የምሥጢረ ቁርባን አመሠራረት
ምሥጢረ ቁርባንን ጌታችን ከሕማማቱና ከሞቱ በፊት በዋዜማው ኀሙስ ማታ መሥርቷል። ይህም ሰዓት በአይሁድ የቀን አቆጣጠር ወደ ዓርብ ይታሰባል። በዚያም ወቅት የኦሪት የፋሲካ በግ የሚሠዋበት ጊዜ በመሆኑ ጌታችን ከደቀመዛሙርቱ ጋር የኦሪትን መሥዋዕት አሳልፎ መሥዋዕተ ወንጌልን መሥርቷል። በዚያችም ምሽት የኦሪቱን በግ መሥዋዕትነት አበቃ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እውነተኛው የእግዚአብሔር በግ ይሠዋል። እርሱም የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው። ስለዚህ በማዕዱ ዙሪያ ለተሰበሰቡት ሐዋርያቱ በብሉይ ኪዳን ምሳሌ የተመሰለለትን: ትንቢት የተነገረለትን አዲሱን ቃል ኪዳን ጌታ በራሱ ሥጋና ደም መሠረተ። የእውነተኛው መሥዋዕት ምሳሌ የሆነው የኦሪቱን ማዕድ እየበሉ ሳለ “ኢየሱስ እንጀራና ኅብስትን አንስቶ ባረከ። ቆርሶ ለደቀመዛሙርቱ ሰጠና እንካቹ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው። እንዲህም አለ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” በማለት ምሥጢረ ቁርባንን መሠረተ /ማቴ ፳፮፣፳፮-፳፰/። ኪዳን ማለት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገባው ቃል ኪዳን የሚያመለክት ነው።