ትንሣኤ (በመልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን)
በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረው አዳም
አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ፍጥረታትን ለተከታታይ አምስት ቀናት ከፈጠሩ በኋላ በስድስተኛው ቀን /ዓርብ/ በነግህ እንዲህ አሉ። ‹‹ንግበር ሰብአ በአርዓያነ ወበአምሳሊነ፤ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር›› /ዘፍ ፩፥፳፮/። ሥላሴ በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ማለታቸው እንዴት ነው ቢሉ ሥላሴ ለባውያን፣ ነባብያን፣ ሕያዋን ናቸው። አዳምም ለባዊ፣ ነባቢ፣ ሕያው ነው። ሥላሴ ፍጹም መልክእ እንዳላቸው አዳምም ፍጹም መልክእ አለው። ሥላሴ በልብ በቃል፣ በእስትንፋስ ይመሰላሉ ለሰውም ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አለው። ሥላሴ በባሕርያቸው የሚገዙትን አዳም በጸጋ እንዲገዛ ሥልጣን ሰጥተውታል።