View in English alphabet 
 | Friday, April 19, 2024 ..:: ስብከተ ወንጌል ::.. Register  Login
  

ቤተልሔም እንሂድ ሉቃ ፪፥፲፭

በመላከ ሕይወት ቀሲስ ዕርገተቃል ይልማ

ትራክቱን ለማግኘት ይህን ይጫኑ

ቤተልሔም ማለት የእንጀራ ቤት ማለት ነው። ታሪካዊ ሥፍራ ናት። ዳዊትም ተወልዶ ያደገው፣ ለንጉሥነት የተቀባውና ቤተ መንግሥቱም የነበረው በቤተልሔም ነበር። ስለዚህ በእስራኤላዊያን ታሪክ ውስጥ ቤተልሔም የተወለደ «ቤተልሔማዊ ነኝ» ብሎ ራስን ማስተዋወቅ ክብር ነበረው። ቤተልሔም የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ሲከፈል ቀድሞ የነበራት ታላቅነትና ዝና እንዳልነበረ ሆኗል። ከነቢያት ወገን የሆነው ሚክያስ ለማስተማር ሲያልፍ ይቺ ስመ ጥር የሆነችው ከተማ ተፈትታ፣ ምድረ በዳ ሆና፣ ቋያ በቅሎባት ክብሯ ሁሉ ከላይዋ ላይ ተገፎ ተመለከታት። ከተማይቱ እንደዚህ ሆና እንደማትቀር በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ «አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ የይሁዳ ምድር፣ ከይሁዳ ገዥዎች ከቶ አታንሽም ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና» ሚክ ፭፥፪ ሲል ተነበየላት።

ይህም የነቢዩ ትንቢት ለጊዜው ተፈጽሞ ዘሩባቤል ነገሠባት። የነጋሪት ድምጽ ተሰማባት። ድንኳን ተተከለባት። የአብርሃም ልጆች እስራኤል ዘሥጋ ደጅ ጠኑባት። አሕዛብም መጥተው ገበሩባት። የትንቢቱ ፍጻሜ ግን ይበልጥ የጎላው ንጉሠ ሰማይ ወምድር የሆነ መድኃኔዓለም ሲወለድባት ነው። ያን ጊዜ ሠራዊተ መላእክት ከኖሎት ጋር በኅብረት ሲዘምሩ ተሰምቶባታል። የብርሃን ዓምድ ከሰማይ ወርዶ ተተክሎባታል። ከምሥራቅ ተነስተው የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው ኮከቡን ከምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናል። እያሉ እጅ መንሻ ዕጣን ወርቅ ከርቤን ገብረውባታል።

ትንቢተ ነቢያትን ጠንቅቀው የሚያውቁ መሢሑ መቼና በየት እንደሚወለድ ሱባኤ የቆጠሩ ጸሐፍት ፈሪሳያውያን ነበሩ። እነርሱ ከቤተልሔም አጠገብ ተቀምጠው ይህን ድንቅ አምላካዊ ሥራ ለማየት አልታደሉም። እነርሱ መሢሑን የሚጠብቁበት መንገድና መሢሑ የመጣበት መንገድ የተለየ ሆነ። «ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው» እንዲል ኢሳ ፶፭፥፱ መሢሑን እንደ አንድ የጦር መሪ ጄነራል ሠራዊት አሰልፎ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብሎ የሚመጣ አድርገው ጠበቁት። አንዳንዶችም ያለምንም ደም ጠብታ በተዓምራት እስራኤልን ከሮማዊያን ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት የሚመጣ ነጻ አውጪ አድርገው ጠበቁት። አንዳንዶችም በራሳቸው አመለካከት የመሲሑን መምጣት ተስፋ አደረጉ። እርሱ የሰውን ልጅ ሁሉ ከዘላለማዊ ሞትና ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት የሚመጣ መሆኑን አልተረዱም።


ሄሮድስ የካህናት አለቆችንና ጻፎችን ሰብስቦ ክርስቶስ በየት ይወለዳል? ብሎ ጠይቋቸዋል። የነቢያትን ትንቢት ጠንቅቀው የሚያውቁ ነበሩና በቤተልሔም ነው ብለው ለመናገር ምንም ጥርጥር አልነበረባቸውም። ከሩቅ ምሥራቅ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው የመጡ የጥበብ ሰዎች እንደነገሯቸው ወደ ቤተልሔም ሲሄዱ ከእነርሱ ጋር አብረው ለመጓዝ የተነሱ አልነበሩም። ሰማያዊው ንጉሥ በቤተልሔም እንደሚወለድ የነቢያትን ትንቢት ጠንቅቀው የሚያውቁ ተቀምጠው ትንቢተ ነቢያትን የማያውቁ ሰዎች ነገሩ በተፈጸመ ጊዜ ከቤተልሔም ደረሱ። እናውቃለን ብለው በዕውቀታቸው ለሚመጻደቁ የቤተልሔም ታላቅ ምሥጢር ተሰወረ። ይህን ድንቅ ምሥጢር ዮሐንስ አፈወርቅ «የወለደችህ እናትህ እጅግ አስደናቂ ነች። ጌታ ወደእርሷ ገብቶ አገልጋይ ሆነ። መናገር የሚችል ሆኖ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ዝም አለ። የሁሉ እረኛ ሆኖ በእርሷ ውስጥ ገብቶ እነደ በግ ሆነ። እያለቀሰ ወጣ የእግዚአብሔር በግ የሰውን ልጆች ኃጢአት ለማስተስረይ በበጎች መሐል በበረት ተገኘ»። ሲል ገልጾታል።


ቤተልሔም ቀድሞ ከነበራት ክብር የበለጠ አሁን ከበረች። ዳዊት ስለተወለደባትና ቅብዐ መንግሥትን ተቀብቶ ስለነገሠባት ብቻ ነበር ታሪኳ ገኖ የነበረው። ያም ቢሆን በኋላ ዘመን በደረሰባት ውድቀት የተረሳች እስክትመስል ድረስ ታሪኳ እንዳልነበረ ሆኗል። ጌታ በቤተልሔም ሲወለድ ግን በሩቅ ያሉ ሁሉ በኮከብ እየተመሩ መጥተውባታል። አስታዋሽ አጥታ ተረስታ የነበረችው ቤተልሔም ሰማያዊ ምሥጢር ተገልጦባታል። እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሳልና። በኃጢአት ወድቆ ታሪኩ ተበላሽቶ ዘላለማዊ ሕይወትን አጥቶ የነበረውን የሰው ልጅ ወደ ቀድሞ ክብሩ ይመለስ ዘንድ በቤተልሔም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የማዳን ሥራ ጀመረ። እነሆ የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደባት። ዳዊት ቢነግስ ደስታው ለእስራኤል ዘሥጋ ብቻ ነበር። አሁን ግን የክርስቶስ መወለድ የሚያስደስተው አሕዛብንም ጭምር ሆነ። የእግዚአብሔር መልአክ ለእረኛች «እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። ዛሬ በዳዊት ከተማ መደኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል» ሲል የጌታ መወለድ ደስታው የሰው ዘር በሙሉ መሆኑን ተናግሯል።


ዳዊት ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት በራእይ በኤፍራታ ምድር በቤተልሔም የአምላክ ሰው የመሆን ምሥጢር ተገለጠለት። ስለዚህም ወደ እርሷ በመንፈስ ሄደ ድምጹንም አሰምቶ «እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን» መዝ ፻፴፩፥፮ ሲል ተናገረ። እረኞች ከመልአኩ የምስራች ቃል እንደሰሙ እንዋል እንደር ሳይሉ «እንግዲህ እስከ ቤተልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔር የገለጠልንን ይህን የሆነውን እንይ ተባባሉ ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙት» ሉቃ ፪፥፲፭-፲፮ ወደ ቤተልሔም የሄዱ እረኞች ጌታን ከእናቱ ጋር አግኝተውታል። ስብአ ሰገልም ወደ ማደሪያው ወደ ዋሻው ገብተው ሰግደውለታል። ሳጥናቸውን ከፍተው ለዘላለማዊው ንጉሥነቱ ወርቅ፣ እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት ለሆነው ክህነቱ ዕጣን፣ የሰውን ልጅ ለማዳን ስለሚቀበለው መሪር ሞት ከርቤን ገብረውለታል። እኛም ዛሬ ወደ ቤተልሔም ልንሄድ ያስፈልጋል። ለምን ቤተልሔም መሄድ አስፈለገ ቢሉ፦


ቤተልሔም የእግዚአብሔር ፍቅር ተገልጦባታል።

ስለ ጌታችን፣ ስለ አምላካችን፣ ስለ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ማርያም መወለድ ብዙ ነቢያት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ የሁሉም የትንቢት ምሥጢር የሰው ልጅ የድኅነት ጉዳይ ነው። ሰዎች ወደዚህ ምድር የሚመጡት ለመኖር ነው እርሱ ግን ወደዚህ ዓለም የመጣው የሰውን ልጅ በሞቱ ሊያድን ነው። እናቱ ድንግል ማርያም እንደተወለደ አውራ ጣቱን ማሰርዋና በጨርቅም መጠቅለሏ ግንዘቱን ያመላክታል። የምሥራቅ ሰዎች ካቀረቡት እንጅ መንሻ ውስጥ አንዱ ከርቤ የሞቱን ምሥጢር ያስረዳል። እርሱ ሰው የሆነው ርቀን የነበርነውን ሊያቀርብ፣ ተለያይተን የነበርነውን አንድ ሊያደርግ ነው። በዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ገልጾታል። «እኛም አይተናል አባት ልጁን የዓለም መድኃኒት እንዲሆን እንደላከው እንመሰክራለን ...እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን አውቀናል አምነንማል» ፩ኛ ዮሐ ፬፥፲፬-፲፮።

የእግዚአብሔር የማዳን ምሥጢር ታይቶባታል።

ለሰው የተሰጠው የመዳን ተስፋ የተፈጸመው ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ በሚል አምላካዊ ቃል ኪዳን መሠረት ነው። ስለዚህም መዳን ነቢያት በትንቢታቸው አስቀድመው ተናገሩ። «ኃይልህን አንሣ እኛንም ለማዳን ና አሉ» መዝ ፸፱፥፪ የሰውን ልጅ ከዘላለማዊ ሞት ለማዳን ጌታ በቤተልሔም ተወለደ። ቅዱስ ያሬድ «በግርግም ተኛ በጨርቅም ተጠቀለለ በድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ የዓለም መድኃኒት ጌታ ዛሬ ተወለደ» ሲል ዘምሯል። ይህ የእግዚአብሔር የማዳን ምሥጢር እፁብ ድንቅ ነው መላእክትን ያስገረመ ሊቃውንትን ያስደነቀ ነው። ሰይጣን የሰውን ልጅ ከእግዚአብሔር የለየው በእባብ ተሰውሮ በመከረው ምክር ነው። ይህን የሰይጣንን ክፉ ሥራ መድኃኔዓለም ድል ያደረገው የሰውን ሥጋ በመዋሐድ ነው። «የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ» ፩ኛ ዮሐ ፫፥፰ እንደተባለ ሰይጣን ድል ተደርጓል።

ምስጋና ይገባታል።

ቀድሞ መላእክትና ሰው የተፈጠሩት እግዚአብሔርን አመስግነው ክብሩን እንዲወርሱ ነው። ከመላእክት ወገን የነበረውና የሌለውን ክብር በመሻቱ ወደምድር የተጣለው ሰይጣን የሰውንም ልጅ ከእግዚአብሔር እንዲለይ አድርጎታል። ጸጋው ተገፎ ክብሩም ጎስቁሏል። በዚህም የተነሳ ከእግዚአብሔር ጋር ሰው ሲጣላ የእግዚአብሔር ከሆኑ ሁሉ ጋር ተጣልቷል። ነፍስና ሥጋ ሰማያዊያንና ምድራዊያን ተጣልተዋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ሰላምና ዕርቅ ሰፍኗል። በኃጢአት ጨለማ የነበሩ የጽድቅ ብርሃን ወጥቶላቸዋል። ሠራዊተ መላእክት ከሰማይ ወርደው የሰውን ልጅ ደስታ በኅብረት ተጋርተዋል። ከእረኞች ጋር በመሆን «ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ» ሉቃ ፪፥፲፬ ብለው አመሰገኑ። ከጥንትም የተፈጠሩት አመስግነው ክብሩን ሊወርሱ ነውና።

የጌታ ልደት በሕይወታችን ውስጥ ትርጉም ሊኖረው ይገባል። በምዕራቡ ዓለም የዚህ ታላቅ በዓል ዓላማ እየተዘነጋ ገበያ ማድመቂያ ብቻ እየሆነ መጥቷል። እኛ ግን ወደ ቤተልሔም ልንሄድ ይገባል። እርሷም ቤተ ክርስቲያን ናት። ድኅነተ ሥጋና ድኅነተ ነፍስ በእርስዋ ይደረጋልና። የአምላክ ሰው የመሆን ምሥጢር ይነገርባታል። ስብሐተ መላእክት ይደመጥባታል። «አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፥ ሞቱም። ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ የሕይወት እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።» ዮሐ ፮፥፵፱-፶፩ ያለው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን በቤቱ ለመኖር እንዲያበቃን ፈቃዱ ይሁን። አሜን!


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Written By: admin
Date Posted: 1/1/2011
Number of Views: 8289

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement