View in English alphabet 
 | Friday, May 3, 2024 ..:: ትምህርተ ሃይማኖት ::.. Register  Login
  

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ!

በትራክት መልክ የተዘጋጀውን ለማግኘት ይህንን ይጫኑ

መስቀሉ ከየት መጣ?

ስለ መስቀል ስንናጋር ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ እንዲሉ ከመሠረቱ ብንናገር ይቀለናል። መስቀል በገነት ውስጥ ካሉ የተለያዩ ዕፅዋት ግኝት ነው። ከዕፅ ዘይት፣ ከዕፅ ከርካህ፣ ከዕፅ ወይራ፣ ከዕፅ ሥርናይ /ምንጭ፦ ሕማማተ መስቀል ገጽ ፴/።


ቃኤል ወንድሙ አቤልን በቅንዓት ከገደለው በኋላ ጽኑዕ የእግዚአብሔር መርገም በላዩ ላይ ወደቀበት። ደም ያሰከረው ቃኤል በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ሆነ። እርሱም ሰውን ባየ ቁጥር ይሸሻል። ሰውም በእርግማን የቆሰለው ሕይወቱን እያየ ይሸሸዋል።

ማኅበራዊ ሕይወት ጀርባዋን የሰጠችው ቃኤል ብቸኝነት ስለከበደችው ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል የጸጸት ዕንባውን ረጨ። «እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ከምድር ፊት አሳደድከኝ ከፊትህም እሰወራለሁ፡ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ: የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል» አለ። እግዚአብሔርም ቃኤልን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክትን አደረገለት።

ይህ ምልክት ምንድን ነው?

ቃኤልን የሚጠብቅ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር። እግዚአብሔር ይህንን መልአክ በያዘው የነበልባል ሰይፍ የገነትን ዕፅ ቆርጦ ለቃኤል እንዲያመጣለት አዘዘው። መልአኩም የተባለውን ፈጸመ። አምጥቶም ተከለለት። ቃኤልም ያየው ሁሉ እንዳይገድለው ከጥፋት የሚሰወርበት የድኅነት ምልክት ሆነለት /ዘፍ. ፬፥፱-፲፭/።


የዕፀ መስቀል ምሥጢር ከዚህ ይነሣል። ይህ የገነት ዕፅ እስከ ጠቢቡ ሰሎሞን ድረስ ከደረሰ በኋላ ከሰሎሞን እስከ ክርስቶስ ልደት የተነሡ ሠላሳ ነገሥታት በእየዘመነ መንግሥታቸው ሲነሡ በየብሮቻቸው ይለብጡታል። ከዚህ ብር የወሰደ ርጉም እንዲሆን ነበር /ካህናተ አይሁድ ጌታን ከይሁዳ በገዙት ጊዜ ለይሁዳ የሰጡት ከዚህ ሠላሳ ብር ነው። ከቃኤል ጀምሮ የነበረው እርግማን በይሁዳ ላይ ወድቋል/።

ጠቢቡ ሰሎሞን ስለዚህ ዕፀ መስቀል ትንቢት ተናግሯል። /መሓ. ፫/ «ዘእምኃሲሶን ይትገዘም ወበጎለጎታ ይተከል» ኃሲሶን ከሚባል ቦታ ተቆርጦ በጎልጎታ ይተከላል /የግዕዙን ዳዊት ተመልከት/ እንዳለ አይሁድ ይህንን ዕፅ ኃሲሶን ከሚባል ቦታ ወስደው በጎልጎታ ተክለውታል። በመጨረሻም አይሁድ ጌታችንን ለመስቀል ባሰቡ ጊዜ መስቀልን ከዚህ የገነት ዕፅ አዘጋጅተውታል። መስቀል ከተለያዩ የገነት ዕፅዋት የበቀለ እንደመሆኑ ክብደቱ መጠን የለውም። አይሁድ ጌታቸውን ጠልተውታልና መስቀል ተሸክሞ የቀራንዮን ዳገት ሲወጣ ወገቡ እንክት ብሎ ይሙት ብለው ስላሰቡ ዕፀ መስቀልን ለሞቱ አዘጋጁለት።

ጌታችን ግን የመጣበት ዓላማ ነውና ሞትን /ዲያብሎስን/ በመስቀል ላይ ድል አድርጎ ለእኛ መስቀልን የድኅነት ምልክታችን፣  ከጠላት ቀስት መሰወሪያችን አድርጎ ሰጠን /ለቃኤል የድኅነት ምልክት እንዳደረገለት/ ፍጻሜው ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የድኅነት ምልክት አድርጎ መስቀልን ሲሰጠን ነው። /መዝ. ፶፱፥፬/ «ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው» ተብሏልና።

ድኅነት በመስቀል ላይ የተፈጸመበት ምክንያት

የእኛ ጌታ ለሥራው ሁሉ ምክንያት አለው። ሞት በዕፅ /በዕፀ በለስ/ ምክንያት ስለመጣ ሕይወት በዕፀ መስቀል ምክንያት ተገኘ። በዕፅ ምክንያት የወደቀብንን የሞት ቀንበር በዕፅ ምክንያት ሲሰብርልን ነው። ዲያብሎስ በዕፅ ምክንያት አዳምን ቢያሸንፈው ጌታችን በዕፀ መስቀል አሽነፈለት። ዱላን በዱላ እንዲመክቱ በዕፅ የጣለን ሰይጣን በዕፅ ተመክቶበት ጭንቅላቱን ተቀንጥሶ ወድቋል። የሰይጣንም ጥበብ በክርስቶስ ጥበብ ተንዶ ተሸንፏል። ጠቢባን ሁኑ እንዳለ በወንጌል /ማቴ. ፲፥፲፮/ አንድም ሰውን በሞተበት ነገር ማዳን ለእግዚአብሕር ልማዱ ነው። በኖኅ ዘመን ዓለም በውኃ ቢጠፋ ሰውን መልሶ በጥምቀት በኩል ውኃን ለድኅነታችን እንዳደረገልን ማለት ነው /ማር. ፲፮፥፲፮/።

በብሉይ ኪዳን መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበር። ጌታችን እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ተሰቀለበት። መስቀሉንም በደሙ ቀድሶ አሁን የወንጀለኞች መቅጫ ሳይሆን የወንጀለኛው የዲያብሎስ መቅጫ አድርጎ ለእኛ ሰጠን። በብሉይ ኪዳን መስቀል የርጉማን መስቀያ ተብሎ ይታመንበት ነበር። የርጉማን ደም መሬትን ያረክሳል ብለው ስለሚያምኑ ከምድር ከፍ ባለ መስቀል ላይ ይሰቅሏቸው ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን እርግማን በመስቀል ላይ ተሸክሞ ከሕግ እርግማን ነጻ አወጣን። በቅዱስ ደሙ ቀደሰን።

በዓለ መስቀል

የአይሁድ ሊቃናት ከካህናቱና ከሕዝቡ ጋር በሰይጣናዊ ቅንዓት ተነሣሥተው በስቅላት ያስገደሉት ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ሥጋው ከተቀበረም በኋላ ቅንዓታቸው ሊበርድ፣ ጭካኔውም ሊረግብ አልቻለም። ያ ያሰቃዩት ጌታ ስለፍጥረቱ ቤዛነት የመጨረሻው ፋሲካ በግ ሆኖ የተሠዋበትንና ይህን የመሰለው መለኮታዊ ፍቅር ተፈጽሞ ምሥጢሩ የተከሰተበትን እንጨት እንኳ በርኅራኄ ትተው ሊያልፉት አልፈለጉም። «ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሰርቀው እንዳይወስዱ» በሚል ምክንያት መቃብሩን እንዲያስጠብቅላቸው ወደ ጲላጦስ ሄደው በመማጸንና እርሱም ፈቃዳቸውን በመፈጸም በድኑን ሳይቀር እንዳልተውት ሁሉ፡  አሁንም በመስቀሉ ላይ የፈጸሙት ግፍ ከዚያ ያላነሰ እንዲያውም የባሰና ወደር የማይገኝለት ሆኖ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን እነሆ እንመለከታለን ።


ይኸውም መስቀሉ ደብዛው ሳይቀር ጨርሶ እንዲጠፋ ያደረጉበት መሠሪ ዕቅዳቸውና ክፉ ድርጊታቸው ነው። በዚህ ዕቅዳቸው መሠረት ማንም ሰው፡ የራሳቸው የሆኑት ወገኖቻቸው እንኳን ሳይቀሩ ሊጠረጥሩ በማይችሉበት ሁኔታና ሥፍራ መስቀሉን በድብቅ አስወስደው ቀበሩት፤ ያም ሥፍራ ለከተማው የቆሻሻ መጣያ የተመደበው ቦታ ነበር። በዚህ ድርጊታቸው ሦስት እኩይ ዓላማዎቻቸውን የፈጸሙ መስሏቸው ነበር። ከእነዚህ ዓላማዎቻቸው መካከል፦

የመጀመርያው፦ የሰማይና የምድር ፈጣሪና ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው የተቆረሰበትንና ክቡር ደሙ የፈሰሰበትን ምሥዋዕ /መሠዊያ/ መስቀሉን ማርከስ ሲሆን፣

ሁለተኛው ደግሞ፦ ሕዝቡ ሁሉ የቤቱንና የከተማውን ጥራጊና ቆሻሻ በየቀኑ ያለማቋረጥ በማፍሰስና በመጣል መቀበሩን ማንም ሊያውቅ እንደማይችል፡ ምናልባት ቢታወቅ እንኳ ምን ጊዜም ተቆፍሮ እንዳይገኝና እንዳይወጣ ማድረግ ነው ።

ሦስተኛውም፦ መስቀሉን እንዲህ አድርገው በሚቀብሩበት ጊዜ የክፋታቸው መጠን ምን ያህል የጸና መሆኑን የሚያመለክተው ሌላው ገጽታ ይታያል። ይኸውም ዕፀ መስቀሉ ምናልባት ተቆፍሮ የተገኘ እንደሆነ የዓለም መድኅን የተሰቀለበት እውነተኛው እንጨት የትኛው እንደሆነ ተለይቶ እንዳይታወቅ ለማደናገር ሲሉ፡ በቀኝና በግራ የተሰቀሉትን ወንበዴዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወንጀለኞች ጭምር የተሰቀሉበትን እንጨት ከጌታ መስቀል ጋር ደባልቀው እንዲቀበር ማድረጋቸው ነው።

ለመሰቀል የጸጋ ስግደት እንዲገባ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ላዳነበት እጁንና እግሩን ለተቸነከረበት ክቡር ደሙ ለፈሰሰበት መስቀል መስገድ እንዲገባ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል። ይኸውም «ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግዚእነ» «የጌታችን እግር ከቆመበት ቦታ እንሰግዳለን» የተባለው ነው /መዝ ፻፴፩፥፯/። ይህም ለቦታ አለ እንጂ መቼ ለመስቀል አለ? እንዳይባል ዓለሙን ስላዳነበት ክቡር ደሙን ስላፈሰሰበት በበለጠ ለመናገር ሲሆን ፴፫ ዓመት ከ፫ ወር በተመላለሰባቸው ቅዱሳት መካናትም ላይ አብያተ ክርስቲያን ተተክለውባቸው ቅዱስ ሥጋው ተፈትቶባቸው ክቡር ደሙ ፈስሶባቸው ቅዱስ መስቀሉ ተተክሎባቸዋልና «ውስተ መካን» ቢልም አንድ ነው። እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተስፋ መስቀል በሌለባቸው ወገኖች ዘንድ ለመስቀል መስገድ ስንፍና ነው፣ ተስፋ ባለን በእኛ ዘንድ ግን መስቀል የእግዚአብሔር ኃይል ነው ባለው መሠረት መስቀል ኃይልነ፣ መስቀል ጽንዕነ፣ መስቀል ቤዛነ፣ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ እያልን ለመስቀል እንሰግዳለን። «እስመ ነገረ መስቀሉሰ ዕበድ ውእቱ በኀበ ኀጉለን ወበኀቤ ነሰ ለእለ ድኅነ ኃይለ እግዚአብሔር ውእቱ» እንዳለ /፩ ቆሮ. ፩/። ደግሞም እኔ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንጂ በምንም በምን አልመካም ብሏል /ገላ. ፮÷፲፬/። እንኳንስ ዓለሙ ለዳነበት፣ ክቡር ደሙ ለፈሰሰበት መስቀል፡ ያዕቆብ ለገዛ በትሩ እየሰገደ እግዚአብሔርን ስላመሰገነ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት ተመሰገነበት እንጂ አልተነቀፈበትም /ዘፍ ፵፯÷፴፩፣ ዕብ ፲፩÷፳፩/። ያዕቆብ ከራሱ በትር በመስገዱ አምልኮ ባዕድ ያልተቆጠረበት ክርስቶስ ለተሰቀለበት ክቡር ደሙ ለፈሰሰበት ቅዱስ መስቀል የሰገደማ እንዴት ሊመሰገን አይገባ!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት፣ መስከረም ፳፻፫ ዓ.ም.


Written By: admin
Date Posted: 9/25/2012
Number of Views: 6077

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement