View in English alphabet 
 | Thursday, April 25, 2024 ..:: ስብከተ ወንጌል ::.. Register  Login
  

ገዳመ ቆሮንቶስ

ቆሮንቶስ የግሪክ ከተማ ናት። ከአቴናም 75 ኪ.ሜ. ያህል ትርቃለች። በአዲስ ኪዳን ዘመን ስድስት መቶ ሺህ ሰዎች የሚኖሩባት ትልቅ ከተማ ነበረች። አቀማመጧ በሁለቱ የግሪክ አውራጃዎች በመቄዶንያና በአካይያ መካከል በሚገኘው ልሳነ ምድር ነበረ።

ከተማይቱ የተመሠረተችው በባሕር መገናኛ ላይ በመሆኑ ከምሥራቅና ከምዕራብ ለሚመጡ መርከቦች ምቹ ወደብ ነበረች። ከዚህም የተነሣ ንግድ እየደራባት ሄደ። ከተማይቱም እጅግ ተለወጠች። የከተማይቱ ነዋሪዎች የሚያመልኩት አፍሮዳይቲ የምትባለዋን የፍቅር አምላክ ነበር። «ቆሮንቶሳዊ» መባል የስድብ ስም እስኪሆን ድረስ የዝሙት ኃጢአት በከተማይቱ በዛ። አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ግሪኮች ሲሆኑ ብዙ ሮማውያንና አይሁዶች ይኖሩባት ነበር።

ገዳመ ቆሮንቶስ በቆሮንቶስ ተራራ ላይ የተመሠረተ ሲሆን በኢያሪኮ ይገኛል። ከኤልሳዕ ምንጭ ዋናውን መንገድ ወደ ቀኝ በመተው በግራ በኩል ባለው ጐዳና በመጓዝ ቆሮንቶስ ተራራ ሥር ይደረሳል። ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ለመሄድ ተራራውን በእግር መጓዝ ግድ ይላል። ዳገቱን ጨርሶ ከተራራው መካከል የሚገኘው ጌታ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት የጾመበት ሥፍራ ተለይቶ ይታያል። /ቅድስት ሀገር፤ ገጽ 111-112/ በዚህ ሥፍራ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ታንጾበት ነበር። ኋላም ለ135 ዓመታት ጠፍቶ /ባዶ/ ሆኖ ነበር። በ1874 ዓ.ም. ግሪኮች ድንቅ ቤተ ክርስቲያን አሠርተውበታል፤ ገዳምም ገድመውበታል።

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ፤ ተራበ። በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል።

ዲያብሎስ ጌታችንን እንዴት ፈተነው፤ ጌታስ እንዴት ረታው?
  1. ዲያብሎስ በምግብ በእንጀራ ፈተነው፣ ጌታችንም በመራቡ ድል ነሳው «ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም» እንዳለው።
  2. ጌታችንን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል «የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ወደ ታች ራስህን ወርውር» ብሎ ፈተነው። ጌታችንም «ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፎአልና» ብሎ ረታው።
  3. ጌታችንን እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወስዶ የዓለምን መንግሥት ክብራቸውን ሁሉ አሳይቶ «ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ» ብሎ ፈተነው። ኢየሱስ ክርስቶስም «ሂድ አንተ ሰይጣን ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና ብሎ አሳደደው፤ ያንጊዜም ዲያብሎስ ተወው። እነሆም መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር። /ማቴ. ፬፥፩-፲፩/።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስስት የመጣበትን በትዕግሥት፣ በትዕቢት የመጣበትን በትህትና፣ በፍቅረ ንዋይ /ገንዘብን በመውደድ/ የመጣበትን በጸሊአ ንዋይ ድል ነስቶ ድል መንሳትን አስተምሮናል። በገዳሙ የውጭ በረንዳ ላይ ወጣ ብሎ ቁልቁል ሲታይ እጅግ በጣም ያስፈራል።

በእዚህ ላይ ሆኖ የኢያሪኮን ከተማ ልምላሜ፣ የዮርዳኖስን ወንዝ ሸለቆ፣ የኦሞን ተራራ የተባለውን አርቆ አሻግሮ ለማየት ይቻላል። ጌታ በቆሮንቶስ ተራራ የተፈተነበትን በእግረ ሥጋ ረግጦ፣ በዓይን ዓይቶ ምስክር ለመሆን እንዲያበቃን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፦ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ድረ ገጽ የቀድሞ ሕትመት

Written By: admin
Date Posted: 4/2/2012
Number of Views: 10674

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement