“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።” የማርቆስ ወንጌል 16፥15
ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በ ኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ከጳጉሜን 1985 ዓ. ም ጀምሮ ለ18ዓመታት በየወሩ አሁን ደግሞ በየሁለት ሳምንቱ በመታተም የቤተክርስቲያንን ዜናዎችን፣ ትምህርተ ወንጌልን፣የአባቶችን ሕይወት፣ ከምዕመናን የሚነሱ መንፈሳዊ ጥያቄዎችን ምላሽ በመስጠት፣ የገዳማት እና አድባራት እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንቅስቃሴ በመዘገብ ምዕመናን በማስተማር፣በማሳወቅ እና መንፈሳዊ ችግር/ፈተና ፈቺ በመሆን አገልግሎት ስትሰጥ የኖረች የቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ነች::
ስምዐ ጽድቅ መታተም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ባቀረበቻቸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት የሚጻረር ጽሁፍ አቅርባ አታውቅም:: ይህም የሆነበት ምክንያት ማንኛውም ጽሁፍ በጋዜጣዋ ላይ ከመውጣቱ በፊት ቅዱስ ሲኖዶስ ለማኅበሩ በሰጠው ስልጣን መሰረት ማኅበሩ ባቋቋመው የነገረ ሃይማኖት እና የጋዜጠኝነት ሙያ ጥልቅ ዕውቀት ባላቸው የኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት ተደጋግሞ ስለሚገመገም ነው፣ በተጨማሪም የታወቁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በነፃ ሓሳባቸውን እና ምክራቸውን በመለገስ ለማስተካከል ስለሚተባበሩ ነው::