ዝክረ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ

“የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው” በሚለው የቅዱስ ዳዊት መዝሙር መነሻነት ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም. “ዝክረ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ” በሚል ርዕስ ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ያረፉበት ፳፩ኛ ዓመት (ሐምሌ ፳፪) በልዩ  መርሐ ግብር ታስቦ ውሏል። በማ/ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል የትምህርት እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል የተዘጋጀው ይኸው የመታሰቢያ ዝግጅት ሁለት ሰዓት ተኩል የፈጀ የስልክ መርሐ ግብር ሲሆን በአሜሪካ ማዕከል ውስጥ ባሉ አስራ አንድ ቀጣና ማዕከላት የሚገኙ የማኅበሩ አባላትና ምዕመናን ተሳትፈውበታል::  በዝግጅቱ ላይ የብፁዕ አባታችን አጭር የሕይወት  ታሪክ ከተነበበ በኋላ  እና ብፁዕነታቸው ባቋቋሙት በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሰልጠኛ በመግባት ከእግራቸው ሥር ቁጭ ብለው ወንጌልን በሕይወት ከተማሩት፣ የአባታችንን የሕይወት እና የአገልግሎት ፍሬዎች በዓይናቸው ከተመለከቱት እና መጽሐፎቻቸውን በጥልቀት ካነበቡት አባቶች እና ወንድሞች መካከል መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ፣ መልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን እና ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ ምስክርነታቸውን ጥልቅ በሆነ የፍቅር ስሜት ገልጸዋል።

መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ብፁዕነታቸው በማኅበረ ቅዱሳን ምሥረታ የነበራቸው ሚና እና ለወጣቱ የነበራቸው ትኩረት ምን እንደሚመስል ሲገልጹ፤ በ፲፱፻፸፬ ዓ.ም. የ፴፫ኛው ዙር የዝዋይ ካህናት ማሰልጠኛ ሰልጣኝ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚያውቋቸው እና ትውልዱን ለመለወጥ አቅደው ለትምህርት ከሄዱበት ከውጭ አገር የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብለው ትምህርታቸውን አቋርጠው የመጡ ታላቅ አባት እንደነበሩ፤ ትምህርተ ወንጌልን ዘርግተው፣ ሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅተው መጽሐፍ ጽፈው ያስተምሩ እንደነበረ፤ ካህናት አባቶችም ከየወረዳው እና ሀገረ ስብከት እየተወከሉ እየመጡ መሰልጠናቸውን በተለይም ለሕጻናት የተለየ ትኩረት ሰጥተው ያለ ምንም በጀት እየለመኑ ያሳድጓቸው እንደነበር፤ የዕለቱን ወንጌል ሁሉም ሰልጣኝ በቃሉ እንዲይዝ ማድረጋቸውን፤ ራስን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት በልምድ መኖር ብቻ ሳይሆን በሕይወትም ጭምር በመኖር ያሳዩ አባት መሆናቸውን፤ ካሳደጓቸው እና ካስተማሯቸው መካከል ለክብረ ጵጵስና እና ሌሎችም ታላላቅ የአገልግሎት ደረጃዎች የደረሱ እንደሚገኙ፤ ብፁዕ አባታችን ለወጣቱ እና ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከነበራቸው ከፍተኛ ትኩረት የተነሣ ወጣቱ ላይ የማይጠፋ ፍቅር ያሳደሩ አባት መሆናቸውን በተለይ ከ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. እስከ ፲፱፻፹ ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲ ይካሔድ የነበረውን የጽዋ መርሐ ግብርና መንፈሳዊ አገልግሎት በቅርብ ይከታተሉ እንደነበር፣ በ፲፱፻፹ ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምረቃ በዓል ላይ ከሌሎች ሦስት ብፁዓን አባቶች ጋር ተገኝተው እንደባረኩና ለቀጣዩ ትውልድ ቤተ ክርስቲያንን በተረካቢነት አደራ እንደሰጡ፣ በተለያየ ጊዜ በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ከገቡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተጨማሪ እስካረፉበት ጊዜ ድረስ ለሦስት ዓመታት ፷፱ ተማሪዎችን በተለየ ትኩረት እንዲሠለጥኑ ማድረጋቸው /በ፲፱፻፹ ዓ.ም. ፲፪ ተማሪዎችን፣ በ፲፱፻፹፩ ዓ.ም. ፲፪ ተማሪዎችን፣ በ፲፱፻፹፪ ዓ.ም. ፵፭ ተማሪዎችን/ እና ይህም ለማኅበረ ቅዱሳን ምሥረታ ዋና ምክንያት እንደሆነ፤ እንደዚሁም ብፁዕነታቸው ሰውን ከሰው የማያበላልጡ፣ ቋንቋና የትውልድ ቦታ የማይጠይቁ፣ ስሕተትን በግልጽ የሚያርሙ እንጂ ሐሜታን የማይወዱ ልዩ አባት እንደነበሩ በሰፊው አብራርተዋል:: ለመነኮሳት እና ብፁዓን አባቶች የተለየ ክብር ይሰጡ እንደነበር እና በአገልግሎት ውስጥ ብዙ ቀዳዳ በዘርፈ ብዙ አገልግሎት የደፈኑ እጅግ ታላቅ አባት መሆናቸውን ገልጸዋል።
 
መልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ በበኩላቸው የብፁዕ አባታችን የአገልግሎት የትኩረት አቅጣጫ ምን እንደነበረ ሲገልጹ፤ በ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. በዝዋይ የካህናት ማሰልጠኛ ገዳም ለሥልጠና በሄዱበት ወቅት የገጠማቸውን የተለየ መንፈሳዊ ስሜት እና ሥልጠናው እና አገልግሎቱ በወንጌል እና በጠንካራ ጸሎት ላይ የተመሠረተ እንደነበረ እና በተለይም የሚሰበከው ወንጌል ወደ ሕይወት የመለወጥ እውቀት የሚገኝበት ቦታ እንደነበረ አስታውሰዋል።  ብፁዕ አባታችን የብህትውና (የጸሎት፣ የስግደት እና የምጽዋት)፣ የዕውቀት (ቢጽፉ እና ቢናገሩ የማያልቅባቸው) እና የዓላማ ሀብታት እንደነበሯቸው፤ ለዩኒቨርሲቲ እና ለተማረ ሰው የነበራቸው ትኩረት ልዩ ስለነበር እስካሁን የሚታዩ  ብዙ ፍሬዎች ማፍራቱን፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አባላት ያሉት ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ምሳሌ ሊቆጠር እንደሚችል አብራርተዋል። በካህናት ማሰልጠኛው የሰለጠኑ ካህናት እና ሕጻናት ዛሬ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብርሃን እየሆኑ መሆናቸውን፤ ብፁዕ አባታችን ሳይጠገቡ ድንገት የጠፉ፣ በጨለማ ውስጥ ብርሃን እየሰጠ እንደነበረ እንደሚያጓጓ ሻማ እንደሆኑ አስረድተዋል።

በ፲፱፹፪ ዓ.ም. በዝዋይ ገዳም ገብቶ የተማረው ወንድማችን ዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ በበኩሉ በ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተነሡት አባቶች መካከል ትተውት ባለፉት መልካም አሻራ ልናስታውሳቸው የሚገቡ ታላቅ አባት መሆናቸውን ገልጿል። በካህናቱም፣ የአስኳላ ትምህርት በተማረውም/ ባልተማረውም እኩል ተቀባይነት የነበራቸው የተለዩ አባት እንደነበሩ፣ እስካሁን እንደ ብፁዕ አባታችን በ፶ ዓመት ውስጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ትልቅ የአገልግሎት አሻራ የጣለ አባት እንደሌለ። በቃላቸው ትምህርት፣ በመጽሐፋቸው፣ ገዳም በማስፋፋታቸው የቅድስና ማዕረግ የሚገባቸው አባት እንደሆኑ፤ በቤተ ክርስቲያናችን የዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ታላቅ እርሾ የጣሉ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በዓለም የቱ ጋር እንዳለች ትክክለኛ ቦታዋን ያሳዩ አባት መሆናቸውን፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በመቅረብ ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ያስተማሩ እንደነበሩ፤ መጽሐፎቻቸውም በበቂ መረጃ የተደገፈ እንደሆነ እና በአጠቃላይ ብፁዕ አባታችን የ፳ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ አባት እንደሆኑ በመግለጽ ማብራሪያውን ደምድሟል።

በመጨረሻም ብፁዕ አባታችን ካዘጋጇቸው ስምንት መጻሕፍት መካከል  ለሕትመት ያልበቁ አምስቱ መጽሐፎቻቸው የሚታተሙበት መንገድ እንዲመቻች፣ ብፁዕ አባታችን ያቋቋሙት የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ካህናት ማሰልጠኛ ትኩረት ተሰጥቶት በግልም ሆነ በማኅበር ድጋፍ እንዲደረግለት፣ ትምህርቶቻቸውን እና አገልግሎታቸውን የሚያሳዩ በድምጽም ሆነ በምስል የተዘጋጁ መረጃዎች እንዲሰባሰቡ እንዲሁም በዚሁ በሰሜን አሜሪካ ተመሳሳይ የሆነ የዝዋይ ዓይነት የካህናት ማሰልጠኛ መቋቋም የሚቻልበት መንገድ እየተጠና እንዲቆይ ከተለያዩ  አባላት እና ምስክርነት ከሰጡት አባቶች አስተያየቶች ተሰጥተው የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።
   
ዘገባ፦ በትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል የመዝሙርና ኪነጥበባት ንዑስ ክፍል፣ ሐምሌ ፳፮ ቀን ፳፻፫  ዓ.ም.


Written By: admin
Date Posted: 8/8/2011
Number of Views: 4865

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement