View in English alphabet 
 | Thursday, May 2, 2024 ..:: ዜናዎች ::.. Register  Login
  

መግለጫ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከል የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል አስተባባሪነት እና በኮሎምበስ፣ ኦሀዮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ አስተናጋጅነት በሰሜን አሜሪካና ካናዳ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ የሚያገለግሉ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ካህናት ሰባክያነ ወንጌልና መዘምራን የተሳተፉበት  ዓርብ ጥቅምት ፲፯ ቀን  ፳፻፬ ዓ/ም (October 28, 2011) እና ቅዳሜ ጥቅምት ፲፰ ቀን  ፳፻፬ ዓ/ም (October 29, 2011) የተካሄደው የምክክር ጉባኤ የጋራ መግለጫ


“አንትሙሰ ሰማዕቱ ለዝንቱ ነገር”  ሉቃ ፳፬፥፲፰

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊትና ሐዋርያዊት እንደመሆኗ መጠን የበርካታ መንፈሳዊ  ሀብት ባለቤት ናት። ይህች ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓቷ  ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ስትተላለፍ ቆይታ ለእኛ ደርሳለች። የቤተክርስቲያን እምነት ሥርዓትና ትውፊት ተጠብቆ ለዚህ ትውልድ የደረሰው በየዘመኑ የነበሩት ክርስቲያኖች በከፈሉት መስዋዕትነት ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር አስገድዷቸው ፤ የተሰጣቸው መንፈሳዊ ኃላፊነት እና አደራ አስጨንቋቸው ክርስትና እውነትን በመመስከር የሚገኝ ሕይወትና ክብር መሆኑን ተረድተው  ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ቤተክርስቲያንን ያገለገሉ ሊቃውንተ በፈጸሙት ገድል፤ ምእመናን ባሳዩት ታማኝነትና ትጋት  ዛሬ ሁላችንም ለምንኮራበት የታሪክና የመንፈሳዊ ሀብት ባለቤት ለመሆን በቅተናል።
 
ይህንን የመሰለ ታሪክና መንፈሳዊ ሀብት ያላት ቤተክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የውስጥና የውጭ ችግሮች ተከባለች። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየው ዘርፈ ብዙ ችግር እየተቃለለ ይሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም እየተባባሰ በመሄዱ ብዙ ካህናትና ምእመናን በማዘን ላይ ይገኛሉ። ይህንን እየተከሰተ ያለውን ዘርፈ ብዙ የቤተክርስቲያን ችግር በተለይም በፕሮቴስታንት የሚመራው የተሐድሶ እንቅስቃሴ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመነጋገርና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማግኘት በኢ/ኦ/ተ ቤተክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በሰሜን አሜሪካ ማዕከል የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል በተዘጋጀ ዐውደ ጥናት ጥቅምት 17 እና 18 2004 ዓ. ም በኮሎምበስ ኦሃዮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል የኢ/ኦ/ተ ቤተክርስቲያን ተካሄዷል። በዚህ ዐውደ ጥናት ላይ በተለያዩ  የአሜሪካ ግዛቶችና ካናዳ ውስጥ የሚያገለግሉ በጠቅላላ 30 የሚሆኑ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ካህናት: ሰባክያነ ወንጌልና መዘምራን ተገኝተዋል ።

በወጣው መርሐግብር መሠረትም ከዚህ የሚከተሉት ጥናታዊ ጽሑፎች በተለያዩ ካህናት የቀረቡ ሲሆን:-
  1. በፕሮቴስታንት የሚመራው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ምንነትና አሁን እያስከተለው ያለው ችግር: በቀሲስ ዶክተር መስፍን ተገኝ።
  2. ይኸው የተሐድሶ ቡድን በሀገራችን በኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት እያደረሰ ስላለው ከፍተኛ ጥፋት የአይን ምስክር በመሆን በቅርቡ ከኢትዮጵያ በተመለሱት:  በመልአከ ሣሌም አባ ገብረኪዳን እጅጉ።
  3. ወቅታዊ የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው በሚል --- በዲ/ን ኤፍሬም እሸቴ።
  4. የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች በሚያቀርቧቸው የክህደት ትምህርቶች ላይ የቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ትክክለኛ ትምህርት የሚያስረዳና ለመናፍቃኑ ጥያቄ ምላሽ የሚሆን ገለጻ በሚከተሉት መምህራን በሰፊው ቀርቧል።
    4.1. ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ:- በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው።
    4.2. ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም:- በቀሲስ ብርሃኑ ጎበና።
    4.2. ስለ ቅዱሳት መጻሕፍቶቻችን:- በመልአከ ሕይወት ቀሲስ እርገተ ቃል ይልማ እና በመልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን። 
በእነዚህ በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻነት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር እየተከሰተባት ያለው ችግር በጉባዔው ተሳታፊዎች ተነስቶ ጥልቅ ውይይት ተደርጎበታል። በውይይቱም ውስጥ ከተነሱት ሀሳቦች መካከል
  • የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን እምነትና ሥርዓት ለመለወጥና ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ወደ ፕሮቴስታንት ቤተእምነት ለመቀየር እየተደረገ ያለውን የድፍረት እንቅስቃሴ እጅግ ከባድና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የደረሰ መሆኑን ጉባኤው በጽኑ ተገንዝቧል።
  • ይህ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጆች (መናፍቃን) የቤተክርስቲያኒቱ የጀርባ አጥንትና መሠረት ሆነው ሊቃውንት የሚፈልቁበትን አብያተ ክርስቲያናት: አብነት ት/ቤቶችና ገዳማትን ለመበረዝና ለማጥፋት ሥር የሰደደ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ መሆናቸውን መስማት ፍጹም የህሊና እረፍት የሚያሰጣ በመሆኑ አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ተወስኗል።
  • እያንዳንዱ ሰው የፈለገውንና የመረጠውን ሃይማኖት በነጻነት መከተል እንደሚችል የታወቀ ቢሆንም የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች (መናፍቃን) ግን የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ከሆኑት ካህናት መነኮሳት: ዲያቆናትና መናንያን ጋራ እየተመሳሰሉ አርአያ ክህነትን በሚያስነቅፉ ቦታዎች በመገኘት : ከቤተክርስቲያኒቱ ትምህርትና ሥርዓት ውጭ የሆኑ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራትን በመፈጸም በጎችን ከእረኞች የማለያየትና የማራራቅ : የቤተክርስቲያናችንን መልካም ገጽታ የማጉደፍ ሥራ በስፋት እየሠሩ መሆኑን ጉባኤው ተገንዝቦ: በሚመለከታቸው አካላት በዚህ የጥፋት ተግባር ላይ የተሰማሩትን ሰዎች በሕግ ተጠያቂ የሚያደርግ አሠራር መተግበር እንደሚገባው ታምኖበታል።
  • የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች ይህንን ያህል ጉልበት አግኝተው በይፋ ለመንቀሳቀስ የቻሉት ቤተክርስቲያናችን በገጠማት ዘርፈ ብዙ ችግርና ይህ የተሐድሶ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ በሚጥሩ:  በውስጧ ሠርገው ሊገቡ በቻሉ ኃላፊዎች እና በይሁዳ ግብር በሚሄዱ ሰዎች ሳቢያ መሆኑን: ለአብነትም ከዚህ በፊት ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ከሕገ ወጥ ሰባክያን እንዲጠበቅ ያስተላለፈው መመሪያ እንኳ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዳይሆን መደረጉን ጉባኤው  በመረዳቱ ለመፍትሔው ጊዜ መስጠት እንደማይገባ  በጽኑ ታምኖበታል።
  • በተለይም በሰሜን አሜሪካ ያለው የአባቶች መለያየትና አንድነት ማጣት ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎች በር የሚከፍትና የምዕመናንንም ሃይማኖታዊ ግንዛቤ መሠረት የሚያናጋ በመሆኑ አባቶቻችን አንድነቱን ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት በሁሉም ዘንድ በትኩረትና በጉጉት እየተጠበቀ መሆኑን  ጉባኤው አምኖበታል።
ውሳኔ
በዚህም መሰረት ጉዳዩ  የሚመለከታቸውና በየደረጃው የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ አካላት ማለትም የቅዱስ ሲኖዶስ ፤ የመንበረ ፓርትያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት እና የየአኅጉረ ስብከት ኃላፊዎች ሁሉ አስቸኳይ መፍትሔ ይሰጡ ዘንድ  በታላቅ አክብሮት እንማጸናለን።
  1. የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እያደረሰው ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ የጉዳዩን  አሳሳቢነት  በመገንዘብ ጥናት በማድረግና ያሉትን መረጃዎችን በመመርመር የማያዳግም መፍትሔ  ይሰጥበት ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን።
  2. ቤተክርስቲያናችን እየተገለገለችባቸው ያሉትንና በተለያዩ ክፍሎች በቤተክርስቲያኒቱ ስም ታትመው የተሰራጩትን አዋልድ መጻሕፍት ሊቃውንት ጉባኤው መርምሮ በመለየት ለምዕመናኑ አስፈላጊውን ትምህርት ይሰጥ ዘንድ እንጠይቃለን።
  3. የቤተክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት ለማስጠበቅ ፤ መናፍቃኑ በየጊዜው ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት፤ በቤተክርስቲያኒቱ ስም የሚወጡ ማናቸውም መጻሕፍት/የህትመት ውጤቶች/ እና የመዝሙር ካሴቶች የቤተክርስቲያንን ትምህርት እና ሥርዓት የጠበቁ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ እንዲቻል የሊቃውንት ጉባኤ በሰው ኃይል: በቁሳቁስና በአሠራር ይጠነክር ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥበት በአጽንኦት እየጠየቅን ለዚሁ ተግባራዊ ክንውን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
  4. በቀደሙ አባቶቻችን በዘመነ ሊቃውንት ይደረግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በየጊዜው ትክክለኛውን የሃይማኖት ትምህርት የሚያስረዱ ለመናፍቃኑ ምላሽ የሚሰጡ ትምህርቶችን በመጻህፍትና በልዩ ልዩ መልክ በስፋትና በይበልጥ እየተዘጋጁ ለህዝብ ይሰራጩ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።
በመምህራነ ወንጌልና ዘማርያን በኩል ልናደርግ የሚገባንን በተመለከተ የተወሰኑ ውሳኔዎች:-
  1. በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ  መምህራነ ወንጌልና  ዘማርያን በየጊዜው በመገናኘት በጋራ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚሠራበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ማኅበረ ቅዱሳን በሚያዘጋጃቸው የአገልግሎት መርሐ ግብሮች ውስጥ በተገቢው መንገድ መሣተፍ
  2. በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተከሰተውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ልዩነት አንድ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ
  3. በተጠናከረ መልኩ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተከፈተውን የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ምዕመናን በትክክል እንዲረዱትና ቤተክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ

    • በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ መጻሐፍት ማዘጋጀት
    • በኢንተርኔት ፓልቶክ ስካይፒ ወዘተ....... ትምህርት መስጠት
    • በማኅበሩ የህትመት ውጤቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ /ሐመር፣ስምዐ ጽድቅ በድረ ገጽ ላይ ትምህርት መስጠት ወዘተ.... 
    • በሬዲዮና ተሌቪዥን ለኮሚኒቲዎች የሚሰጠውን ነጻ ጊዜ በመጠቀም የስብከት አገልግሎት መስጠት

     4. ተተኪ መምህራንን ለማፍራት የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት ፈቃደኛ የሆኑና ፍላጎት ያላቸውን   
          የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ምዕመናንን ማስተማር
     5. በሰሜን አሜሪካ ለተወለዱና በልጅነታቸው ለመጡ ኢትዮጵያውያን ህጻናት ትኩረት በመስጠት ቢያንስ

         ባለንበት አጥቢያ የአገራቸውን ቋንቋና ሃይማኖታቸውን እንዲያውቁና በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ
         ማድረግ

     6. በአገር ቤት የሚሰጠውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በሁሉም ዘርፍ ማገዝ

 
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ቅዳሜ ጥቅምት ፲፰ ቀን  ፳፻፬ ዓ/ም (October 29, 2011)
ኮሎምበስ፣ ኦሀዮ


Written By: admin
Date Posted: 11/27/2011
Number of Views: 4833

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement