View in English alphabet 
 | Tuesday, May 7, 2024 ..:: ነገረ ቅዱሳን ::.. Register  Login
  

ቅዱሳን መላእክት- የመላእክት አገልግሎት

ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ለአገልግሎት የሚፋጠኑ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትንና ቸርነትን ወደ ሰው ልጆች፣ የሰዎችንም ጸሎትና ልመና ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ናቸው፡፡

ስለ ተራዳኢነታቸው - በቅዱሳት መጻሕፍት

ቅዱሳን መላእክት በመንገዳችን ሁሉ እንደሚጠብቁን ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል «በመንገድ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንነተ ያዝዛቸዋልና፣ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል» (መዝ. 90/91/-11)፡፡

ያዕቆብ የልጁ የዮሴፍን ልጆች ምናሴንና ኤፍሬምን ሲባርክ «አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፣ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፣ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ» ብሏል (ዘፍ. 48፥6)፡፡ በዚህም መላእክት ከክፉ ነገር ሁሉ የሚያድኑና የሚጠብቁ እንደሆኑ፣ መባረክም እንደሚችሉ አስገንዝቧል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የመላእክትን አዳኝነት ሲያስገነዝብ «እግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል፡፡ ብሏል» (መዝ. 33/34/፥1)፡፡

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለሕዝበ እግዚአብሔር /ለእሥራኤል/ አገልጋዮቹ መላእክትን ሊያሳዝኑ እንደማይገባ ሲያስጠነቅቃቸው «በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ፣ ወደ አዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ፣ እነሆ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፡፡ ቃሉንም አድምጡ፡፡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት» (ዘጸ. 23፥20) ብሏል፡፡

የቅዱሳን መላእክት ረዳትነት አስፈላጊ መሆኑን ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤል ሲያመለክት ‹‹የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፡፡ እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፡፡ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት›› (ዳን. 10፥13) ብሏል፡፡

በተለይ በፍጻሜ ዘመን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ለክርስቲያኖች በአማላጅነቱና በተራዳኢነቱ እንደሚቆምላቸው «ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል» ተብሎ በነቢዩ በዳንኤል መጽሐፍ ተገልጧል (ዳን. 12፥1)፡፡

የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት በሁለት መንገድ ነው፡፡ ማለትም የሰውን ጸሎት ቅድመ እግዚአብሔር የሚያደርሱና የእግዚአብሔርንም ምሕረት ለሰው ልጆች የሚያመጡ ናቸው፡፡ በተለይ የሰዎች መከራ፣ ዕንባና ጸሎት ቅድመ እዚአብሔር የሚያደርሱና ለሰዎች ልጆች እንደሚያማልዱ በትንቢተ ዘካርያስ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፏል፦ «…የእግዚአብሔር መልአክ መልሶ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህን ሰባ ዓመት የተቆጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከመቼ ነው; አለ…እግዚአብሔር መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው፡፡ ስለዚህም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፡፡ ስበክ፡፡ እንዲህም በል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡፡ … ወደ ኢየሩሳለም በምሕረት ተመልሻለሁ» (ዘካ. 1፥12-17)፡፡

ጌታ በዘመነ ስብከቱ የቅዱሳን መላእክትን አማላጅነት በምሳሌ ሲያስረዳ «አንድ ሰው በታወቀች በወይኑ ቦታ ውስጥ በለስ ነበረችው፡፡ ፍሬ ሊለቅም ወደ እርስዋ ሄደ አላገኘም፡፡ የወይኑን ጠባቂም የዛችን በለስ ፍሬ ልለቅም ስመላለስ እነሆ ሦስት ዓመት ነው፡፡ አላገኘሁም፡፡ እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቁረጣት አለው፡፡ እሱም መልሶ እንዲህ አለው፣ ‹አቤቱ የዘንድሮን እንኳን ተዋት፡፡ ዙሪያዋን አፈር እስካስታቅፋት፣ ፍግም እስካፈስሰባት ድረስ፡፡ ምናልባት ለከርሞ ታፈራ እንደሆነ፣ ያለዚያ ግን እንቆርጣታለን›፡፡» (ሉቃ. 13፥7-9)፡፡

በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር የተናገረው የበለስዋ ባለቤት እግዚአሔር ነው፡፡ በለስ የሰው ልጅ ነው፡፡ የወይኑ ጠባቂም ጠባቂ መልአክ ነው፡፡ ፈጣሪያችን በሥራችን አዝኖ በሚፈርድበት ጊዜ አማላጆቻችን መላእክት «አቤቱ ጌታ ሆይ ይህቺን ያሁንዋን ብቻ ታገሥ፣ እኛ ተራድተን መልካም ምግባር የማይሠራ ከሆነ እንደፈቃድህ ይሁን» በማለት በአማላጅነታቸው ይራዳሉ፡፡ ሙሴ እሥራኤል እግዚአብሔርን አሳዝነው ጽኑ ፍርድ ተፈርዶባቸው ሳለ የፈረደውን ፍርድ በምልጃው እንዲያነሣ እንዳደረገው ሁሉ ማለት ነው (ዘጸ. 32፥1ዐ-14)፡፡

የቅዱሳን ጸሎት የሚያርገው በመላእክት እጅ ነው፡፡ ለዚሁም ማስረጃ የሚሆነን በዮሐንስ ራእይ ላይ ተጽፎ የምናገኘው ነው፡፡ «…የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው፡፡ የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር በመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ፡፡» (ራእይ 8፥3-5)፡፡

ስለዚህ ቅዱሳን መላእክት ጸሎታችንን፣ ልመናችንን እና ዕንባችንን በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባሉ፡፡ መልስም ያሰጣሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የመላእክትን ተራዳኢነት ሲያስገነዝብ «ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ፣ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን» ብሏል (ዕብ. 1፥14)፡፡

Written By: admin
Date Posted: 12/19/2007
Number of Views: 11378

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement