እኔ ብቻ
በዲ/ን አብነት አረጋ
ምድር እንኳ በመስከረም
ምንም እርሷ ብታረምም
በአበቦች ኅብረ ቀለም
አረንጓዴ ለብሳ ለምለም
አፍላጋቱ ባሕር ውቅያኖስ
ጥርት ብለው ከመደፍረስ
ጭጋግ ጠፍቶ ከሰማያት
ከልካይ ሲያጡ ብርሃን ሙቀት
የቤት የዱር እንስሳት
በመደሰት ሲራኮት
በደመ ነፍስ ዘመን ቆጥሮ
አሮጌውን ዘመን ሽሮ
ከአዲሱ ጋር ሲጓዝ አብሮ።
ፍጥረት ሁሉ በደመ ነፍስ
በአዲስ ዓመት ሲሆን አዲስ
ብቻ! እኔ… እኔ ብቻ!
ተለይቼ አጥቼ አቻ
ስቆጥር ዓመት ስደምር
ሳሰላ ዘመን ስቀምር
አሮጌ ስል አዲስ ዓመት
እየኖርኩኝ በመሞት
ስለፋ፣ ስደክም ስጥር
ጉድፌን በሜካፕ ልቀይር
አዲስ ስጫማ አዲስ ስለብስ
ወይም ፓርቲ ስደግስ
ከዘመኑ ጋር ሳልታደስ
ወደ ሞቴ ስገሰግስ
ሳልበላ የአምላኬን ሥጋ
ወደ ሞቴ ስጠጋ
እላለሁ ዛሬም አዲስ ዓመት
በኃጢአት ታጭቼ ለሞት።
በንስሐ በመታደስ
ወደ አምላኬ እንድመለስ
አብቅቶ የኃጢአት ዘመን
በልቼ ሥጋ ወደሙን
በአዲስ ዓመት አዲስ እንድሆን
አምላኬ ፈቃድህ ይሁን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Written By: admin
Date Posted: 9/16/2011
Number of Views: 15412
Return