View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ::.. Register  Login
  

ምሥጢረ ጥምቀት - በማን ስም ልንጠመቅ ይገባል

 ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጆች ይሆኑ ዘንድ በሥላሴ ስም ታጠምቃለች፡፡ ይህም ጌታ ራሱ ለሐዋርያቱ ‹‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም  ያጠመቃችኋቸው፡፡››  (ማቴ. 28÷19) ብሎ የሰጠውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ዘመን አንስቶ በሥላሴ (በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ) ስም መጠመቅ የድኀነት በር ቁልፍ መሆኑን ስታስተምርና ተግባራዊ ስታደርግም ኖራለች፡፡

 ይህንን የወንጌል ቃል የሚያጣምሙ መናፍቃን በኢየሱስ ስም ብቻ መጠመቅ አለብን እንጂ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ የለብንም ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን አነጋገር ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ ለተሰበሰቡት አይሁድ የምሥራቹን ቃል ድምጹን ከፍ አድርጐ ባሰማቸው ጊዜ ልባቸው ተነካ፡፡ ስለዚህም ‹‹ምን እናድርግ›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን እንዲነግራቸው ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ንስሐ ግቡ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ አላቸው›› (የሐዋ ሥራ 2÷38)፡፡
ሐዋርያው ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ብሎ ማስተማሩ ለምን ነበር? ለምን ጌታ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ ያለውን ተከትሎ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ አላለም? የሚል ጥያቄ ለሚያነሣ ሁሉ ምክንያቱ እንደሚከተለው ነው፡፡በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ የተሰበሰቡት አይሁድ ከጥንት ጀምሮ በነቢያት አንደበት ይወርዳል ይወለዳል እየተባለ የተነገረለትን መሲሕን ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡ ሐዋርያውም ያ የተስፋው ቃል ዛሬ መፈጸሙንና በተስፋው ቃል መሠረት ከድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ 33 ዓመተ ከ3 ወር በምድር ላይ ተመላልሦ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሰውን ልጅ በደሙ የዋጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት የተነገረለት ሱባዔ የተቆጠረለት መሆኑን አምነው በሰው ካልተጠመቁ በስተቀር አብርሃም አባታችን እግዚአብሔር አምላካችን በሚለው እምነት ብቻ አምነው ጌታን በሰቀሉት አይሁድ መንገድ የሚጓዙ ከሆነ እንደማይድኑ በመሲሕ አምነው በስሙም ከተጠመቁ ግን እንደ ሚድኑ ሊያስተምራቸው ስለፈለገ የጌታን ስም ለይቶ ጠራ፡፡ በዚህም የጌታን አዳኝነትና መሲሕነት አምነው እንዲቀበሉ በአጽንዖት መናገሩ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሐዋርያት ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ቤዛ የሆነልንን ጌታ ሰው ሁሉ አምኖ እንዲድን በየሄዱበት የጌታን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት አሰተምረዋል፡፡ የስብከታቸው ማዕከል የነበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ክህደቱ ጸንቶ የነበረው በጌታ የባሕርይ አምላክነት ላይ ነበርና፡፡ በዚህ የተነሣ የእርሱን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት ለማሳመን ጌታን የስብከታቸው ማዕከል አደረጉ፡፡

Written By: host
Date Posted: 12/17/2007
Number of Views: 15681

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement