View in English alphabet 
 | Friday, April 26, 2024 ..:: ስብከተ ወንጌል ::.. Register  Login
  

ስብከት


ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል
    ዕብ. ፲፩፥፬
(በመምህር ቀሲስ ስንታየሁ ደምስ ከሚኒሶታ)


መልእክቱ ለዕብራውያን የተጻፈ መልእክት ነው። ዕብራውያን የሚለው ስያሜ ምን አልባትም ከአብርሃም ቅድመ አያት ከነበረው “ከዔቦር” ስም የተመሠረተ ሊሆን እንደሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ። መልእክቱ የተጻፈበት ዘመን ሮማውያን የኢየሩሳሌምን ቤተመቅደስ ካፈረሱበት ከ70 ዓ.ም. በፊት በ60ዓ.ም. እንደሆነ ይነገራል።
በዕብራውያን ያሉትን መልእክታት ስንመለከታቸው በብሉይ ኪዳን ይከናወኑ የነበሩትንና ይደረጉ የነበሩትን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንዴት እና ምን ይመስሉ እንደ ነበር፣ እንዲሁም በአዲስ ኪዳን ያሉትን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችና አስተምህሮዎች ላይ ያተኮረ ነው::

የዕብራውያን መልእክትን የጻፈው ቅዱስ ጳውሎስ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምሁረ ኦሪት እንደመሆኑ መጠን ይህን መልእክት ለየት በማድረግ ጽፎታል “ለአባቶቼም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።” ገላ ፩፥፲፬ ብሎ እንዳለ።
አምላክ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ  ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ተወልዶ በኋላም ለሰው ልጆች ሲል ተሰቅሎ አዳምንንና ልጆቹን ከሞትና ከኃጢአት ቀንበር ነጻ ማውጣቱን በሐዋርያት የተሰበከውን ትምህርት ሰምተው የብሉይ ኪዳንን ሕግ ብቻ ጠብቀው የሚጓዙትን አይሁድን፣ እንዲሁም  ከአሕዛብነት ወደ ክርስትናው ገብተው የነበሩት ምዕመናንን ለማጽናናትና ለማበረታት፣ በአዲስ ኪዳን አምነው በመጠመቃቸውና በሕይወታቸው በመለወጣቸው እየደረሰባቸውና  እየከበባቸው ያለውን ፈተና በድል መወጣት እንዲችሉ የተጻፈ መልእክት ነው። ዙሪያቸውን የከበባቸውም ፈተና፣ መከራ፣ ስደት፣ እንግልትና መታሰር ወ.ዘ.ተ. ይህ ሁሉ  ወደ ክርስትናው ሕይወት  በመግባታቸው እንደሆነ በማሰብ ወደኋላ ተመልሰው አይሁዶች  ወደነበሩበት የአይሁዳዊነት ሥርዓታቸው፣  ከአሕዛብነት የተመለሱትም  ወደቀደመ ግብራቸውና ወደ ጣዖት አምልኮታቸው ተመልሰው እንዳይገቡ የሚበልጠው ክርስቶስ እንዳለ እየተቀበሉት ያለው ፈተናም ብዙ እንዳይደል ሊታገሱና ሊጸኑ እንደሚገባ  “ከኃጢአት ጋር እየተጋደላቸሁ ገና ደምን እስከማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁምና ።” ዕብ ፲፪፥፬ በማለት ጽፎላቸዋል።

በስሙ አምነው የተጠመቁትና እየተከተሉት ያለውን ከሙታን ተለይቶ ተነስቶ በክብር ያረገው ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት በላይ፣ ከመሪዎቻቸውና  ከመምህራኖቻቸው ከእነ ሙሴ፣ ከእነ አብርሃም፣ ከካህናቶቻቸውም ከእነ አሮን፣ ከእነ ኤሊ ከሌሎቹም ሁሉ በላይ እንደሆነና የበለጠውን መሥዋዕት ያቀረበ መሆኑን በማብራራት በአዲስ ኪዳን ላይ ስላለው ስለ አማናዊ መሥዋዕትና ስለሚበልጠው ሕግና ሥርዓት እንዲጠነቀቁ መክሯቸዋል።
በዚህ በምዕራፍ አሥራ አንድ ላይ አበው በሃይማኖት ያደርጉት የነበረው መንፈሳዊ ጦርነትና ውጊያ፣ ያገኙትን መንፈሳዊ ክብርና በረከት፣ እንዲሁም ፀጋ በመዘርዘር ይናገራል። በእምነት በተደረገ የመንፈሳዊ መሥዋዕት አቀራረብ ውስጥ ሊረሳ ስለማይገባው ሰለ ታላቁ ሰው አቤል “ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ አስከ አሁን ይናገራል።” በማለት ተናገረ፡፡

ዘወትር  ሊዘከሩ ከሚገባቸው መንፈሳውያን አባቶች መካከል አንዱ ስለሆነው በገዛ ወንድሙ ተገድሎ ሞትን የቀመሰውን አቤልን ማስታወስ እንደሚገባ፣ እንዲሁም ስለ መሥዋዕት አቀራረቡ፣ ያቀረበው መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት እንደመልካም መዓዛና  ዕጣን ሁኖ የተወደደውን መሥዋዕቱን ማስታወስ ሊኖርብን እንደሚገባ ጽፎአል። ለመሆኑ አቤል እንዲህ የተመሰገነው በምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ፦

፩. አብነት (አርአያ) የሚሆነው ሳያይ በመሥራቱ
የአቤልን መሥዋዕት ልዩ ያደረገው ነገር ቢኖር አብነት የሚሆነው ማንንም ማን ሳያይ ፍጹም የሆነ በጎ ሥራ በመሥራቱ ነው። ያለአስተማሪና መካሪ በሕገ ልቦና ተመራምሮና ተረድቶ ነቅዕ ጉድፍ የሌለበትን መሥዋዕትን ከሕሊናው አንቅቶ ከልቦናው አመንጭቶ ንጹሐ ባሕርይ እግዚአብሔር ንጹሕ ነገር ይወዳል በማለት የፈጠረውን እግዚአብሔርን ሲያከብር አብነት፣ አርአያ የሆነው ማንም የለም። አላገኘምም ነበር። ምነው አባቱ አዳም እናቱ ሔዋን አሉ እነርሱ አያስተምሩትምን ቢሉ እነርሱ እራሳቸው በድለው በመከራ፣ በግዞት፣ በውርደት ነውና ያሉት፤ እንዲሁም እንኳንስ በጎ ሥራ ሊሠሩ አምላክ ከሰጣቸው ክብር ተለይተው ነበርና። ሌላ ሰው ደግሞ እንዳያስተምረው ያን ጊዜ የነበረ ሰው አልነበረምና ስለዚህ በመሥዋዕቱ አስከ አሁን ይነገራል አለ።

፪. በመሥዋዕቱ
“አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አምላኩ በእምነት አቀረበ በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው መሰከረለት” ዕብ ፲፩፥፬። በእግዚአብሔር መልካምና በጎ ምርቃት የከበሩ አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት ተብለው በተመረቁት ምርቃት አቤልንና ቃየልን ወልደዋል። አቤል ኖላዊ አባግዕ (የበግ ጠባቂ) ነበር። ቃየል ደግሞ ምድርን የሚያርስ (ገበሬ) ነበር።
አቤልና ቃየል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ ቀረቡ አቤል ንጹሐ ባሕርይ እግዚአብሔር ንጹሕ ነገር ቢያቀርቡለት (ቢሰዉለት) ይወዳል ብሎ ቀንዱ ያልከረከረውን፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረውን፣ ጸጉሩ ያላረረውን ዓመት የሆነውን ጠቦት ሰውቷል። በዚህ ልዩ በሆነው መሥዋዕት “እግዚአብሔርን አስደስቷል እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ።” እንደተባለ ዘፍ ፬፥፬። እሳትም ከሰማይ ወርዶ በልቶለታል። በፍጹም መሥዋቱ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና።

፫.ምስክርነቱ ከእግዚአብሔር ስለሆነ
አቤል ልዩ በሆነው መሥዋዕት አቀራረቡና ችሎታው እንዲሁም ባለው የልቦና ንጹሕነት የአምላክን ቀልብ (ሕሊና) ስቧል። ለምን ቢሉ ከበደለና ካሳዘነ ከአዳም ተወልዶ በልጅነቱ የአባቱን አካሄድ ሳይከተል ለእግዚአብሔር የተመረጠና የሠመረ መሥዋዕት ማቅረቡ እጅግ የተወደደ አድርጎለታል። እግዚአብሔርም እንደተቀበለለት መሰከረለት። መሥዋዕቱ ውጫዊ የሚታይ መሥዋዕትን ወይም በግን ብቻ በመምረጥ የቀረበ አይደለም። ልቡናውን ከክፋት፣ ከቂም፣ ከቅንዓት ሁለ ያጠራ ነበር። በእርግጥም መዝሙረኛው ዳዊት እንዲህ አይደል ያለው “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፣ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” መዝ ፶፥፲፯። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ስለተመሰከረለት በመሥዋዕቱ እስካሁን ይናገራል አለ ።

፬. ስመ ጥሩነቱ አልቀረበትምና
አቤል ባቀረበው መሥዋዕት እግዚአብሔር ስለተቀበለለት ወንደሙ ቃየል ቢገድለውም፣ እግዚአብሔር ግን የአቤልን ክብርና ዝና ስመ ጥሩነት ለትውልደ ትውልድ መልካም መዓዛ ያለው መሥዋዕት ለማቅረቡ መታሰቢያው እንዳይጠፋ ከወንድሙ ከቃየል ይልቅ ገኖ ለዘላለም የሚኖር አደረገው። “የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል።” እንደተባለ መዝ ፻፲፩፥፮። አንዳንድ ሰዎች መልካም በመሆናቸው ሊታሰሩ፣ ሊሰደዱ፣ ሊገደሉ ይችሉ ይሆናል። ግን በእውነትና በጽድቅ ከሆነ ከአሳዳጁ፣ ከገዳዩ፣ ከአሳሪው በላይ ስማቸው ገኖ የሚሰማው የተበደሉት ሰዎች ለመሆኑ ዛሬም ያለን ሰዎች ምስክሮች ነን። እንዲህም ስለሆነ ነው ሞቶ ሳለ እስከ ዛሬ በመሥዋዕቱ ይናገራል ያለው። ምንም እንኳን ከዚህች ምድር በወንድሙ ገዳይነት ቢሞትም ታሪኩ፣ ዝናው፣ መታሰቢያው፣ ያደረገው ነገር ለዘላለም ለትውልድ ሁሉ ሲነገር ይኖራል። በእርግጥ ብዙ አቤል ተብለው የሚጠሩ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ማንም ሰው የወንድሙ ገዳይና ምቀኛ በሆነው በቃየል ስም ልጆቹም ሆነ እሱ እንዲጠራ ስም አያወጣም። ለምን? ታሪኩ የተበላሸ ሰለሆነ። አቤል ግን በስም ብቻ ሳይሆን በቤተክርሰቲያናችን ዋና ጸሎት በሆነው በቅዳሴ ጊዜ እንኳን “መሥዋዕተ አቤልን የተቀበልክ አምላክ መሥዋዕታችንና  ዕጣናችንና ልመናችንን ተቀበል” እየተባለ በእርሱ አምሳል የእኛንም ጸሎትና መሥዋዕት እንዲቀበልልን አንለምናለን። እንግዲህ ይህ ነው ሞቶ ሳለ ሕያው ሆኖ መኖር ማለት። ከሞት በላይ ስምና ታሪክ ገኖ ለዘላለም መቆየት።
አንተ ዛሬ በሕይወትህ እያለህ ሕሊናህ ያመነበትንና እውነት የሆነውን በመናገርህ ትናቅ፣ ትሰደብ፣ ብሎም ትዋረድ ይሆናል  ታሪክህ ግን እያደር እንደ አቤል እየገነነና እየተስፋፋ ስለሚሄድ ስለእውነት፣ ስለሃይማኖት፣ ስለቤተክርስቲያን፣ ስለሀገር ከመናገር ወደኋላ፣ በጎ ከመሥራትም ችላ የምትል ልትሆን አይገባህም። ለምሳሌ አቡነ ጴጥሮስ በዘመናቸው ባደረጉት የእውነተኝነትና የሃይማኖተኝነትን የሀገር ወዳድነት በጊዜው የሰማዕትነት ሞት ተቀብለው ቢያልፉም እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ነውና ታሪክ እንደገና አንስቶ በስማቸው ቤተክርስቲያን እንዲሁም ሰው ሁሉ በሚያየው ቦታ ሐውልታቸው ተተክሎ ታሪካቸው እንዲወሳና እንዲነገር ሆነዋል። ይህ ነው እንግዲህ ሞቶ ሳለ በመሥዋዕት አስከ ዛሬ መናገር ማለት ።

፭. ከውስጥ የመነጨ ሥጦታ ስለነበር
ከላይ እንደተመለከትነው አቤል ከውጪ በሚታይ ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ በጉን ብቻ በማሳመር አላቀረበም። ከሚቀርበው መሥዋዕት በፊት ልዑል አምላክ ስለሚያየው እሱነቱ አውቆና ተረድቶ ንጹሕ ሕሊናን ይዞ መቅረብ ነው የቻለው። ነቢዩ ኢሳይያስም እንዲህ እንዳለ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እኔ ወደ ትሑት መንፈሱም ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።” ኢሳ ፷፮፥፪።
ዛሬ የብዙዎቻችን ችግር የሚሆነው ነገር ቢኖር በእግዚአብሔር ፊት የሚታይ ሥጦታ ወይም መሥዋዕት የቅኔ፤ የቅዳሴ፣ የዝማሬ፣ የስብከት፣ የልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ብቃት ከክፋትና ከቅናት፣ ከቂምና ከጥላቻ ያልራቀ አገልግሎት በማገልገል ብቻ ውስጡን ሳይሆን ውጪውን ብቻ ያጠራ የተርዕዮ ግልጋሎት ማገልገልን ተያይዘነው የምንታየው። ይህም በመሆኑ ነው ወደ እግዚአብሔር መንበር ደርሶ ለለመንነው ጸሎታችን  ዋጋን፣ ለተሳልነው ስለታችን መልስን ሊያመጣልን ያልቻለው። ስለዚህ ሁላችንም አንደ አቤል የጠራና የነጻ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ልንጨነቅ ይገባል። የምናቀርበው መሥዋዕት በአምላካችን ፊት የከበረ እንዲሆንና መልካም ሆኖ እንዲቀበልልን ከቂም፣ ከበቀል፣ ከተንኮል፣ ከቅናት፣ ከምቀኝነት… ልቦናችንን ማንጻት ይጠበቅብናል።
  ታዲያ በዘመናችን ብዙ የምናቀርባቸው መሥዋዕቶች አሉ። የቅዳሴ፣ የዝማሬ፣ የቅኔ፣ የስብከት፣ የገንዘብና ሕዝብን የማስተዳደር (የመምራት) የጉልበት  አገልግሎቶች።  እነዚህ መሥዋዕቶች እንደ አቤል መሥዋዕት ለምን መናገር አልቻሉም? መለያየትን፣ ዘረኝነትን፣ መነቃቀፍን፣ መተቻቸትን፣ ጥላቻን፣ ልዩነትን፣ ጎሰኝነትን አውጥተው ጥለውልን በአንጻሩ ሠላምን፣ በረከትን፣ አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ ፍቅርን ፣ ሕብረትን  ለምን አላመጣልንም? ጉድለቶች ስላሉብን ነው። እነዚህም፦

፩.  ፈሪሀ እግዚአብሔር መጥፋት
መዝሙረኛው ዳዊት ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።” ብሏል መዝ ፻፲፥፲። በእርግጥም ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ሰው የታዘዘውን ማድረግ ይናፍቃል። የታዘዘውንም በአግባቡና በሥርዓቱ ይፈጽማል። ይኸውም ከፍቅር ነው። አባታችን አብርሃም ለእግዚአብሔር ያደረገው እንዲህ ነበር በእርጅና የወለደውን ልጅህን ሰዋልኝ በተባለ ጊዜ ልጁ ይስሀቅን ለመሠዋት ወደ ሞሪያም ተራራ ወሰደው በዚያም እንደሚሰዋው ለልጁ ነገረው። ሊሰዋውም በመሰዊያው ላይ አስተኛው እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለው “በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ አንዳችም አታድርግበት፣ አንድ ልጅህን ለእኔ አልሳሳህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁና ።” ዘፍ ፳፪፥፲፪። በእርግጥም አብርሃም እግዚአብሔርን መፍራቱን ያረጋገጠው በመታዘዝ እና አቅርብ የተባለውን በማቅረብ ነው እኛስ ዛሬ ቤተመቅደሱን፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነችው ቤተክርስቲያንን እናከብር ይሆን? እሱ ለይቶና ቀብቶ የእርሱ እንደራሴ አድርጎ የሾማቸውን አገልጋይ ካህናቶችንስ እናከብር ይሆን? ቢያጠፉና ቢበድሉስ ገበና ሸፋኝ ሆነን ይሆን ? ወይስ ሰድቦ ለሰዳቢ፣ ተናግሮ ለተናገሪ እንዲሁም መሳቂያና መሳለቂያ እንዲሆኑ አድርገን ይሆን? ጌታ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል “ልጅ አባቱን፣ ባሪያም ጌታውን ያከብራል እኔስ አባት ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ት. ሚል ፩፥፮። ለመሥዋዕታችን መልስ እናገኝ ዘንድ ፈሪሀ እግዚአብሔር በሁላችን ሕይወት ይኖር ዘንድ ያስፈልጋል።   

፪. ነቃፊ በመብዛቱ
እንቅፋት የሚመታው ሰው ሲራመድ እንጂ ሲቀመጥ እንዳይደለ ሁሉ ለመሥራት፣ ለማገልገል፣ የሚንቀሳቀስ ሰው እንቅፋት (መሰናክል መጥቶ ሊጥለው) ይችላል። ነገር ግን መሳሳቱን ከማረም ይልቅ ደግሞ እየነቀፉ መኖር ደግሞ የክርስትና መንገዱም አካሄዱም አይደለም። ሰው በሠራው ሥራ ተመስግኖ ባጠፋው ጥፋት ደግሞ ሊወቀስ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስም ያስተምረናል። በዮሐንስ ራእይ በምዕራፍ ፪፥፩-፭ እንደዚህ ተብሎ እንደተጻፈ “ሥራህንና ድካምህን ትዕግስትህንም አውቃለሁ… የምነቅፍብህ ነገር ደግሞ አለኝ” በቅድሚያ ስለነቀፌታው ሳይሆን እየቀረበለት ያለው መልካም ጎን ነው። ከዚያ የሚነቀፍበት ነገር ተነግሮታል። ዘመናችን ግን የሚያሳዝነው ከዚህ በተገላቢጦሽ እየሆነ ነው። አንድን ሰው መልካም ያደረገውን ነገር ሁሉ ወደ ጎን በመተው መንቀፍ ብቻ የተያያዝንበት ዘመን ነው። ምንአልባት ይኽ ለሰውየው ካለን ጥላቻ የተነሳ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ግን አግባብ አይደለም።
ይኽም የሚያመጣው ነገር የሌላውን መልካም ሥራ ሁሉ እንደ በጎ አለመመልከት፣ የሌላውን ሰው ደካማ ጎኑን እንጂ ብርቱ ጎኑን አለመመልከት፣ ይህ ጎደለህ፣ ያ ጎደለ፣ ይህ የለውም፣ ያ የለውም፣ ብሎ ሁል ጊዜ ለወቀሳ ብቻ መዘጋጀትን ያመጣል። እንዲህ ዓይነት ጉዞ የሚጓዝ ሰው በግልም ይሁን በቡድን ወይም በማኅበር ከቅድስና ውጪ የሆነን መንገድ ይዞ መጓዝ እንደሆነ ሊመረምር ይገባዋል። ሰው ከቅድስና የራቀ ሕይወትን መያዝ ከጀመረ የተመቸውን አጽድቆ፣ ያልተመቸውን ኮንኖ መኖርን እንደ ትክክለኛ መንገድ አድርጎ ይቆጥረዋል። “ሕዝቤ ኃጢአት መብል ሆኖባቸዋል ልባቸውንም ወደ በደላቸው አድርገዋል። እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፣ በመንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፣ ሥራቸውንም እመልስባቸዋለሁ። እግዚአብሔርንም መጠበቅ ትተዋልና ሲበሉ አይጠግቡም ሲያመነዝሩም አይበዙም።” ት. ሆሴ ፬፥፰ እንደተባለ ዛሬ በየድረ ገጹና በየመጽሔቶችና በየጋዜጦች የምናየው መሰዳደብ፣ መነቃቀፍ፣ መተቻቸት፣ በሃይማኖት ካለን  ከክርስትያኖች  የሚጠበቅ አይደለም። ነገሩ የትንቢት መፈጸሚያዎችን ለመሆናችን ቀድሞ  አንደኛችንም እያስተዋልነው አይደለም። “አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ ልጆች አባቶቻቸውን ይበላሉ።” እንደተባለ ት. ሕዝ ፭፥፲። በሃይማኖት ለመኖራችን ምስክሩ መቻቻል፣ መተራረም፣ ገበና መሸፋፍን እንጂ  በየጋዜጦች በየድረ ገጾች መነቃቀፋችን፣ መሰዳደባችን አለመሆኑን ልናውቅ ይጠበቅብናል። “ወንድሞች ሆይ እርስ  በርሳችሁ አትተማሙ ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል፤ በሕግም ይፈርዳል በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም።” እንዳለ ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ ያዕ ፬፥፲፩ ታዲያ እኛ ያልፈረድንበት፣ እኛ ያልኮነንነው ማንን ይሆን? አሁንማ ድካሙ እየበረታ መጥቶ ከመቅደስም፣ ከውጭም፣ ከምዕመናንም፣ ከካህናትም እየሆነ ለሰሚ ጆሮ ጭው የሚያደርግ ብሎም በሃይማኖት ላለ ሰውም አንገት የሚያስደፋ ነገር እየሆነ መጥቷል። የአቤል መሥዋዕት ግን ከሰው ፍርድ የነጻች ናትና መሥዋዕታችን እንደ እርሱ እንዲሆንልን ከመነቃቀፍ ገደልና ኃጢአት መውጣት ይገባል።

፫. ለራሳችን ክብር ብቻ መጨነቃችን
ዘመናችን እጅግ በቁጥር በሚያዳግት ውስጥ አደጋ ላይ እየጣለን ያለው ነገር ቢኖር የራሳችን ክብር፣ ዝና፣ ስም፣ ለመጠበቅ ብቻ መጓዛችን ነው። ይኽም ንጹሕ የሆነ አገልግሎትን እንዳናበረክትና እንዳናገለግል ስለቤተክርስቲያናችን እንዳንጨነቅ እያደረገን ነው። አሁንም ሊያስጨንቀን የሚገባው የቤተክርስቲያነችን ጉዳይ ሊሆን ይገባል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አንዳለ “ልጆች ሆይ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሳል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንት ምጥ ይዞኛል።” ገላ ፬፥፲፱። አሁን በብዙም ይሁን በጥቂት ሁላችን ለተጠራንበት ኃላፈነት ስለቤተክርስቲያን ክብር ስንል ልናደርገው ይገባል። “በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ ስለ ሥራችሁ ክፋት ቁጣዬ እንደ እሳት እንዳይሆን የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳይቃጠል፣ ለእግዚአብሔር ተገረዙ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ” እንደተባለ ት. ኤር ፬፥፬ ክብራችንን ጥለን ለእግዚአብሔር እና ለቤተክርስቲያን ክብር መጨነቅ ይኖርብናል ያን ጊዜ ዘላለማዊ እግዚአብሔር እንደ አቤል መሥዋዕት አድርጎ ይቀበልልናል።

እንግዲህ ከላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገርው አቤል ሞቶ ሳለ እስካሁን በመሥዋዕቱ ይናገራል እንዳለው የማይጠፋ ታሪክ ለትውልድ ፤ ክብር፣ ሃይማኖት፣ ሀገርን፣ ሥርዓትን ማስተላለፍ እንዲቻል መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ ሥራ ስለሆነ በተቻለ መጠን መሥዋዕትነት ለመክፈል ልቦናችንን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። አባቶቻችን አበው መሥዋዕትነትን ከፍለው ያቆዩልንን የቤተክርሰቲያን አደራ እኛም ለሌላው ማስተላለፍ ይኖርብናል። አቤል ለድኅነት ምክንያት የሚሆነው ሳይኖር የሚናገር መሥዋዕትን አቀረበ። እኛ ግን ቀድሞ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን አዋርዶ በሥጋ አዳም ተገልጦ አስተምሮን  ሞቶ ተሰቅሎ ታሪካችንን ቀይሮ ፤ በኋላም ምሳሌ መስለው ሃይማኖት አጠንክረው ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ፣ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ ጽድቅ መልሰው የሚያስተምሩ ሐዋርያትን እንዲሁም በዘመናችንም ደግሞ የሚመክሩ መምህራነ ወንጌልና ካህናተ አባቶች ስላሉን እርስ በእርስ መወነጃጀሉን ትተን ከውጭ የሚመጣብንን ክፉ ጠላት ማሸነፍ የምንችልበት ኃይላችንን አጠናክርን ስለ ቤተክርሰቲያናችንና ስለ ሥርዓተ ቤተክርስቲያናችን አበውም ስለ የዋሃን ምዕመናን በጎቻችን ልንጨነቅ ይገባል። ምዕመናንም በአባቶች ትዕዛዝና ሕግ ተመርተን የማታልፈውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚያበቃንን መልካም ሥራ ልንሰራ ይገባል ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካልና ባለንበት ጊዜ መልካምና ቅን ሰውነት ይዘን በመንፈሳዊ መነቃቃት ያለብንን ኃላፊነት ሁላችንም እንደየደረጃችን እንወጣ ዘንድ የቅዱሳን አምላክ ይርዳን።

                             ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር


ጥቅምት ፲፰ /፳፻፪ ዓ.ም.

Share |

Written By: host
Date Posted: 1/28/2011
Number of Views: 8919

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement