View in English alphabet 
 | Wednesday, April 17, 2024 ..:: ስብከተ ወንጌል ::.. Register  Login
  

“ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ” /ኤፌ ፭፥፲፭-፲፯/

በዲ/ን አብነት አረጋ


“በቸርነትህ ዓመት ታቀዳጃለህ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል ኮረብቶች በደስታ ይታጠቃሉ። ማሠማሪያዎችም መንጎችን ለበሱ ሸለቆዎችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምሩማል”  /መዝ ፷፬(፷፭)፥፲፩-፲፫/
እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አሸጋገርዎ!

ቀናት ወቅቶችና ዓመታት  የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ የተገለጠባቸውና የሚገለጥባቸው ሥራዎቹ ናቸው። /ዘፍ ፩፥፲፬፤ ፰፥፳፪/ እያንዳንዷ ቀን እግዚአብሔር የሠራት ናት። /መዝ ፻፲፯፥፳፭/ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት  “አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።” /መዝ ፻፪፥፳፯/ ሲል እንደመሰከረው ዘመናትና በዘመናት ዑደት የሚሳፈሩ የሰው ልጅና መላው ፍጥረታት ሲያልፉ የዕለታትና የአዝማናት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ግን ሁሉን በማሳለፍ ሁሌ አዲስ ሆኖ ይኖራል።

የቸርነት ባለቤት እግዚአብሔር ዓለም ከምንጊዜውም በላይ በኃጢያታችን የረከሰች ብትሆንም በምሕረቱ ታግሶ አዲስ ዓመት በእድሜያችን ላይ በመጨመር የንስሐ እድልና ጊዜ በመስጠት በኢትዮጵያዊያን የዘመን አቆጣጠር 2003 ዓ.ም. ተቋጭቶ 2004 ዓ.ም. የምንቀበልበት የአዲስ አመት ቀዳሚ ዕለት ላይ አድርሶናል።

በዓሉን ለምን እናከብራለን? እንዴትና በምንስ አግባብ ማክበር አለብን ከሚሉ ቁልፍ ጥያቄዎች በፊት የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር መሰረትና የልዩነቱን ምክንያት እንመልከት፦
 
የኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር መሠረቱና የልዩነቱ ምክንያት

የኢትዮጵያ አብዛኛው የኪነ ጥበብ፣ የሥነ ሕንፃ የሥነ ጽሑፍ የአስተዳደርና ሌሎች ሥልጣኔዎች ምንጭ የሆነችው የኢ/ኦ/ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የቀመሩ ባለቤት ነች። ቤተክርስቲያናችን ከሌሎች ሀገራት /አብያተ ክርስቲያናት/ የዘመን አቆጣጠር ተለይታ በ7 ዓመት ልዩነት የተቀመረ የዘመን አቆጣጠር ባለቤት ናት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን ዘመኑን ለመቀመር መነሻ ያደረገችው አዳም ከገነት ወጥቶ በባርነት የነበረበትንና እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ሰውን ለማዳን ቀጠሮ ያደረገውን 5500 ዓመታት ነው። እግዚአብሔር ይህን ቀጠሮውን በዕለትና በሰዓታት እንኳን ሳያሳልፍ እንደፈጸመ ሁሉ ቤተክርስቲያንም የዚህን ዘመን ፍጻሜ የዓመተ ምሕረት መነሻ አድርጋ ተጠቅማዋለች። 

በሌላ በኩል አብዛኛው ዓለም የሚጠቀምበት የምዕራባውያኑ የዘመን አቆጣጠርን የቀመረው ሮማዊ መነኩሴ ዴዮናስዮስ ለቀመሩ መነሻ ያደረገው ታሪካዊ ክስተቶችን በተለይም የሮማን ከተማ የምስረታ ዕድሜ በመሆኑ ለልዩነቱ ምክንያት ሆኗል። /መሪጌታ አዕምሮ ጌታሁን የኢትዮጵያ ፈደል፣ ታሪክና ክፍለ ዘመን ገጽ 31-32፤  ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ፊደል ገጽ 57/

የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ከሌሎች ለምን ተለየ?

እስራኤላውያን ከግብፅ የባርነት አገዛዝ ነፃ የወጡበትን የሚያዝያ ወር የዓመቱ የመጀመሪያ ወር አድርገው እንዲያከብሩ በሙሴ አማካኝነት ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት ሚያዝያን የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ወር አድርገው ያከብራሉ። ምዕራባውያኑ የጥርን ወር የዓመቱ የመጀመሪያ ወር አድርገው ይጠቀማሉ።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን ደግሞ ፍጥረተ ዓለምን የዘመን አቆጣጠር መነሻና መሠረት በማድረግ እግዚአብሔር ፍጥረተ ዓለምን የፈፀመበትን ወርሃ መስከረም የመጀመሪያ ወር አድርጋለች። /አለቃ አያሌው ታምሩ  “የኢትዮጵያ እምነት በሶስቱ ሕግጋት”/  

የበዓሉ መጠሪያ

በዘመን ዑደት አሮጌው አልፎ አዲሱ ዓመት የሚጀመርበት የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን መስከረም አንድ ከሀገሪቱ ብሔራዊ በዓላት አንዱ ሆኖ ይከበራል። ዕለቱ በተለያዩ መጠሪያዎች የሚጠራ ሲሆን ስያሜዎቹ ከእምነትና ታሪክ ጋር የተሰናሰሉ ምክንያቶች አሏቸው።

ሀ. የዘመን መለወጫ
    አሮጌው ዘመን ተቋጭቶ አዲሱ ዘመን የሚጀመርበት /የሚለወጥበት/ የሽግግር ዕለት በመሆኑ በዚህ ስያሜ ይጠራል።

ለ. ቅዱስ ዮሐንስ
    መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ያረፈው መስከረም ሁለት ቀን ቢሆንም ይህ ዕለት በስሙ ይጠራል። ቅዱስ ዮሐንስ ከክርስቶስ በፊት እንደነበሩ ነቢያት ሁሉ “ይመጣል” ብሎ መውረድ መወለዱን የተናገረ ነቢይ ነው።/ማቴ ፫፥፩-፲፩/ እንዲሁም የጌታን መውረድ መወለዱን እርሱም አምላክ ወልደ አምላክ እንደሆነ የመሰከረ ሐዋርያ /ዮሐ ፩፥፲፱-፳፫/ በመሆኑ የዘመን ሽግግር ድልድይ ሆኖ መጠራቱ የተገባ ነው።

ሐ. ርዕሰ ዐውደ ዓመት
    በዓመቱ የዕለታት መጀመሪያ ቀን የሚከበር በዓል በመሆኑና የሌሎች በዓላትና አጽዋማት ስሌት የሚሠራበት  የበዓላት ራስ /መጀመሪያ/ ለማለት በዚህ ስም ይጠራል። 

መ. እንቁጣጣሽ
    እንቁ ዕፅ አወጣሽ ከሚለው ቃል የተገኘ ሲሆን ሜዳና ተራራው በአበባ በሚያጌጥበት በመስከረም ወር የሚከበር በመሆኑ በዚህ ስም ሊጠራ ችሏል።

የዘመን መለወጫን በዓል ለምን እናከብራለን?

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት ሐሤትንም እናድርግ በእርስዋም ደስ ይበለን” /መዝ ፻፲፯፥፳፭/ ሲል እንደገለጸው እግዚአብሔር ዘመናትን በመቀየር ዓመታትን በማቀዳጀት ለሰው ልጆች እድሜና የንስሐ ዕድል በመስጠቱ አሮጌውን ዘመን በመሸኘት አዲሱን ዘመን ስንቀበል በደላችንና ክፋታችን ሳይቆጥር በቸርነቱ ለዚህ ላደረሰን፤ አዲስ ዘመንን ለሥራ ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ልናቀርብ ያስፈልጋል።

ጊዜያት የእግዚአብሔር ሥጦታዎችና የሕይወት ዘመን መለኪያ በመሆናቸው ክቡር ናቸው። አዲሱን ዓመት በድምቀትና በታላቅ ዝግጅት የምናከብረው ከፈጣሪያችን ጋር ያለንን ቃልኪዳን ለማደስ ፣ የራሳችንን የሕይወት ጉዞ ለመመርመር፣ በመንፈሳዊ ኑሮአችን እድገት ለማምጣት ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥርልን ነው። ይህም ሲባል የሰው ልጆች ዘመኑን እንደ እግዚአብሔር ሃሳብ ወደ ልቦናችን ተመልሰን ያለፈ በደላችንን አይተን የዛሬ የእምነት አቋማችንን አስተካክለን ነገን ብሩህና የስኬት ቀን ለማድረግ መሥራት የምንጀምርበት ነው ለማለት እንጂ ዘመኑ በራሱ ስኬት ይዞ ይመጣል ማለት አይደለም።

ክርስቲያን ለመዳን ቀጠሮ አይሰጥም ለዚህ ነው ሐዋርያው “የመዳን ቀን ዛሬ ነው” /፪ኛ ቆሮ ፮-፪/ ያለው ዛሬን የመዳን ቀን ለማድረግ የትላንትናን አኗኗር መፈተሽ ዛሬን የለውጥ ቀን ማድረግ ነገን የዛሬው የለውጥ ሀሳብና ድርጊት የምንቀጥልበት እንዲሆን ማለም ያስፈልጋል።

ስለዚህ ዘመናት ሲቀየሩ ዓመታትንም ስንቀዳጅ የትናንቱ አኗኗራችን ምን ይመስላል? ዛሬ ላይ ምን መወሰን አለብን? ጉዞአችን ወዴት ነው? መድረሻችንስ? ያለምነው ቦታ ለመድረስ ምን እንሰንቅ ምንስ እንታጠቅ? ብሎ ከራስ መክሮ ከራስ ቃል በመግባባት ጉዞ የምንጀምርበት እንጂ በመጠጥና በስካር በጭፈራና በሆይታ የምናሳልፈው የባከነ ዕድሜያችን አካል መሆን የለበትም። 

ትናንት ወይም የቀደሙትን ዘመናት እንዴት ኖርን? ዘመናቱ አለፉን ወይም ሰርተን አለፍንባቸው?

ሰው በተሰጠው ዕድሜ በሥጋውና በነፍሱ የሚጠቅም በጎ ሥራ ሠርቶ ሀገርን ወገኑን ቤተክርስቲያንን ጠቅሞ እግዚአብሔርን ያላስደሰተበት ዘመን የባከነ ዘመን ወይም የተቀበረ የጊዜ መክሊት ነው። ብዙዎቻችን ዓመታትን ከመቁጠር ያለፈ በዘመናቱ የዑደት ሀዲድ ተሳፍረን መድረስ የሚገባን ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ የደረስን አይደለንም።  ስለዚህ ኃላፊው ጊዜ ወይም ትናንት ኖረብን እንጂ ኖርንበት ማለት ይቸግረናል።  በእርግጥ የተሰጣቸውን ዕድሜ በጠቃሚ አግባብ አሳልፈው በነፍስም ሆነ በሥጋ መክሊታቸውን ያራቡ/ያተረፉበት/ የሉም ማለት ደግሞ አይቻልም።  ለዚህ የበቃውን በኖረበት አኗኗር ያጽናው ማለት ይገባል።  “ቀኖቻቸው በከንቱ አለቀ ዓመቶቻቸውም በችኮላ” /መዝ ፸፯፥፴፬/ እንደተባለው በየራሳችን የኅሊና ከሳሽነት በየኅሊናችን የፍርድ ችሎት ፊት የቆምንና ያለፈውን ዘመን ባለመኖር ወይም ለኃጢአት በመኖር እንዳጠፋነው በራሳችን ኅሊና የፈረድን ግን እስከ መቼ? እንበል። ያለፈው አልፏል አምላክ ላባከንነው ዘመን የሰጠንን ይቅርታ አዲስ ዘመን በመስጠት ገልጾታል። 

 “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራት በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክ በመጠጣት ነውር ባለበት በጣኦት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል” /፩ኛ ጴጥ ፬፥፫-፬/ እንዳለው ሐዋርያው በዚህ አይነት አኗኗር ያለፍን በቃን ብለን እንወስን:: 

መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ የብሉይ ኪዳን ዘመን ተፈፅሞ በሐዲስ ኪዳን የሰዎች የነፃነት ዘመን ሲጀመር ከዓመተ ፍዳ /ዓመተ ኩነኔ/ ወደ ዓመተ ምሕረት የሚደረገው ሽግግር አብሳሪ /አዋጅ ነጋሪ/ ሆኖ በተገለጠበት ዘመን አሮጌውን ማንነት ፈትሸን ረብ የለሹን የኃጢአት ሸክም ጥለን በቅድስናና በመልካም አዕምሮ ወደ አዲሱ ዘመን እንድንገባ “እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” እያለ የሰበከው ስብከት ዛሬ ከፍ ብሎ ሊደመጠን ይገባል።

ዛሬ የሃይማኖት /የጽድቅ/ ፍሬ ጎድሏል።  ሰላም በሁሉም ሥፍራ የለም።  ስለ ባልንጀራ ስኬት ከመጨነቅ የውድቀቱን ጉድጓድ መማስ፣ ከማስታረቅ ማጣላት፣ ከመታመን ስርቆት … ወዘተ በርክቷል። ለህግና መልካም ሕሊና ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ፈቃድና ሕግጋት የሚቃረንን ነገር መሥራት የሚያስመካበት ዘመን ላይ ደርሰናል።  እንዲህ ያለውን  እድፍ ተሸክሞ አዲሱን ዘመን በመቀላቀል አዲስ ዓመት ብሎ መጥራት በራስ ላይ መቀለድ ነው የሚሆነው።  በእንደዚህ አይነት አኗኗር ዘመናቸውን ላባከኑ የኤፌሶን ምእመናን መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ ብዕር “አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሳ ክርስቶስም ያበራልሃል” ብሏል /ኤፌ ፬-፭/ ነቃን እያልን ለተኛን ኖርን እያልን ሞተን ያለፍነውን የዕድሜ ዘመናችን የጽድቅ ፍሬ ሳናፈራ ለንስሐም ሳንበቃ ላባከንን ምንኛ የተስማማ ነው።

የተሰጠን ትንሽ ዕድሜ /የጊዜ መክሊት/ በምግባርና በሃይማኖት ፍሬ አፍርተን መጭውን ዘላለማዊ ሕይወት የምንወርስበት እንጂ በሞት በተመሰለ የበደል አኗኗር ቀብረነው ዘላለማዊውን ሕይወት አጥተን ከሞት ወደ ዘላለማዊ ሞት የምንሸጋገርበት ሊሆን አይገባም /ማቴ ፳፭፥፳፬-፴/

የተቀዳጀነው አዲስ ዓመት በሥራችን ሳይሆን በቸርነቱ የተሰጠን ተጨማሪ ዕድሜ ነው። እንደ መንገድ ዳሯ በለስ በልምላሜ ተውበን ፍሬ እንዳይታጣብንና ለእርግማን እንዳንሆን /ማቴ ፳፩፥፲፰-፲፱/ ወይም እንደ ሰነፎቹ ደናግላን ጌታ እስኪመጣ ይዘገያል ብለን በውስጡ ዘይት የሌለው መብራት በመያዝ በመዳናችን ጉዳይ አንዘናጋ /ማቴ ፳፭-፲፫/ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ እንዳለ “ምሳር በዛፍ ሥር ተቀምጧል መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። /ማቴ ፫-፱-፲/ በተሰጠን ዕድሜ ፍሬ ለማፍራት እንሥራ።

እንግዲህ ምን እናድርግ? /የሐ ሥራ ፪፥፴፯/

በበዓለ ሃምሳ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ባስተማረው የእግዚአብሔር ቃል ልባቸው የተነካ ወገኖች “ምን እናድርግ” እንዳሉ እኛም ዛሬ ምን እናድርግ ካልን ዘመኑ አዲስ የለውጥና የስኬት እንዲሆነ ሰው ራሱን ጠይቆ የኖረበትን አኗኗር ለመተው በመወሰን ውሳኔውንም በመተግበር ዘመኑን ልንቀበለው፤ ዓመቱንም አዲስ ልንለው ይገባል።  ያዕቆብ ወደ ቤቴል ከመውጣቱ በፊት እርሱና አብረውት የነበሩ ቤተሰቦቹ የያዟቸውን ባዕዳን አማልክት እንደቀበሩ ለክርስትና የማይስማማ ደባል ጠባያችንን እንቅበር። ያደፈውን የርሱንና የቤተሰቡን ገላ በመታጠብ እንዳነፃ በንስሐ እንባ በመታጠብ እንንፃ። ያዕቆብና ቤተሰቦቹ ንፁህ ልብስ በመልበስ ወደ ቤቴል እንደወጡ እኛም በአዲሱ ዓመት  የንፁሐ ባህሪ ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል ክርስቶስ ኢየሱስን እንልበስ /ዘፍ ፴፭÷፩-፭/

ትናንት ባክኖ አልፏል። ትናንት ያልተሠራ ሥራችንም አብሮ ዛሬ ከኛ ጋር ነገ ደግሞ ከፊት አለ።  ዛሬ ትናንት ሳይሆን የእምነት አቋማችንን ፈትሸን ነገን ብሩህ ለማድረግ እንሥራ። ከትናንት ብንዘገይ ከነገ መቅደም አለብን። ነገን ለመቅደም ደግሞ ዛሬን እንኑርበት “የመዳን ቀን ዛሬ ነው”

በዚህ መንፈስ ለራስ ለሀገር ለወገንና ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት የምናቅድበት፤ መሥራት የምንጀምርበት፤ በመሥራት የምናሳልፈውና ፍሬ የምናይበት ዘመን ያድርግልን።

                                                         ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Written By: admin
Date Posted: 9/11/2011
Number of Views: 7494

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement