View in English alphabet 
 | Wednesday, April 24, 2024 ..:: ስብከተ ወንጌል ::.. Register  Login
  

ወዴት ነህ? /ዘፍ. ፫፥፱/

በቀሲስ ብርሃኑ ጎበና


በምክረ ከይሲ ተታልለው ትዕዛዘ እግዚአብሔርን የጣሱት አዳምና ሔዋን ዕራቁታቸውን እንደሆኑ ባወቁ ጊዜ የበለስን ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም በማድረግ የአምላካቸው የእግዚአብሔርን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰምተው በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ ወዴት ነህ? አለው። /ዘፍ. ፫፥፯-፱/።

የአዳምና የሔዋን ልጆች እንደመሆናችን የውድቀታቸው መንስኤም ሆነ የድኅነታቸው መሠረት ከእኛ ጋር የተገናዘበ ነው። አዳምና ሔዋን ትዕዛዘ እግዚአብሔርን የጣሱት ከጸጋ እግዚአብሔርም ሊራቆቱ የቻሉት እንዴት ነበር? የሚለውን መጠይቅ አንስተን ለውድቀታቸው መንስኤ የሆነውን እንመርምር። በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ የገባው ሰይጣን አዳምንና ሔዋንን ከእግዚአብሔር መንገድ ያስወጣቸው ደረጃ በደረጃ እያዋዛ መሆኑን እንገነዘባለን። አዳምና ሔዋን ከንጽሕና እርካብ እንዴት እንደወረዱ ስናጤን፦


መነሻው፦ የሔዋንና የእባብ አጉል ጓደኝነት ነው።
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ክፉ ባልንጀራ መልካሙን ዓመል ያበላሻል” /፩ ቆሮ. ፲፭፥፴፫/ በማለት እንዳስገነዘበው በእባብ ሥጋ ተሰውሮ የመጣው ሰይጣን ሔዋንን የቀረባት ለማሳት በመሆኑ የሔዋንን ጓደኝነት ለምን ሻተው ብለን አንጠይቅም የመጣበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚያዋጣውን መንገድ ሁሉ ከመጠቀም የሚያግደው ነገር የለምና። ሔዋን ግን “ከአነጋገር ይፈረዳል ከአያያዝ ይቀደዳል” እንዲሉ አበው፣ መጀመሪያ ከእባብ ሠላምታ ንግሥተ ሰማይ ወምድር ሳትሆን ንግሥተ ሰማይ ብሎ መጥራቱ ቀጥሎ ክፉ ምክሩ “ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።” ከሚለው የተነሳ ልብዋ ሊጠረጥርና ከእርሱ ጋር ያላትን ግንኙነት ልትቆርጥ ይገባት ነበር። የሌላትን ክብር እንዳላት አድርጋ ሠላምታውን በደስታ ተቀብላ በእባብ ውስጥ ላደረው ባላጋራ ጥርጊያ መንገዱን ማስተካከል አልነበረባትም።

“ከማያምን ጋር በማያመች አካሄድ አትጠመድ” /፪ ቆሮ. ፮፥፲፬/ እንዳለው ቅዱስ ጳውሎስ አብረናቸው የምንውላቸው ሰዎችና የምንውልበት ቦታ ነው ለመንፈሳዊ ሕይወታችን መዳከምና ብሎም መጥፋት በር የሚከፍተው “ከማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ” የሚለው አባባል ይህን እውነታ የሚገልጽ ነው። አምኖን በእህቱ ላይ አስነዋሪ ድርጊት ሊፈጽም የቻለው በዚህ የተነሳ በወንድሙ በአቤሴሎም እጅ የተገደለው በኢዮናዳብ ክፉ ምክር መሆኑን ልብ ይሏል። /መጽ. ሳሙ. ካልእ ፲፫፥፭/።

ስለዚህ መንፈሳውያን ከማን ጋር ልንውል ከማን ጋር ልንመክር ማንን ስለ ሕይታችን ልናማክር እንደሚገባን ማወቅ ይኖርብናል። “ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?” /ማቴ. ፯፤፲፮/ እንዳለ ጌታ በሕይወት ከማይመስሉን ሰዎች ለመንፈሳዊ ሕወታችን የሚጠቅም አንዳች ነገር እናገኛለን ብለን አንጠብቅ።

ምኞት፦ በእባብ ሥጋ የተሰወረ ዲያብሎስ ሔዋንን ጓደኛ ካደረገ በኋላ የመጀመሪያ ተግባሩ ያደረገው በሔዋን ልቡና ውስጥ ምኞትን ማስረጽ ነበር። “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዟልን?” የሚለውን ተንኮል ያለበትን ጥያቄ የጠየቀው ክፉ ምኞትን በሔዋን ሕሊና ላይ ለመትከል መንገድ ሲከፍት ነው እንጂ ይህ ተሰውሮት አልነበረም። የተደገሰላትን መጥፎ ድግስ ያላወቀች ሔዋን ገር ገሩን በማሰብ “በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ እግዚአብሔር አለ፦ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም።” በማለት መለሰች።

ያሲያዘችውን ጫፍ ይዞ ወደ እርሱ ፈቃድ በምኞት ይስባት ጀመር “ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉውን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” የእብድ ባልንጀራ ድንጋይ ያቀብላል እንዲሉ ክፉው ባልንጀራ ዲያብሎስ ለሔዋን በእግዚአብሔር ላይ የምትወረውረውን የክህደት ድንጋይ በእጅዋ አቀበላት።  “ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች” የሚለውን አባባል ስንመረምረው እናታችን ሔዋን ከዚያ በፊት አስጎምጅቷት የማያውቀው የበለስ ፍሬ ዛሬ እንዴት ሊያስጎመጃት ቻለ? አዳምና ሔዋን በገነት የኖሩት ሰባት ዓመት እንደሆነ ሊቃውንት ያስተምራሉ ይህን ያህል ዘመን በገነት ስትኖር ትዕዛዘ እግዚአብሔርን መሠረት አድርጋ አይደለም ለመብላት ለማየት እንኳን ያልደፈረችውን ለመብላት እስከ መጎምጀት ያደረሳት ምንድር ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ግልጽ ነው፤ ዲያብሎስ በልብዋ ላይ የተከለው አምላክ የመሆን ምኞት ነው።

በሕገ እግዚአብሔር አጥር ታጥረን ከምንኖርበት መንፈሳዊ ሕይወት በሰይጣን ተገፍተው በቀረቡንም ሆነ እኛው ይሆኑናል ብለን ባቀረብናቸው የክፋት ኃይሎች አማካይነት ያልኖርንበት ወይንም አሽቀንጥረን የመጣነው የዓለም ሕይወት አስደሳችነት ይተረክልናል። ክፉውን ዘር በሕሊናችን እንዲዘሩ በጎ ፈቃዳችንን ያገኙት ወገኖች በምኞት ፈረስ አፈናጠው ሽምጥ አስጋልበው ሲመልሱን በዓለም ምኞት እንጠለፋለን “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” /ያዕ. ፩፥፲፬/ እንደተባለው ተዳፍኖ የነበረውን ፈቃደ ሥጋችንን እንዲያነሳሱት አርነት በሰጠናቸው ሰዎች አማካይነት በምኞት ማዕበል እንዋጣለን።

ድፍረት፦ ዲያብሎስ በሕሊናዋ አምላክ የመሆን ምኞትን ከለኮሰባት በኋላ እናታችን ሔዋን የድፍረት ኃጢአት ገዛት። ለሰባት ዓመታት ያህል በፍጹም ታዛዥነት ጠብቃው የኖረችውን ሕግ ዲያብሎስ በምኞት ፈረስ ሽምጥ ባስጋለባት በዚያች ቅጽበት ናደችው። ለመብላት ያማረ፣ ለዓይን የሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም መልካም እንደሆነ የታያትን ፍሬ ወሰደችና በላች ለባልዋም አበላች። የፈጣሪዋን ትዕዛዝ ለመተላለፍ ምክረ ዲያብሎስ ድፍረት ሰጣት።
 
በእኛም ላይ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ የሚያርገው ይህንኑ ነው። በምኞት ሰመመን ይወስደንና ሕገ እግዚአብሔርን በድፍረት እንድንጥስ ያደርገናል በፍጹም ትህትና የተመላለስንበትን ሕይወት በቅጽበት ለውጠን በትዕቢት እንታጀራለን፣ በአፍአ ሳለን እናከብራት የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ውስጥዋ ስንገባ የደፋሮችን ምክርና አካሄድ ተከትለን እንደፍራታለን፣ ለዘመናት የኖርንበት መንፈሳዊውን ሕይወት በአጓጉል ሰዎች አደፋፋሪነት ምን ይመጣብኛል በሚል ድፍረት እንተወዋለን።

በድፍረት የጣሱት ትዕዛዘ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ከፀጋ እግዚአብሔር አራቆታቸው እንጂ የተመኙትን አምላክነት አላስገኘላቸውም።
 
የፀጋ መገፈፍ፦ በምክረ ከይሲ ተመርተው ትዕዛዘ እግዚአብሔርን ጥሰው የበሉት በለስ ለአዳምና ሔዋን አይደለም የአምላክነት ክብር ሊያስገኝላቸው እንዲህ ተብሎ እንደተገለጸው የሰውነት ክብርንም አሳጥቷቸዋል “የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ” /ዘፍ. ፫፥፯/።

በድፍረት የጣሱት ሕገ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ከእግዚአብሔር ለይቷቸዋል። ከእግዚአብሔር መለየታቸው ደግሞ በፀጋ ከእግዚአብሔር አግኝተውት የነበረውን ሁሉ እንዲያጡ አድርጓቸዋል። ዕራቁታቸውን መቅረታቸው የሚያሳየው ይህንን ነው። አዳም በተፈጠረ በአርባ ቀኑ ሔዋን በተፈጠረች በሰማንያ ቀኗ ያገኙትን የልጅነት ፀጋ አጥተዋል። የሚከተለው መርገም ደርሶባቸዋል “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛዋለሁ በጭንቅ ትወልጃለሽ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል እርሱም ገዥሽ ይሆናል። አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ። ወደ ወጣህባት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራህን ትበላለህ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና።” /ዘፍ. ፫፥፲፮-፲፱/።

ዛሬም ቢሆን የተሸለ ሕይወት የሚገኝ መስሎን ሕገ እግዚአብሔርን በድፍረት ጥሰን በመሄድ የምናገኘው ምንድር ነው? ሰላም የሌለበት፣ በሥጋት የታጠረ፣ ጭንቀት የሞላበት ሕይወት ፀጋ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በሚሆንበት ጊዜ የምንለብሰው ያሞቀናል ያደምቀናል፤ የምንበላው ያጠግበናል ጤና ይሆነናል፤ የምንጠጣው ያረካናል፤ የምንሠራው ይባረክልናል፤ ጥቂቱ ይበዛል ከሥጋት ነጻ የሆነ ሰላማዊ ኑሮ እንኖራለን። ወዴት ነህ? የሚለው ጥያቄ የለብንም በተሰማራንበት ጸንተናልና ሕገ እግዚአብሔርን በድፍረት በመጣሳችን ራሳችንን የምንሸሽግበት መሸሸጊያ ፍለጋ አንማስንም። ከወንጀል፣ ከሕሊና ወቀሳ ከሰሳ ነፃ ነንና ማድረግ የሚገባንን በማን አለብኝነት ሳናደረግ ቀርተን ከሚመጣብን ፍርድ እንድናለን።

በድፍረት ሕገ እግዚአብሔርን የሚጥሱ ሰዎች  ፀጋቸውን ስለሚገፈፉ እንደ አዳምና ሔዋን ዕርቃናቸውን መሆናቸው ስለሚታወቃቸው ሁልጊዜ ከለላ የሚሆናቸው ጥሻ ያስሳሉ ግን ነውራቸውን ለመሸሸግ የሚያደርጉት ሩጫ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው። ሰው በክፉ ስራው ከሰው ቢሸሸግ ከሕሊናው ግን መሰወር አይችልም። ስለምንጥሰው ሕግ የሕሊና ወቃሽ እንዳለብን ማስተዋል ይገባል። ስለዚህ የዚህ ሁሉ መፍትሄ፣ የተገፈፍነውን ፀጋ ለማስመለስ ንስሐ የማያወላዳ ምርጫ ነው።
 
የሞት ፍርድ፦ “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ ነገር ግን መልካምንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ።” /ዘፍ. ፪፥፲፯/ የሚለውን አምላካዊ ቃል አዳምና ሔዋን ተላልፈው በተገኙ ጊዜ ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ አግኝቷቸዋል።

“ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” /ያዕ. ፩፥፲፭/ እንደተባለ በእባብ ሥጋ የተሰወረ ዲያብሎስ በሔዋን አእምሮ ላይ የሳለው ከንቱ ምኞት በፍጥነት አድጎ ኃጢአትን ወልዷል። በድፍረት ትዕዛዘ እግዚአብሔርን ጥሰው በለስን ቀጥፈው በልተዋል። በዚያች ቅጽበት ሞተ ነፍስ አግኝቷቸዋል ማለትም ፀጋቸው ተገፍፏል፣ ባሕርያቸው ጎስቁሏል፣ ክብራቸውን አጥተዋል። በኋላም የሥጋ ሞት አግኝቷቸዋል፤ በአካለ ነፍስም ወደ ሲዖል ወርደዋል።

የዓይናችንን አምሮትና የሥጋችንን ፍላጎት ብቻ ተከትለን የኃጢአት ተገዥ ከሆንንበት ሕይወት በፍጥነት በንስሐ ካልወጣን የእኛም ዕጣ ያው ነው። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ “ከወዴት እንደወደቅህ አስብ ንስሐ ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ።” /ራእ. ፪፥፭/።   


ወስብሐት ለእግዚአብሔር



Written By: admin
Date Posted: 7/27/2012
Number of Views: 6898

Return

  
Copyright 2016 by Mahibere Kidusan USA Center  | Terms Of Use | Privacy Statement