የሲያትሉን በዓል ያስተባበሩት በካሊፎርኒያ ሀ/ስብከት የዋሺንግተን ግዛት ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኙት የደ/መድኃኒት ቅ/አማኑኤል ወ አቡነ አረጋዊ፤ የደ/ሰላም ቅ/ሚካኤል፣ ደ/ቁስቋም ቅ/ማርያም ወደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ የደ/ምሕረት ቅ/ሚካኤል እና የደብረ አሚን አቡነ ተ/ሃይማኖት አብያተ ክርስቲያናት ሲሆኑ በተመሳሳይ መልኩም የጥምቀትን በዓል በጋራ እያዘጋጁ መሆኑ በዝግጅቱ ላይ ተገልጿል።
በዕለቱ ለምእመናን መልእክት ያስተላለፉት የወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት መ/ኃይል ቆሞስ አባ ዘመልአክ “ሃይማኖታችንን፣ ክርስቲያናዊ ባህላችንን መጠበቃችን በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስ የሚያሰጠን ጸጋችን ነው” ካሉ በኋላ ምእመናን በዚህ አገር የሚወልዷቸውንና የሚያሳድጓቸውን ልጆቻቸውን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዲያሳድጉ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲያመጧቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ዝግጅቱ የተዋጣለት መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ ምእመናን ጸሎቱ፣ መዝሙራቱ እንዲሁም የዕለቱ ትምህርት እና አጠቃላይ ዝግጅቱ በሰዓቱ ተጀምሮ በተባለው ሰዓት መፈጸሙን እንደ ትልቅ ጠንካራ ጎን ጠቅሰው ከካህናቱ ጸሎትና መዝሙር ባሻገር የሰንበት ት/ቤት መዘምራንና ተተኪ የሚሆኑ ሕጻናት በጋራ ያቀረቡት ዝግጅት ሊበረታታ እንደሚገባው ተናግረዋል።
በ2006 ዓ.ም በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በአካባቢው ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ቀይ ምንጣፍ በማንጠፍ በመሐል አደባባይና በዋና ዋና ጎዳናዎች በማቋረጥ የተከበረ ሲሆን በዚህ ዓመትም ይኸው የአንድነት እና የሕብረት ዝግጅት ቀጥሎ በጥር ወር ላይም እንደሚደገም የወረዳው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ለምእመናን አስታውቋል። በዓሉ የደመራውን ችቦ በመለኮስና በማቃጠል ከተከበረ በኋላ ምእመናን ከትርኳሹ በራሳቸው እና በልጆቻቸው ግንባሮች ላይ የመስቀል ምልክት በመሥራት ከበረከቱ ተካፍለው ተመልሰዋል።