አንቺ ትኖሪያለሽ
በዲ/ን አብነት አረጋ
የኑፋቄ ትምህርት እንክርዳድ ቢዘራ
ያሸነፈ መስሎት አሕዛብ ቢያቅራራ
ወጀብ ቢወጅብም ቢነሳ ዐውሎ ነፋስ
ውቅያኖስ ቢያናውጽ ዛፍን ቢገረስስ
ንውጽውጽታ በዝቶ ቢሰማ ነጐድጓድ
ሜዳው ቢጥለቀለቅ ተራራውም ቢናድ
እልፍ ቢኮበልል ጥርጥሩ በዝቶ
ሚሊዮኑ ቢክድ መከራውን ፈርቶ
ወይም ሌላው
ማስተዋል ቢያቅተው አዕምሮውን አጥቶ
ብኩርናውን ንቆ የምሥር ወጥ ጓጉቶ
ሊሸጥሽ ቢስማማ ሊኖር ሆዱን ሞልቶ።
የጥፋት ደመና ከሰማይ ቢያንዣብብ
ዝናቡ ቢዘንብ ወጀቡ ቢወጅብ
ምንም ቢመስላቸው የምትሰጥሚ በቅርብ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማናዊት መርከብ።
የእነ ጴጥሮስ እምነት ኰኵሐ ሃይማኖት
የቀጠቀጠባት የአርዮስን ክህደት
የተቀደሰችው የአትናቴዎስ እምነት
በፍጹም አትፈርስም ከቶም አትሞከር
የገፋሽ ሊወድቅ የቀሰጠሽ ሊያፍር
አፍራሽሽ ሊፈርስ ቀባሪሽ ሊቀበር
ቃል እንደገባልሽ አምላክሽ እግዚአብሔር
ትናንትን እንዳለፍሽ በወጀብ መካከል
ክር ላያቃጥል እሳት ሲንቀለቀል
ጸጥ እረጭ ሊል እሱ ሲቀሰቀስ
ማዕበል ቢነሳ ዐውሎ ነፋስ ቢነፍስ
በከሀዲ ክፋት ቢፈርስ መቅደስሽ
እሱ እንደፈረሰ አንቺ ግን እንዳለሽ
የዛሬው እንክርዳድ ወደ እሳት ተጥሎ
የዘመኑ ዑደት ሒደቱን ቀጥሎ
ጌታ እስከሚመጣ እስከ ምጽአት ድረስ
ስሙን እየቀደስሽ ክብሩን እያወረስሽ
አጥፊሽ እየጠፋ አንቺ ትኖሪያለሽ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Written By: admin
Date Posted: 10/18/2011
Number of Views: 16153
Return