View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: ስብከተ ወንጌል ::.. Register  Login
  

የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የትንሣኤ ድርሳን

እግዚአብሔርን የሚወዱ መንፈሳውያን ሰዎች ሁሉ በዚህ የትንሣኤ በዓል ደስ ይበላቸው፡፡ ጠቢባን (የእግዚአብሔር) አገልጋዮች ወደ ጌታቸው ደስታ ይግቡ፡፡ የጾምን ቀንበር ተሸክመው የነበሩ ዛሬ ዋጋቸውን ይቀበሉ፡፡

ከቀኑ በአንደኛው ሰዓት ጀምረው በሥራው ላይ ተሰማርተው የነበሩ ይምጡና ደመወዛቸውን ይቀበሉ፡፡[1]  ከሦስተኛው ሰዓት በኋላ የመጡ ማንኛቸውም (ሠራተኞች) የበዓሉ ዕድምተኞች በመሆናቸው ምሥጋና ያቅርቡ፡፡ ከስድስተኛው ሰዓት በኋላ የመጡም ቢሆኑ ዘግይተው የመጡ መስሏቸው አይፍሩ፡፡ ቸር የሆነው ጌታ በመጨረሻ የመጣውን ሳይቀር ቀድሞ እንደመጣ አድርጎ ይቀበለዋልና፡፡ በአሥራ አንደኛው ሰዓት የመጣውንም፣ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ሲደክም የዋለውንም (እኩል) ማረፊያ ይሰጣቸዋል፡፡ ኋላ የመጣውን(ም) ያገለግለዋል፡፡ ይሸልመዋል (ማቴ. 20፣ 1-16)፡፡ እውነት ነው ቀድሞ ለመጣው ያዝንለታል (ቀኑን ሙሉ ሲደክም ውሎ ጥቂት ከደከመው እኩል ተከፍሎታልና)፡፡ ስለ ድካሙ ግን ያመሰግነዋል፣ ያከብረዋል፣ ከፍ ከፍ ያደርገዋል፡፡ 
ሁላችሁም ኑ፣ ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ፡፡ አንተ ቀድመህ የመጣኸውም አንተ ኋላ የመጣኸውም እኩል (እኩል በአንድ መልክ) ዋጋችሁን ተቀበሉ፡፡ እናንተ ብርቱዎችም፣ እናንተ ደካሞችም ይህችን ዕለት እኩል አክብሯት፡፡ የጾሙን ወራት የጠበቃችሁም እንዲሁም መጠበቅ ያልቻላችሁም ዛሬ ግን በአንድነት፣ በቸርነቱ ደስ ይበላችሁ፡፡[2] እነሆ ማዕዱ ሙሉ ነው፡፡ የሰባው ፍሪዳ ተሰውቷል፡፡[3] ማንም እንደተራበ አይሂድ፡፡ ሁላችሁም የእምነትን ማዕድ ተቋደሱ፡፡ ሁላችሁም የቸርነቱን ብዕል (ሀብት) ተቀበሉ፡፡[4] ዛሬ በትንሣዔ ዕለት ማንም ስለ ድህነቱ አይዘን፡፡[5] ማንም ስለ ኃጢአቱ አያልቅስ፡፡ ምክንያቱም ሥርየተ ኃጢአታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቃብር ተገልጧልና፡፡ የመድኃኒታችን ሞት ነጻ አውጥቶናልና ከእንግዲህ ማንም ሞትን አይፍራ፡፡ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመታገስ ሞትን አጠፋው፣ ወደ ግዛቱ ወርዶ ሲዖልን ከንቱ አደረገው፡፡
ኢሳይያስ ይህንን ሁሉ ተመልክቶ ‹ሲዖል በመምጣትህ ታወከች› (ጌታ ነፍሳትን ነጻ ለማውጣት ወደ ሲዖል በመውረዱ) (ኢሳ.14፣9) አለ፡፡
ሲዖል ታወከች ምክንያቱም መሳለቂያ ሆናለችና፡፡
ሲዖል ታወከች ምክንያቱም ድል ተነስታለችና፡፡
ሲዖል ታወከች ምክንያቱም (ለ5ሺህ አምስት መቶ ዘን ያጋዘችውን ነፍስ በሙሉ ማርኮ) ባዶ አድርጓታልና (በርብሯታልና)፡፡[6]
ሲዖል ታወከች ምክንያቱም አሁን ምርኮኛ ሆናለችና፡፡
ሲዖል እርሱንም አስገባችው (እንደ ሌሎች ሙታን ሁሉ መስሏት)፡፡ ነገር ግን፣ ይደንቃል፣ ሲዖልም ከመንግሥተ ሰማያት ጋር ተገናኘች፡፡
የሚታየውን (የአዳም አምሳል ዳግማዊ አዳም ሆኖ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የመጣውን) ያዘችው፣ በማይታየው (በመለኮታዊ ሥልጣኑ ደግሞ) ድል ተነሳች፡፡
(እንግዲህስ ምን እንላለን?) ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲዖልስ ማሸነፍሽ የት አለ? (1ኛ.ቆሮ. 15፣55)፡፡ (ሁለታችሁም) ክርስቶስ በመነሣቱ ተደምስሳችኋል፡፡
ክርስቶስ ተነሣ ሰይጣን ተዋረደ፡፡
ክርስቶስ ተነሣ ቅዱሳን መላእክት ተደሰቱ፡፡
ክርስቶስ ተነሣ የሰው ልጅ ነጻ ወጣ፡፡
ክርስቶስ ተነሣ መቃብሩ ባዶ ሆነ፡፡
ክርስቶስ በመነሣቱ ለሞቱት ሁሉ በኵርና አርአያ ሆነ፡፡
            ኃይል፣ ክብር፣ ምሥጋና ለእርሱ ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡[7]


[1] ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን የሚጠቅሰው በማቴ 20 ከቁ.1-16 ላይ ያለውን ለወይኑ ሠራተኞችን የቀጠረውን ሰው ታሪክ ነው፡፡
[2] የሮሜ መልእክት ምዕራፍ 14ን ተመልከቱ፡፡
[3] መጽሐፈ ምሳሌ 9፣1-7 ‹ጥበብ ቤቷን ሠራች. . .ፍሪዳዋንም አረደች፣ የወይን ጠጇንም ደባለቀች፣ ማዕድዋን አዘጋጀች› ይላል፡፡
[4] ‹በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ፡፡› ት.ኢሳ.45፣3
[5] ‹እግዚብሔር ዙፋኑ በሰማይ ነው፡፡ ዓይኖቹ ወደ ድሃ ይምለከታሉ፡፡› መዝ. 10(11)፣4
[6] ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው ጌታችን በዕለተ አርብ በተሰቀለ ጊዜ ‹ሰላም ለእናንተ ይሁን› ብሎ ‹በሲዖል ላሉ ነፍሳት ሰበከላቸው› (1ጴጥ. 3፣19)፡፡
[7] Easter Homily ከሚለው ትምህርቱ የተወሰደ ነው፡፡ ትርጉሙ የቀና እንዲሆን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የራሴን ማብራሪያና ትርጉም ለመስጠት ሞክሬያለሁ፡፡ ጥቅሶች ያልተጠቀሱበትንም ማመሳከሪያውን ከመጽሐፍ ቅዱስ አቅርቤአለሁ፡፡ ከዚያ ባሻገር ያለው ግን የቅዱስ ዮሐንስ የትንሣዔ መልእክት ሙሉ ሐሳብ መስመር በመስመር የተተረጎመው ነው፡፡

Written By: host
Date Posted: 5/4/2008
Number of Views: 11620

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement