View in English alphabet 
 | Sunday, May 5, 2024 ..:: ነገረ ቅዱሳን ::.. Register  Login
  

ዝክረ ቴዎፍሎስ

 

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአገራችን ሁለንተናዊ ማንነት ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይት ናት ሲባል ሁልጊዜ እንደሚባለው በሥነ ጽሑፍ ወይም በሥነ ሕንፃው፣ በሥነ ሥዕሉ ወይም በሥነ ትምህርቱ ብቻ አይደለም። ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ማንነት ላይ የነበራትና ያላት አስተዋፅዖ ፍጹም ስለሆነ ለአገሪቱ የመጣን ደግ ነገር የመካፈሏን ያህል ጉዳቷንም ተቀብላለች። ኀዘኗን አዝናለች፣ ሕማሟን ታማለች። የአገሪቷም ሆነ የቤተ ክርስቲያናችን ያለፈ ታሪክ የሚያስረዳን ይኽንኑ ነው።

ጥንት የሚባለው ታሪካችን እንዳለ ሆኖ ባለፉት መቶ ዓመታት የተመዘገበውን ታሪክ ብንመለከት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአገራችን በተከሰተው ውጣ ውረድ ቀደምት ተጠቂ እንደሆነች እንረዳለን። ይህ ደግሞ ለአገሪቱ ህልውና የቤተ ክርስቲያን ሚና ወሳኝ እንደሆነ ያረጋግጣል።

በዚህ ጽሑፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕውቀት መንፈሳዊ ወልዳ ለወግ ለማዕረግ ካበቃቻቸው በኋላ የሰጠቻቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ደፋ ቀና ሲሉ በገፋዕያን የተገደሉትን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ዜና ሕይወትና የሰማዕትነት ዕረፍት እናዘክራለን።

ቀድሞ ሊቀ ሥልጣናት መልእክቱ ይባሉ ነበር፤ ከአባታቸው ከአቶ ጀንበሬ ውቤ ከእናታቸው ከወ/ሮ ዘሪቱ አደላሁ በቀድሞው የጐጃም ጠቅላይ ግዛት፣ በደብረ ማርቆስ አውራጃ፣ በማቻከል ወረዳ፣ ደብረ ገነት ኤልያስ በሚባለው ታላቅ ደብር ሚያዝያ 16 ቀን 1902 ዓ.ም. ተወለዱ። በደብረ ኤልያስ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ /የንባብና የዜማ/ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ተምረው ከግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ ማዕረገ ዲቁናን ተቀበሉ። በዚያው ደብር ከመምህር ገብረ ሥላሴ ቅኔ  ከነአገባቡ ተምረው በመምህርነት ተመረቁ። በርእሰ አድባራት ደብረ ጽዮን አዲስ ዓለም ማርያም ከንቡረ እድ ሐዲስ ተክሌ /በኋላ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ/ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜ በሚገባ አሔዱ።

በ1930 ዓ.ም. ወደ ደብረ ሊባኖስ በመውረድ ማዕረገ ምንኩስናን ተቀበሉ፤ ብዙም ሳይቆዩ ከአቡነ አብርሃም ማዕረገ ቅስናን ተቀበሉ። በ1935 ዓ.ም. በወቅቱ መካነ ሥላሴ ገዳም ይባል በነበረው በዛሬው መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መምህር ሆነው ተሾሙ። ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓ.ም. በካይሮ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ አንብሮተ እድ ከሌሎች አራት አባቶች ጋር «አባ ቴዎፍሎስ ጳጳስ ዘሐረር» ተብለው ተሾሙ። ከ1943-1963 ዓ.ም. አገረ ስብከታቸውን ከማስተዳደር ጋር የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡን ባስልዮስ እንደራሴና በኋላም ሊቀ ጳጳስ በመሆን አገለገሉ።

 

በ1963 ዓ.ም. ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ። እስከ መጋቢት 1968 ዓ.ም. ቤተ ክርስቲያንን በቅንነትና በትጋት አገለገሉ። መጋቢት 3 ቀን 1968 ዓ.ም. ዘውዳዊውን መንግሥት በኃይል አውርዶ ሥልጣን በያዘው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መንግሥት ለእስር ተዳረጉ። ከ28 ወራት እስርና እንግልት በኋላ ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ.ም. በሰሜን አዲስ አበባ፣ በወረዳ 12 ቀበሌ 22 በሚገኘው የራስ አሥራተ ካሣ ቤት በሚያሰቅቅ ሁኔታ በገመድ ታንቀው ተገደሉ። አስከሬናቸውም የእርሳቸውን ዓይነት የሞት ጽዋ ከተቀበሉ ሰዎች ጋር በዚያው ቅጽር ግቢ ተቀብሮ ከቆየ በኋላ በወቅቱ አሟሟታቸውንና የተቀበሩበትን በተመለከተው የደርግ ባለሥልጣን ጥቆማ አጽማቸው ወጥቶ ሐምሌ 4 ቀን 1984 ዓ.ም. በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር ዐረፈ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመከራ ጽዋ ተቀብለው ያለፉትን ቅዱስ አባት በሰማዕታት መዝገብ ውስጥ እንዲሰፍር፥ በክብራቸውም «ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ» እንዲባሉ ወስኗል።

ከዚህ በመቀጠል ቅዱስነታቸው በደርግ ወታደሮች ከተያዙበት ቀን ጀምሮ በእስር ቤት ያሳለፉትን የመከራና የእንግልት ሕይወት፣ በመጨረሻም በሚያሰቅቅ ሁኔታ እንዴት እንደተገደሉ እናቀርባለን። ለምናቀርበው ሐተታ ምንጫችን የቅዱስነታቸው የሥጋ ወንድም የአቶ አበራ ጀንበሬ የዓይን ምስክርነት ነው። አቶ አበራ ጀንበሬ በወቅቱ እርሳቸውም ለእስር ተዳርገው የቅዱስነታቸውን የእስር ቤት ሕይወት ከመጀመሪያው ጀምሮ ተከታትለው በመመዝገብ የእስር ቤቱ አበሳ በታላቁ ቤተ መንግሥት ከ1966-1974 ዓ.ም. በሚል ርዕስ በ1995 ዓ.ም. አንድ መጽሐፍ አሳትመዋል።

 

+++

 

«በታላቁ ቤተ መንግሥት ታስረው የነበሩ የቀድሞው መንግሥት ባለሥልጣኖች ንጹሕ አየር ለማግኘት፣ በፀሐይ አካላቸውን ላማሞቅ፣ የተሳሰሩ እግሮቻቸውን ለማፍታታት በዙፋን አዳራሽ አጠገብ በሚገኝ በሽቦ በታጠረ ጠባብ ክልል ውስጥ ይንከላወሳሉ። ቀኑ መጋቢት 3 ቀን 1968 ዓ.ም. ከእኩለ ቀን በኋላ ነበር። በዚህ ወቅት ታላቁ መንፈሳዊ አባት ሁለት እጆቻቸውን በአንድ ላይ በሰንሰለት ታስረው እየተገፈተሩ ያለጫሚያ በባዶ እግራቸው ሲመጡ የተመለከቱት እነዚያ እስረኞች ባሉበት ክው ብለው ቀሩ። በዚህ ወቅት ነበር አንዱ እስረኛ ልቡ ተነክቶ «አዲዮስ የኢትዮጵያ ሰብአዊነትና መንፈሳዊነት!!» ያለው።

«… የኢትዮጵያ ሕዝብ ግብረ ገብነትና መንፈሳዊነት በእነዚህ ጋጠ ወጦች አይለካም» አለ ሌላው በድርጊቱ መብገኑን ሁኔታው እየነገረበት። «ካህኑን እንደ ፖለቲከኛ፣ መንፈሳዊ አባቱን እንደ ወንጀለኛ የሚመለከት ወታደራዊ ቡድን በዚህች ቅድስት አገር መነሣቱ ያሳዝናል። መንፈሳዊ አባት በግፍ ሲንገላታ ከማየት መሞት ይመረጣል» አለ ሌላው በመበሳጨት።

«የአደፈ ሽሮአማ ቀሚስ እንደለበሱ ከቀኝም፣ ከግራም፣ ከኋላም ሳንጃ የተሰካበት ጠመንዣ ተደግኖባቸው ወደዚያች የፖለቲካ እስረኞች መቀየጃ ቅጥር ግቢ ሲገቡ መንፈሳዊው አባት «የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» በማለት ግፍ ለሚፈጸሙባቸው የሚጸልዩ እንጂ የተበሳጩና የተሸበሩ አይመስልም ነበር።

«እስረኛው ከድንጋጤው ገና ሳይላቀቅ፣ ምን እንደሚልና እንደሚያደርግ አሰላስሎ ሳይጨርስ፣ ከቆመበት ሳይላወስ ነበር ከአንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ አስገብተው የቆለፉባቸውና እግራቸውን በእግረ ሙቅ እጃቸውን በሰንሰለት ጠፍረው ከአልጋ ጋር ያሰሯቸው። «ይህን አዚመኛ ቄስ ተጠንቅቃችሁ ጠብቁ» በማለት ለወታደሮቹ ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቶ የዘቡ አዛዥ ከአጥሩ ወጥቶ ሄደ።

«መንፈሳዊው አባት የታሰሩበት ክፍል በማግሥቱ የአሳሪዎች ምልልስ ታየባት። ሹማምንት በመፈራረቅ ጎበኟት። ፈንጠር፣ ፈንጠር፣ ቀበጥበጥ ብለው እንዳልገቡ ተስፋ ቆርጠው ሲወጡ ተስተዋሉ። ይህ ሁሉ ምልልስ፣ ይህ ሁሉ ጋጋታ የተከሰተው ከአንድ ክፍል ውስጥ እግር እጃቸው ከአልጋ እግር ጋር የታሰረው መንፈሳዊ አባት ምግብ አልበላም ብለው በመወሰናቸው ነበር። ሻለቃ ዳንኤል አስፋውና ሌሎች የእስር ቤቱ ኃላፊዎች የሚመጣላቸውን ምግብ እንዲመገቡ ለማድረግ ቢሞክሩም ጽኑዕ አባት አልተበገሩም። ከዚህ በኋላ ነበር ምግብ አልበላም በማለት ማስቸገራቸውን በመግለጽ ሻለቃ ዳንኤል ለደርግ የጸጥታ ጥበቃ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ባቀረበው ማስታወሻ ግርጌ ላይ «ምግብ እንዲገባላቸው አድርጉ እንጂ ቢበሉ ባይበሉ የራሳቸው ጉዳይ ነው» ሲል ሻለቃ ተካ ቱሉ ምልክት ያደረገው።

«እኒያ አባት በዚያች መስኮት በሌላት ጠባብ ክፍል ምግብ ብቻ ሳይሆን ንጹሕ አየርም ሳያገኙ ሰባት ቀን ጦማቸውን ውለው አደሩ። ከዚያ በኋላ ነበር ሌሎች እስረኞች አግባብተው ምግብ እንዲበሉ እንዲያደርጉ ለአንድ ቁጥር ክፍል ኃላፊ ትእዛዝ በመስጠት አሳሪዎቻቸው ከሰው እንዲቀላቀሉ ያደረጉት። እግር እጃቸው ከብረት ተላቆ ከመንፈስ ልጆቻቸው ጋር ተቀላቀሉ። ለጸሎት እንዲያመቻቸውም ወደ ዙፋን አዳራሽ በመግቢያው ዋና በር ደረጃ ሥር የሚገኘው ጎሮኖ ለእርሳቸው መኝታ ተለቀቀላቸው። በአንድ ቁጥር ክፍል ውስጥ የሚገኙት እስረኞች በተለይም ብርጋዴር ጀነራል ሳሙኤል በየነ አቅማቸው በፈቀደ መጠን የሚጐድላቸውን አሟልተውና አንጥፈው ተቀበሏቸው። ምግብ ሲያቀርቡላቸው ግን «እግዚአብሔር ይስጣችሁ አልበላም» የሚል ሆነ መልሳቸው። የደረቀ ጉሮሯቸውን በውኃ እየተጉመጠመጡ ብቻ ምግብ ሳይበሉ፣ ውኃ ሳይጠጡ መጾሙን ቀጠሉ። ጠንካራነታቸውን አስመሰከሩ፤ የመንፈስ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ምግባቸውም ጾም ጸሎት ሆነ። የዕለት ተዕለት ሁኔታቸውም ለሌሎች እስረኞች መንፈሳዊ ጽናትን ሰጠ።»

«ይሁንና ፋሲካ በዋለ ማግስት ከእስረኞች መካከል በዕድሜ የገፉት እንደነ ደጃዝማች ሐረጐት ዓባይ ያሉት አጥብቀውና አስጨንቀው ስለለመኗቸው እህል ሊበሉ መቻላቸውን አብረዋቸው ታስረው ከነበሩት ለማረጋገጥ ተችሏል።»

የቅዱስነታቸውን የእስር ቤት የሰቆቃ ቆይታ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የተረከው የአቶ አበራ ጀንበሬ የእስር ቤቱ አበሳ በታላቁ ቤተ መንግሥት 1966-74 ዓ.ም. የተሰኘው መጽሐፍ በመጨረሻ እንዴት ጽዋ ሰማዕትነትን እንደተቀበሉ በሚከተለው መልኩ ያስረዳል።

«ሐምሌ 3-10 ቀን 1971 ዓ.ም. ከታላቁ ቤተ መንግሥት እስር ቤት ክፍል 1፣ 2 እና 11 እስረኞች በየሦስተኛው ቀን ሁለትም ሦስትም ኾነው እየተጠሩ ተወስደው የግፍ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስም ከክፍል 1 የተጠሩትና የተወሰዱት ከደጃዝማች ካሣ ወልደ ማርያምና ከብርጋዴር ጀነራል ሳሙኤል በየነ ጋር በዕለተ ቅዳሜ ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ.ም. ከቀኑ በአምስት ሰዓት አካባቢ ነበር። ቅዱስነታቸው የሰማዕትነት ጽዋን እንዲቀበሉ የተወሰዱት በሰሜን አዲስ አበባ ወረዳ 12 ቀበሌ 22 ወደሚገኘው የራስ አሥራተ ካሣ ሕንፃ ቤት ነበር። በዚህ ዘመናዊ ሕንፃ ቤት ውስጥ የተገደሉት እስረኞች ቁጥር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ጨምሮ 33 ሲሆን አንገታቸውን በገመድ ታንቀው እንዴት እንደተገደሉ በዓይን ምስክር የተነገረውን ቀጥሎ ካለው ገለጻ መረዳት ይቻላል።

 

+++

 

ሚያዝያ 20 ቀን 1984 ዓ.ም. የቅዱስነታቸውን መቃብር በተጠቀሰው የራስ አሥራተ ካሣ ግቢ ይፈልግ ለነበረው ኮሚቴ ገለጻውን ያደረገው በደርግ መንግሥት የደኅንነት ሹም የነበረ ኮሎኔል ነው። የኮሎኔሉን ገለጻ በትክክል ለመረዳት እንዲቻል የተገደሉበትን ቤት ውስጣዊ ክፍል እንዲወክል ተደርጐ የተሣለውን ባለ 8 ቁጥር ሥዕል ከገለጸው ጋር ማገናዘብ ያስፈልጋል።

ሀ/ የሚገደሉት እስረኞች ከሕንፃው ውጪ ከደረጃው በታች ቁጥር 1 አካባቢ ተሰልፈው እንዲቆዩ ይደረጋል። ሕንፃው ከፍ ብሎ የተሠራ በመሆኑ ቁጥር 1 አካባቢ ሆኖ ወደ ውስጥ ማየት አይቻልም። ወደ ሕንፃው መግባት የሚቻለው በረጅም ደረጃ ወጥቶ ሲሆን እስረኞቹ ተሰልፈው ሞታቸውን የሚጠብቁት ከቤቱ ደረጃ በታች ነበር።

ለ/ አንድ ኮማንዶ ቁጥር 2 አካባቢ ሆኖ የሚገደሉትን እስረኞች አንድ በአንድ እየጠራ ወደ ሕንፃው ውስጥ ያስገባል።

ሐ/ የተጠራው እስረኛ የሞት ጐዳና የሆነውን ቀስት ተከትሎ በመሄድ ቁጥር 3 አካባቢ ሲደርስ የኮማንዶዎቹ አዛዥ ቁጥር 4 አካባቢ ከክፍሉ በር ላይ ቆሞ እስረኛውን «ወደዚህ ና» ይለዋል።

መ/ እስረኛው ወደ ቀኝ በመዞር አሁንም ቀስቱን ተከትሎ «ወደዚህ ና» ወደ አለው የኮማንዶ አዛዥ በመሄድ ላይ እንዳለ ቁጥር 5 አካባቢ ሲደርስ ቁጥር 6 አካባቢ በጨለማ ኮሪዶር ውስጥ ተደብቀው ከሚጠባበቁት ገዳይ ኮማንዶዎች መካከል አንዱ እስረኛውን ሳያስበው በድንገት በሲባጐ ያንቀዋል። ኮማንዶው በሁለት እጆቹ ላይ ጠምጥሞ አጥብቆ የያዘውን ሲባጐ በእስረኛው አንገት ላይ ካጠለቀ በኋላ ሲባጐው እንዲሸረብ ከእግሩ ሽብርክ በማለት በራሱ ዙሪያ ይሽከረከርና ቀና ብሎ በአንገቱ ላይ ሲባጐ ያገባበትን እስረኛ ነፍሱ እስክትወጣ ድረስ በጀርባው ላይ ይሸከመዋል። ነፍሱ በዚህ ሁኔታ ከወጣች በኋላ ከመሬት ላይ ይጥለውና የእስረኛውን ሬሳ ጐትቶ በመውሰድ ቁጥር 7 ውስጥ ያስቀምጠዋል።

ሠ/ ከውስጥ ምልክት ሲያገኝ ቁጥር 2 አካባቢ ያለው ኮማንዶ የሚቀጥለውን እስረኛ ስም ይጠራል። ከእርሱ በፊት ተጠርቶ የገባው እስረኛ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ የማያውቀው ተረኛ እስረኛ ተጠርቶ ይገባል፤ ቁጥር 5 አካባቢ ሲደርስ በተረኛው ገዳይ ኮማንዶ በሲባጐ ታንቆ ይገደልና ፌሳው ወደ ቁጥር 7 ይወሰዳል። ቁጥር 7 በእስረኞች ሬሳ ከሞላ በኋላ ሬሳ የማከማቸቱ ተግባር ወደ ቁጥር 8 ተዛወረ። በዚህ ሁኔታ እስረኞቹ በሙሉ ተገደሉ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስም በገመድ ታንቀው ጽዋ ሰማዕትነትን የተጐነጩት በዚህ ዘግናኝ ሁኔታ ነው። ይህ ዘግናኝ ሁኔታ መንፈሳቸውን የነካው ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ በግጥም ገልጸውታል፦

«አንች የሐምሌ ሳምንት ሥቃይ የታየብሽ
የሕዝብ ደም እንደ ጐርፍ በግፍ ፈሰሰብሽ
እንደ እስስት በገመድ አቡን ታነቁብሽ»

 

ረ/ እስረኞቹ በሙሉ ከተገደሉ በኋላ ሬሳቸው በሁለቱ ክፍሎች ውስጥ በሸራ ተሸፍኖ ዋለ። ግድያው የተጀመረው ጧት አካባቢ ነበር። ግድያው ከበላይ አካል በታዘዘው መሠረት ስለመፈጸሙ ሪፖርት ቀረበ። ባለሥልጣኖች መጥተው ዓይተው ከአረጋገጡ በኋላ የእስረኞቹ ሬሳ እንዲቀበር ታዘዘ። ቀብሩ የተፈጸመው በዚያው ዕለት ከምሽቱ 3፡00-4፡00 ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር። በዚሁ ወቅት የእስረኞቹ ትርፍ ልብሶች ተሰብስበው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ከተጨመሩ በኋላ ኖራ ተነስንሶባቸው ተቀበሩ።

የእስረኞች ሬሳ የተቀበሩባቸው ጉድጓዶች በቁጥር 10 እና 11 አካባቢ ግንቡን አስጠግቶ በሰሜን ወደ ደቡብ በረጅሙ የተቆፈሩት ግድያው ከመፈጸሙ ከጥቂት ቀናት በፊት እንደነበር ቦታውን ጠቁሞ ካሳየ የደኅንነት ክፍል ወታደር ለመረዳት ተችሏል። በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አስከሬን ተጥሎ የተገኘው በቁጥር 11 በተመለከተው ጉድጓድ ከተቀበረው ከዶ/ር ኃይሌ ፊዳ ጋር ነበር።»

 

ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት በሚል ርዕስ ሐምሌ 4 ቀን 1989 ዓ.ም. በወጣው መጽሔት እንደተገለጠው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አስከሬን ከራስ አሥራተ ካሣ ግቢ ከተጣለበት ተቆፍሮ ወጥቶ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አርፎ ከቆየ በኋላ ሐምሌ 4 ቀን 1984 ዓ.ም. በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐውደ ምሕረት ጸሎተ ፍትሐት ተደርጐለት ሲያበቃ ያን ጊዜ ዓቃቤ መንበር የነበሩት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በቅዱስ ሲኖዶስ ስም የሚከተለውን መልእክት አስተላለፉ።

«ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕት ተብለው እንዲጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።»

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከላይ በተገለጠው ሁኔታ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያበረከቱት አስተዋጽዖ ሲዘከር ይኖር ዘንድ በአዲስ አበባ አገረ ስብከት በሚገኘው መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቤተ መዘክር ተቋቁሞላቸዋል። ሐውልትም ታንፆላቸዋል። የቅዱስነታቸው በረከት ይደርብን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 

 ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት መጋቢት/ሚያዝያ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ለድረ ገጽ እንዲመች ሆኖ የተወሰደ

 

 


Written By: admin
Date Posted: 7/7/2011
Number of Views: 6750

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement