በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“አላ ሰብእ አልብየ” ሰው የለኝም (ዮሐ 5፥7)
በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ከፈለኝ ወልደጊዮርጊስ
ቤተ ሳይዳ ወይም ቤተሰዳ ማለት የምህረት ቤት ማለት ነው አምስትም መመላለሻ ያላት ማለትም አምስቱ አዕማደ ምሥጢር የሚገኝባት በነዚህ ሁሉ ድህነትን የምትሰጥ ናትና ቤተሳይዳ የምህረት ቤት ናት። አምስቱ አዕማድም የተባሉትም 1) ምስጢረ ሥላሴ 2) ምስጢረ ሥጋዌ 3) ምስጢረ ጥምቀት 4) ምስጢረ ቁርባን እና 5) ምስጢረ ትንሳኤ ሙታን የሚባሉ ናቸው። እንግዲህ ወደዚች የምህረት ቦታ፣ የፀበል ቦታ በመጀመሪያ ሄዶ የተገኘ፣ ገብቶ የተጠመቀ፣ ካለበት ሕመም ሁሉ ፍጹም ጤነኛ ይሆናል። ይህም ሰው 38ዓመት ሙሉ በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ወደ ጸበሏ የሚወስደው፣ በርትቶ ጸንቶ ጠብቆ በሰው ፊት የሚያስገባው ሰው አጥቶ ለብዙ ዘመናት በተስፋ መቁረጥ ላይ ይገኝ የነበረ ነበር።